በ2016 የውድድር ዓመት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚታዩ አዳጊ ክለቦች መካከል አንዱ ሻሸመኔ ከተማ ነው። በሶስት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ በቆየው ከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን ከሆኑት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሻሸመኔ ከተማ በአሰልጣኝ ጸጋዬ ወንድሙ እየተመራ ከ15 አመት በኋላ ወደ ትልቁ የውድድር መድረክ ተመልሷል።
ሻሸመኔ ከተማ ለስኬት ሲደርስ የቀድሞ ተጫዋች የአሁኑ አሰልጣኝ ጸጋዬ ትልቅ ሚና አላቸው። ወደ አሰልጣኝነት ሙያ ከገቡ በኋላ አቃቂ እና ኢትዮጵያ መድንን የመሩት እኚህ ሰው በቀጣይም ሻሸመኔ ከተማን በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የማድረግ እቅድ አላቸው። ሻሸመኔ ከተማ በ2000 የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፤ ላለፉት 15 ዓመታት በከፍተኛ ሊግ ሲወዳደር ቆይቷል።
ባለፉት ዓመታት የከፍተኛ ሊግ ቆይታው አጥጋቢ እንቅስቃሴ ማሳየት ያልቻለውን ሻሸመኔ ከተማን የተረከቡት አሰልጣኝ ጸጋዬ፣ በራሳቸው መንገድ ተጫዋቾችን ለውድድር በማዘጋጀት ክለቡ በተሳተፈበት የሲቲ ካፕ ውድድር ጥሩ ብቃት እያሳዩ ወደ ውድድር መግባታቸውን ያስታውሳሉ።
በከፍተኛ ሊግ ላይ ከየምድባቸው አንደኛ የወጡ ክለቦች ብቻ ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀሉ እንደመሆኑ ፉክክሩ ፈታኝ እንደነበር አሰልጣኝ ጸጋዬ ያስታውሳሉ። ነገር ግን የክለቡ ግብ ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀለ እንደመሆኑ ለውድድሩ ምን ያስፈልጋል እንዲሁም በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር ምን በምን መልኩ መዘጋጀት ይገባል የሚለውን ከልምድ ተነስቶ በማቀድ እንደተንቀሳቀሱ አሰልጣኙ ይናገራሉ።
በዚህም ክለቡ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በመሪነት ቢቆይም ዙሩን ያጠናቀቀው ግን ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በእኩል ነጥብ ነበር። በሁለተኛው ዙር ደግሞ ጥቂት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ በማካተት እንዲሁም በነበሩባቸው ድክመቶች ላይ በመስራት መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሎ አራት ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮን መሆኑንና ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሱን በጊዜ እንዳረጋገጠ ያስረዳሉ።
ለዚህም አንዱ ምክንያት የቡድኑ አባላት በተመሳሳይ ስሜት እና ዓላማ ተግባብተው መጫወታቸው እንደነበር አሰልጣኝ ጸጋዬ ይናገራሉ። “በጥንቃቄና አብረዋቸው ከሚጫወቷቸው ቡድኖች ጋር በምን መልኩ መቅረብ እንደሚገባቸው አውቀው ከመገኘታቸው በላይ ተጫዋቾቹ ቆራጥ ነበሩ” የሚሉት አሰልጣኙ ጸጋዬ፣ ከፍተኛ ሊግ እጅግ ጠንካራና ተደጋጋሚ ጨዋታ ያለበት ውድድር ቢሆንም ሻሸመኔ ከተማ በሊጉ ታሪክ ብዙ ጨዋታ እየቀረው ማለፉን ያረጋገጠ ቡድን በመሆንም ታሪክ እንደሰራ ያስረዳሉ።
በዚህም ሂደት ከተጫዋቾች ባሻገር የስልጠና ቡድኑ እንዲሁም የክለቡ አመራሮች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር። ክለቡ በከተማዋ ከንቲባ የሚመራ እንደመሆኑ በልምምድ ወቅትም ይሁን በተለያዩ ጊዜያት ከንቲባው መገኘታቸውና ማበረታታቸው ትልቅ እገዛ ማድረጉን አሰልጣኙ ተናግረዋል።
በከፍተኛ ሊግ ጠንካራ የነበሩ ቡድኖች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ቢያድጉም ተወዳዳሪ መሆን ባለመቻላቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደመጡበት ሲመለሱ ይስተዋላል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሻሸመኔ ከተማ ተመሳሳይ ነገር እንዳይገጥመው ዝግጅቱን ከወዲሁ መጀመሩን ጠቁመዋል። አሰልጣኝ ጸጋዬ እንደተለመደው ሳይሆን በሊጉ ክስተት የሆነ ቡድን ይዘው ለ2016 የውድድር ዓመት እንደሚቀርቡ እምነት አላቸው።
አሰልጣኝ ጸጋዬ የውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሻሸመኔ ከተማን ሲረከቡ ክለቡን ለፕሪሚየር ሊግ ለማብቃት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ በዚህም ስኬታማ መሆናቸውን ይናገራሉ። በቀጣይም በዋናው ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ ከወዲሁ እየሰሩ ይገኛሉ። ለዚህ እንዲረዳቸውም ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ አስበዋል። ተፎካካሪ ክለቦች ስላሉበት ሁኔታም ዳሰሳዊ ጥናት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ ባለፈ ቡድናቸውን በወጣት ተጫዋቾች ላይ የተመሰረተ በማድረግ በፕሪሚየር ሊጉ ክስተት የሚሆን ቡድን የመገንባት ሃሳብ አላቸው። ለሊጉ ድምቀት ይሆናል ያሉትን የክለቡ ደጋፊዎችን ይዘውም ውድድሩን የሚመጥን ተፎካካሪ ቡድን እንደሚሰሩ ትልቅ ተስፋ ሰንቀዋል። አሰልጣኙ ያሰቡትን ለማሳካት የመጀመሪያው ዓመት ዕቅዳቸው ክለቡን በተረጋጋ ሁኔታ በሊጉ እንዲቆይ ማድረግ ነው። ያላቸውን ጊዜ ተጠቅመውም ቡድኑን በጥሩ መንገድ ገንብተው ቃላቸውን በመተግባር ለመለወጥ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመዝለቅ በዋናነት አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ ፋይናንስ ነው። የክለቡ አመራሮችም ይህንን የሚገነዘቡ በመሆኑ በዚህ ዓመት ሲያደርጉ በቆዩት መጠን በጠንካራ ጥረትና ክለቡን ከሚወዱት አካላት እንዲሁም ከተለያዩ የገንዘብ ምንጮች ክለቡን ይደግፋሉ የሚል ዕምነት እንዳላቸው አሰልጣኙ ተስፋ አድርገዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የከተማዋን ከንቲባ ጨምሮ የክለብ አመራሮች፣ የከተማው እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ቡድኑን ሲደግፉ ለነበሩ አካላት ላደረጉት እገዛ አሰልጣኙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም