ውድድር ከጀመረ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፤ ዛሬም ድረስ ግን ሳይታክት በታላላቅ የውድድር መድረኮች መሮጡን ቀጥሏል፡፡ በዚህም ጎልሶ እንካን የትልልቅ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሳይስብ ቀርቶ አያውቅም። የረጅም ርቀት፣ የመምና አገር አቋራጭ ውድድሮች ንጉሡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ባለፈው ማክሰኞ የ41ኛ ዓመት ልደት ሻማውን መለኮሱን ተከትሎም መላው ዓለም የእንኳን አደረሰህ መልእክቱን አዥጎድጉዶለታል። ለቁጥር ከሚያታክቱ የታላላቅ መድረኮች ስኬቱ ባሻገር ለማመን በሚከብዱ በርካታ ክብረወሰኖች ደምቆ ረጅሙን የአትሌቲክስ ሕይወት እያገባደደ ይገኛል፡፡
የብዙዎች ብርታትና ጥንካሬ ተምሳሌት በመሆን አንበሳው አትሌት ቀነኒሳ በስፖርቱ ዓለም ታሪክ ውስጥ በጉልህ ስፍራ ይቀመጣል፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ የታየ የምንጊዜም ምርጡ አትሌት ነው። ‹‹አቦሸማኔው›› የተወለደው እአአ ሰኔ 13 ቀን 1982 ነው፡፡ የትውልዱ ስፍራውም የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ ነው፡፡ የአትሌቲክስ ሕይወቱን የጀመረውም ገና በለጋ እድሜው ነበር። ሲሮጥ ያምርበታል፣ አትሌቲክስን በእውቀት ጭምር ነው የሚወዳደርበት፡፡ አስደናቂ ጽናትና ፍጥነት መለያው ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ከምን ጊዜውም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች ግንባር ቀደም ያሰኙት ምክንያቶች እነዚህ ናቸው፡፡ በኦሊምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናና በዓለም አገር አቋራጭ ከፍተኛ ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡
ቀነኒሳ በአገር አቋራጭ፣ በመም (ትራክ) እና በጎዳና ውድድሮች በርካታ ድሎቹ አገሩን አኩርቷል። በተለያዩ ውድድሮች ለኢትዮጵያ 26 የወርቅ ሜዳሊያዎችን አበርክቷል፡፡ የ5ሺ እና የ10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰኖችን ከ15 ዓመታት በላይ ተቆጣጥሮ ቆይቷል። የማራቶንን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት በ2፡01፡41 ሰዓት ያስመዘገበው ታላቅ አትሌት ዛሬም በርቀቱ ቀዳሚውን ሰዓት ለማስመዝገብ ያለው ፍላጎት አልከሰመም፡፡ በሩጫ ዘመኑ ከ120 በላይ ውድድሮችን አሸንፏል፡፡
ቀነኒሳ በኦሊምፒክ መድረክ ሶስት አስደናቂ የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያን የግሉ አድርጓል። በዓለም አገር አቋራጭ 16 የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ፣ በዓለም ቻምፒዮና አምስት የወርቅ እና አንድ የነሃስ ሜዳሊያ፣ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና 1 ወርቅ በአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ፣ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።
በ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ እና በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ፤ በ2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ በ5ሺ እና 10ሺሜትር ድርብ ድልን የተጎናፀፈበት አጋጣሚ የማይረሳ ወርቃማ ታሪኩ ነው። ቀነኒሳ ከ2003 ጀምሮ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለአራት ጊዜ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮን መሆን ችሏል። በመድረኩ በአጠቃላይ 5 የወርቅ ሜዳለያና 1 የነሐስ ሜዳለያ ባለቤትም ነው፡፡
ቀነኒሳ በትራክ ውድድር ካስመዘገበው አስደናቂ ስኬት በተጨማሪ በማራቶን ሩጫም የላቀ ውጤት አስመዝግቧል። እ.ኤ.አ. በ2014ቱ የፓሪስ ማራቶን ውድድር ስድስተኛውን የማራቶን ፈጣን ሰዓት በ2፡05፡ 04 አሸንፏል። እ.ኤ.አ. መስከረም 25 2016 የበርሊን ማራቶንን 2፡03፡03 በሆነ አዲስ የግል ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብም በወቅቱ የምንጊዜውም የማራቶን ሶስተኛው ፈጣን አትሌት ለመሆን በቅቷል፡፡ እአአ መስከረመ 29 ቀን 2019 የበርሊን ማራቶንን በ2፡01፡41 በሆነ ጊዜ በድጋሚ አሸንፏል፣ ይህም በ2018 የበርሊን ማራቶን ከተመዘገበው የኤሊዩድ ኪፕቾጌ የዓለም ክብረወሰን በ2 ሰከንድ የዘገየ ነበር።
ዓለም የቀነኒሳን 41ኛ ዓመት የልደት በዓል ሲያከብር ኢትዮጵያዊው የረዥም ርቀት ሯጭ በአትሌቲክሱ ዓለም ያሳረፈውን አሻራ እያሰበ ነው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ አትሌት፣ የትራክና የጎዳና ውድድሮች ምርጥ አትሌትና የኢትዮጵያ የዓመቱ በጎ ሰው የሚሉ ክብሮችን መቀዳጀት የቻለውን ታላቅ አትሌት ወደፊትም በተለይ የማራቶን ክብረሰወሰን ለመስበር እየሰራ ነው። እኛም 41ኛ ዓመት የልደት በዓሉ አስመልክቶ እንኳን ተወለድክ ብለን ከብዙ በጥቂቱ የአትሌቲክስ ስኬቶቹን ለማስታወስ ወደናል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ11/2015