የ2023 የዓለም ስፔሻል ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ በጀርመኗ በርሊን ከተማ ለዘጠን ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል፡፡ በዘንድሮ ውድድር ከ190 ሀገራት የተወጣጡ 7000 የአእምሮ ውስንነት ያለባቸው አትሌቶች በ26 የስፖርቶች ዓይነቶች በሁለቱም ጾታ ውድድራቸውን ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከተሳታፊዎቹ ሀገራት አንዷ ስትሆን በሁለት ወንድና በሁለት ሴት አትሌቶች የምትወከል ይሆናል፡፡ ውድድሩ በጀርመን ኦሊምፒክ ስቴድም የሚካሄድ ሲሆን አትሌቶቹን የሚመሩ 30 ሺ አሰልጣኞች እና ለውድድሩ መሳለጥ 20ሺ በጎ ፍቃደኞች ዝግጁ መሆናቸው ታውቀል፡፡
ኢትዮጵያ እአአ በ2019 አቡ ዳቢ ላይ በተካሄደው የዓለም ስቴሻል ቻምፒዮና ተጋብዛ ተሳትፎዋን ካደረገች በኋላ ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ በመጀመርያ ተሳትፎዋም ሁለት የነሐስ ሜዳለያ ማሳካት ችላለች። ኢትዮጵያ የሚወክለው ብሔራዊ ቡድን የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቶ ከቀናት በፊት ወደ ውድድሩ ስፍራ ሽኝት ተደርጎለታል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉ ስፖርተኞች በልዩ ሁኔታ እንክብካቤና ድጋፍ የሚያስፈልገቸው ቢሆንም ከተለያዩ አካላት የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ልዑካን ቡድን በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ በትልቅ ውድድር ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ሲያቀና ግን በደማቅ መርሃግብር ተሸኝተል። የስፔሻል ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድኑ ከስድስት ወር በፊት በተደረገ ሀገር አቀፍ ውድድር የተመረጠ ሲሆን በዘንድሮ ኦሊምፒክ በአትሌቲክስ በተለይም በአጭር ርቀት፣ሪሌይ(ዱላ ቅብብል)ና ርዝመት ዝላይ በዋናነት ይሳተፋል፡፡ ቡድኑ በአትሌቲክስ ስፖርት ምድብ በአራት አትሌቶች (ሚሊዮን ያደታ፣ ኪሩቤል ንጉሴን፣ ጊፍቲ ገረመው እና ኤደን ተስፋዬ) ተወክሏል። ቡድኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ እና የተሻለ ሜዳሊያ ውጤት ለማምጣት ጥሩ ዝግጅት ማድረጉም ተጠቁሟል።
የዓለም ስፔሻል (ልዩ) ኦሊምፒክ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የአዕምሮ እድገት ውስንንነት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳትፋል። ውድድሩ የአዕምሮ እክል ያለባቸው ስፖርተኞች ችሎታቸውን ለማሳየት የሚያስችላቸው መድረክ ይፈጥራል ተብሎ ነው የሚካሄደው። ይህም የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ለማበረታታት እና የአዕምሮ እድገት እክል ያለባቸውን ስፖርተኞች ችሎታ ለማሳደግ ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል። ስፔሻል ኦሊምፒክ የአእምሮ እክል ላለባቸው ስፖርተኞች በተወዳዳሪ ስፖርቶች እንዲሳተፉ፣ በራስ መተማመን እንዲፈጥሩ እና ማህበራዊ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ልዩ መድረክ ይፈጥራል። ፉክክሩ ደስታን እንዲለማመዱ፣ ጓደኛ እንዲያፈሩ እና የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል ተብሎም ይታሰባል።
የኢትዮጵያ ቡድን በዓለም ስፔሻል ኦሊምፒክ መሳተፉ ሀገሪቱ የአካል ጉዳተኞችን ማካተት እና የአዕምሮ እክል ያለባቸውን ስፖርተኞችን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሚሆን ተጠቁማል። ይሁን እንጂ በውድድሩ የሚሳተፉ ስፖርተኞች የበለጠ ድጋፍና ትኩረት ሊሰጣቸውና ተሳትፋቸው ሊጨምር ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን አዳዲስ እና ነባር አትሌቶች አዋህዶ የያዘ ሲሆን በውድድሩ ላይ ውጤት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል። ስፖርተኞቹ በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ያጋጠሟቸው ፈተናዎች ቀላል እንዳልሆኑ አገር አቀፍ ኮሚቴው አስታውሳል፡፡
እንደ ስፔሻል ኦሊምፒክ ያሉ የስፖርት ተሳትፎዎች የማህበረሰብን ስሜት ለማዳበር እና የስፖርትን የመለወጥ ሃይል ለማጉላት ይረዳሉ። የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ የልዑካን ቡድን በዓለም ልዩ ኦሊምፒክ መሳተፉ ለአገሪቱ እና ለአትሌቶቹ ትልቅ ምዕራፍ ነው። በውድድሩ ላይ ሲሳተፉ ማክበርና ማበረታታት ይገባል። የአዕምሯዊ ውስንነት ላለባቸው ስፖርተኞች ሁሉን አቀፍ ሁኔታዎችን እና እድሎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ማጉላት፣ የአካል ጉዳተኝነትን፣ ማካተትን ማስተዋወቅ እና የሁሉንም ስፖርተኞች አቅም የማጎልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡
የስፔሻል ኦሊምፒክ የአዕምሮ እክል ያለባቸውን ስፖርተኞች በተመለከተ ቀድሞ የግንዛቤ ስራ መስራት ስፖርቱን ለማሳደግ ይበልጥ እድል ከመሰጠቱም በላይ የአዕምሮ እክል ያለባቸው ስፖርተኞች በስፖርት ውስጥ የመሳተፍ እና ንቁ የአኗኗር ዘይቤን የመምራት መሰረታዊ መብት ያጎናፅፋል ተብሎ ይታመናል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015