የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማናጅመንት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በማኅበረሰብ ሳይንስ ይዘዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደያዙ ስራ የጀመሩት በውሃ ዘርፍ ላይ ነው። በእርግጥ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 17 ዓመታት ያህል በዚሁ በውሃ ዘርፍ ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል – የዛሬው የዘመን እንግዳችን የውሃና መስኖ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪና የውጭ ጉዳዮች ኃላፊው አቶ አበራ እንዳሻው።
አቶ አበራ፣ ገና ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው ባይሰሩም፤ ለ14 ዓመታት ያህል ግን በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በውሃው ዘርፍ አገልግለዋል። ወደውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የመጡት ከ14 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ሲያማክሩ የቆዩት የቀድሞውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ሰለሽ በቀለን ነበር።
እኚህ የዛሬው እንግዳችን በተለያየ የስራ አጋጣሚ በተለይ ከውሃ ጋር በተያያዘ ጉዳይ የብዙ አገሮችን ተሞክሮ ለማየት እድሉን አግኝተዋል። በአንድ መንግስታዊ ድርጅት ውስጥ የሰራ አንድ ሰው የሚያከናውነው ተግባር ለአንድ አገር ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች እንደመሆኑ እርሳቸውም ከዚሁ የተነሳ በዘርፉ ያለውን የብዙ አገሮች ተሞክሮ ለማየትና ለመቅሰም ችለዋል።
በተለየያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት መስራታቸው እድሉን እንዲያገኙ አግዟቸዋል። አህጉር አቀፍ ተሞክሮዎችንም የመቅሰም እድል ያገኙም ሰው ናቸው። የዓለም አቀፍ የውሃ ጉባኤም ሆነ በሌላው የውሃ ጉባኤ መሳተፍም ችለዋል። የዛሬው እንግዳችን በውሃ ዘርፉ ላይ የካበተ ልምድ ያላቸው በመሆኑ አዲስ ዘመን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የሚመለከቱ የውጭ ጉዳዮችን ከተለያዩ ኤምባሲዎች፣ ከአጋሮችና ከሌሎች የልማት ፕሮግራም አጋሮች ጋር ያሉ ግንኙነቶችን በዋናነት ሚኒስተሩን ከሚያማክሩ ከእኚሁ ከአቶ አበራ እንዳሻው ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች ኢትዮጵያን ‹‹የውሃ ማማ ናት›› ይሏታል፤ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ?
አቶ አበራ፡- በእርግጥ ከዚህ ቀደም በነበሩት የጥናት ውጤቶችና መሬት ላይ ያሉት ጠቋሚ መረጃዎች በሚያሳዩት መሰረት ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት ሊባል ይችላል። ለምሳሌ አንዱ ማሳያ ወሰን ተሻጋሪ ወንዝ ያሏት መሆኑና ከእነዚህም መካከል በሙሉ አቅማቸው የሚፈሱ ትልልቅ ወንዞች በመሆናቸው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃም ሌላው ማሳያ ነው።
ይሁንና ‹‹የውሃ ማማ ናት›› የምንለው በንጽጽር ነው። ለምሳሌ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ከሱዳን ወይም ከግብጽ አሊያም ከጂቡቲ ወይም ከኬንያ አንጻር ስናይ ነው እንጂ ከሌለች ሀገራት አንጻር ‹‹ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት›› የሚለውን ለመጠቀም በአሁን ወቅት ይከብዳል። ምክንያቱም አንዳንድ የሩቅ ምስራቅ አገራትን ስናይ በአብዛኛው በውሃ የተከበቡ አገራት ናቸውና ከዛ አንጻር እኛ ምን ያህል የውሃ ማማ ነን ብለን እንናገራለን የሚለው መጤን ያለበት ነው።
ሌላው ከዚህ ቀደም የነበሩ አስተምህሮዎች ‹‹ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት›› የሚለውን አባባል ያሰረጹት ይመስለኛል። ለምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ ናት›› ሲባል እውነት ውሃው አለን ወይ የሚለው ነገር አጠያያቂ ነው፤ ይህ እውነት ስለመሆኑ ጥናት ተጠንቶ ግኝቱ ይፋ የሆነው መቼ ነው። ከዛ በኋላስ ምን ሆነ፤ ከነበረው ውሃስ በትነትም ሆነ በአገልግሎት ምን ያህሉ ሔደ፤ የሚለው መፈተሸ አለበት። ከዚህ አኳያ እኛ አንድን ነገር በመፈተሽ ረገድ ብዙም ብርቱ አይደለንም። ከዚህ ጎን ለጎን የአቅም ውስንነቱም አለብን።
ካለፉት ከሃያና ሰላሳ ዓመታት በፊት እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ‹‹የውሃ ማማ ነን›› ካልን ልንሆን አንችልም፤ ሌላውን ትተነው አሁን ባለው ሁኔታ ያሉን ወንዞች ወቅታዊ ናቸው። ወንዞቻችን የፍሰት መጠናቸውም ሆነ የፍሰት ጊዜያቸው እየቀነሰ ነው። ከዚህ አንጻር እኔ ‹‹የውሃ ማማ ነን›› ብዬ ለመናገር አልደፍርም። ስለዚህ በአሁን ወቅት ‹‹የውሃ ማማ ነን›› የሚለው አባባል አያስኬድም። እንዲያውም ወንዞች እየነጠፉ ባለበት በዚህ ጊዜ ‹‹የውሃ ማማ ነን›› ማለት ራስን እንደማሞኘት እመለከተዋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣዮቹ ጊዜያት ጦር ሊያማዝዝ የሚችለው አንገብጋቢ ጉዳይ ነዳጅ ሳይሆን ውሃ ነው ይባላል፤ ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ያላት እድል ምንድን ነው?
አቶ አበራ፡– ይህ አባባል ትክክል ነው። ለምሳሌ በአገራችን ብቻ ያለውን አንድ ምሳሌ ላንሳ፤ 17ቱ ዘላቂ የልማት ግቦች ተብለው የታቀዱ ስራዎች አሉን። በዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ ከሚካተቱት መካከል የምግብን ዋስትና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ኃይል እና ሌሎችም ይገኙበታል። እነዚህ ሁሉ ትስስራቸው ከውሃ ጋር ነው። እነዚህን 17ቱን ግቦች ብዙዎቹን ከውሃ ውጪ ማሰብ አይቻልም።
እንደሚታወቀውና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደምንሰማው ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ የማዕድን ሀብት በተለይ ነዳጅ እንዳላት ይታወቃል። ይህም ተስፋ ሰጪና አበረታች ነው እየተባለ ሲነገር ይሰማል። ነገር ግን ከነዳጅ ባልተናነሰ የሚያገለግለን ያለንን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ስንችል ነው ባይ ነኝ። በዚህ ብዙ ነገሮችን መቀየር እንችላለን ብዬ አምናለሁ።
ቴክኖሎጂው በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ የአቅም ውስንነት አጠቃላይ የኢኮኖሚ የማስፈጸም፣ የዕውቀትና የክህሎት እንዲሁም የሰው ኃይል ውስንነቶች ጠርንፈው ያዙን እንጂ አቅም ቢኖር ኖሮ ወንዞቻችንን በመጠቀም የበለጠ ውጤታማ መሆን እንችል ነበር።
ለምሳሌ እስራኤልን ማንሳት ይቻላል። እስራኤል በዓለም ደረጃ በግብርናው ቁጥር አንድ መሆን የቻለችው ምንም ለም አፈር በሌለበት ጪንጫ በሆነ መሬት ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ነው። በአሁኑ ወቅት ፍራፍሬና አትክልትን ወደውጪ አገር በመላክ እስራኤልን የሚወዳደር የለም። በረሃማ የሆነውንም ስፍራ ወደገነት ቀይረዋል ማለት ይቻላል።
እንደ እድል ሆኖ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን በመወከል ለስድስት ዓመት ያህል ሰርቻለሁ። ስራውን ስንሰራ በትግራይ ክልል 13 ወረዳ፣ በአማራ ክልል 27 ወረዳ በጥቅሉ ለመጀመሪያ አምስት ዓመት ስንሰራ የነበረው 40 ወረዳ ላይ ነበር። ይህ ፕሮግራም ከአስር በላይ የሚሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ወደ አንድ ያመጣ ነው። ይህን ስራ ስንሰራ እስራኤላውያን ልምዳቸውን እንዲያጋሩን ጠይቀናቸው ነበር። በትግራይ ለቀላሚኖ እና ኤልሻዳይ ልምዳቸውን አጋርተው ያመጡት ለውጥ የሚያስገርም ነው።
ሰርቶ ማሳያውን እንደ ማሰልጠኛ አድርገው በመስራታቸውም የአካባቢውን ወጣቶች አሰልጥነው ቦታውን እንደ ልህቀት ማዕከል አድርገውት ሳይ ምን ያህል ቴክኖሎጂው ውጤታማ መሆኑን እንድገነዘብ የሚያደርገኝ አሰራር ነው። ምንም እንኳ አካባቢው በረሃማ ቢሆንም ያለውን ውሃ በአግባቡና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተሰራው ስራ አስደናቂም ጭምር ነው። ውሃ የልማት ቁልፍ ከመሆኑም በተጨማሪ ችግሮቻችንን የምናይበት መነጽርም ጭምር ነው ብዬ አስባለሁ።
ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪያል ፓርኮች በመስፋፋት ላይ ናቸው። ለአብነት ደግሞ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር እንድትገናኝ ተሰርቷል። እንዲሁም ደግሞ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን እና ከጂቡቲ ጋርም ለመገናኘት እየተሰራ ያለ ፕሮግራም አለ። እንዲሁም ከሱማሊያ ጋር የምንገናኝባቸው የልማት ፕሮግራሞችም አሉ። ዋናው የምንገናኝበት ደግሞ ኃይል ነው። 90 በመቶ ያህል የኃይል ምንጫችን ሃይድሮፓወር ነው። ስለዚህ ፕሮጀክቶችን ተፈጻሚ ለማድረግ ኃይል ማመንጨት የግድ ነው። ኃይል በሌለበት ቦታ ኢንዱስትሪ ልማት ሊታሰብ አይቻልም። ከዚህ አንጻር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ውሃችን ነዳጃችን ነው ማለት እችላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ያሏት አገር ናት፤ ይህ የቀጣናውን አገራት ከማስተሳሰር አንጻር ምን ሚና አለው?
አቶ አበራ፡- ኢትዮጵያ በጋራ የልማት ትብብር ፕሮግራም የምታምን እና የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ላይ አበክራ የምትሰራ ሀገር ናት። መቆም የሚቻለው በጋራና በመተባበር ነው፤ ይህ ካልሆነ በስተቀር ማንም ቢሆን በራሱ ብቻውን ሊቆም አይችልም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን የልማት ኮሪደር በሚል እየተሰራ ያለ ፕሮግራም አለ። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በእርሷ በኩል ያለውን ነገር ጨርሳለች ማለት ይቻላል። ለአብነት ፈጣን መንገዶች ተሰርተዋል። የአግሮፕሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ተሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የኢንዱስትሪያል ፓርኮች ተሰርተዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በእኛ በኩል ያለው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ተዘርግተዋል።
በኬንያ በኩል ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባይሆንም የተወሰነ ርቅት መሄድ ችለዋል፤ ነገር ግን በጣም ብዙ ነገር ይቀራቸዋል። ደቡብ ሱዳን ላይ ደግሞ ምንም አልተጀመረም ማለት ያስደፍራል። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ የሚሔደው የአባይ ውሃ ፍሰት አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ደቡብ ሱዳን ሰፊ መሬት አላት። ስለዚህ በመሪዎች መካከል ጠንካራ የሆነ የትብብር ስምምት ማዕቀፍ መኖር ቢችል ጥሩ የሆኑ የልማት አጋሮች መሆን ይቻላል። ምናልባትም አፍሪካን ከፍ የሚያደርጋት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገሮች ሊተርፍ የሚችል ምርት ማምረት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
ያንን ለማድረግ ግን በሐቅና መተማመን ላይ የተመሰረተ የአገራት የጋራ የትብብር ስምምት ማዕቀፍ መኖር አለበት። ይህ ከመጠባበቅ በዘለለ እና አንዱ ሌላውን ከመጠራጠር በዘለለ በባለሙያዎች የተፈተነ እና ለውሳኔ ሰጪ አካላት ግብዓት ሊሆን የሚችል ተጨባጭ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ አይነቱ ትብብር ካለ በርካቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል። ከዚህ ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ በስደት የሚሄዱ ወጣቶችን ማስቀረት ይቻላል። በጥቅሉ በልማቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ ማስተሳሰር ቢቻል ትውልዱ የራሱን ኑሮ በመለወጥ ጉዳይ ላይ ራሱ እንዲወጣ እድል የሚፈጠር ነው። ይህን ለመጠቀም ግን የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ያስፈልጋል። ከዚህ ባሻገር ቴክኖሎጂም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከሌላው የቀጣናው አገራት አኳያ ሲታይ የውሃ ሀብት እንዳላት ይነገራል፤ ይህን የውሃ ሀብት በአግባቡ ከማስተዳደር አኳያ ምን እየተሰራ ነው? የዘርፉ ምሁራን ኢትዮጵያ ውሃን ማዕከል ያደረገ የውሃ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልጋትም ይናገራሉና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ አበራ፡- ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የውሃ ፖሊስና ስትራቴጂ ሰነድ አላት። ነገር ግን ያ ፖሊሲና ስትራቴጂ አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ መቃኘት አለበት። 40 ሚሊዮን ሕዝብ በነበርን ወቅት የነበረን ፖሊሲና ስትራቴጂ አሁን 120 ሚሊዮን ሕዝብ ሆነንም ተገቢ ሊባል አይችልም። የምናስበው የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓታችን ቀደም ሲል በነበረው መልኩ መሆን የለበትም።
በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ቁጥር ከመጨመሩ በላይ ጠያቂ ትውልድ ተፈጥሯል። የአገራችን የቆዳ ስፋት ግን ያለው ባለበት ቦታ ነው። ባለን የቆዳ ስፋት ላይ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው። ስለዚህ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ከቀን ቀን እየጨመሩ ይመጣሉ። የኢኮኖሚ ጥያቄ ሲባል ደግሞ አንደኛው ምንጩ ውሃ ነው።
ስለዚህ የውሃ አስተዳደር ስርዓታችን በሚገባ መቃኘትና ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ በአግባቡ በፖሊሲ ደረጃ መቀረጽ መቻል አለበት። ያንን ከማድረግ አኳያ በቅርቡ የእኛ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፖሊሲም፣ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፖሊሲም እንዲሁም ኢነርጂ ፖሊሲ ሶስቱም ዘርፎች ፖሊሲያችን ላይ ክለሳ አድርገዋል።
ለምሳሌ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት አሉ። የአዋሽ ተፋሰስ፣ የአባይ ተፋሰስ፣ የስምጥ ሸለቆ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉ። በጽህፈት ቤት ደረጃ እነዚህ ሶስቱ አሉ። ለምሳሌ የአባይ ተፋሰስ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ያለው ባህርዳር ቢሆንም በንዑስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የአሶሳውን ጨምሮ አሉን። ስለዚህ አይናችን ትልቁ ዝሆን ላይ ማተኮር አለበት የሚል እምነት አለን። ለምሳሌ በሰሜን ተከዜ ወንዝ አለ፤ በምዕራብ ደግሞ በለስ ወንዝ አለ። በደቡብ ደግሞ ዋቤ ሸበሌ በሌሎችም እንዲሁ ትልልቅ የሚባሉ ወንዞች አሉ።
የት ቦታ ማድረግ የምንችለው ምንድን ነው? የትኛው ዘርፍ የሚጠበቅበት ምንድን ነው? የሚለውን በጋራ ማየት አለብን። ለምሳሌ ቦረና አካባቢ ለተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለመዝነቡ ሰው ተጎድቷል፤ ከብቶችም አልቀዋል። ከዚህ የተነሳ በኢኮኖሚውም በኩል ብዙ ነገር አጥተናል። በድርቁ ምክንያት የበርካታ ከብቶች ባለቤት የነበረው አርብቶ አደር ከብቶቹን በድርቁ ሳቢያ ተነጥቋል። ይህ አይነት ችግር እንዳይደገም ከአጭር ጊዜ ይልቅ የረጅም ጊዜ እቅዶችን ታሳቢ ያደረጉ የልማት ስትራቴጂዎች መቀረጽ መቻል አለባቸው። ከዚህ የተነሳ የተቀናጀ የልማት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት አለበት። ይህ ሲሆን መሬትና ውሃን አስተሳስረን መያዝ ያስችለናል።
ለምሳሌ ግብርና ሚኒስቴር በሰብል፣ በእንስሳት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ማተኮር ይችላል። የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ደግሞ የሚገነባው ግድቦችን እንዲሁም የመስኖ ካናሎችን ነው። ከዚህ አንጻር ሁለቱ መስሪያ ቤቶች እንዴት ነው ተቀናጅተው እየሰሩ ያሉት? ለምሳሌ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ግድብ ሲገነባ እግረ መንገዱንም ለምን ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚሆን ግድብ አብሮ አይገነባም? ምክንያቱም ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴ በርካታ መዋዕለ ንዋይ ይፈስባቸዋልና መስሪያ ቤቶቹ ለዘርፈ ብዙ ዓላማ መስራት ይኖርባቸዋል ብዬ ስለማምን ነው።
ለምሳሌ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ስንገነባ ታሳቢ ያደረገው ኃይል ለማመንጨት ብቻ አይደለም። ጎን ለጎን ለቱሪዝም አገልግሎት፣ ለዓሳ እርባታ፣ ለመዝናኛነት ብሎም በኢኮሎጂው ላይም የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ሁሉ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው። ፕሮጀክቶች ሲቀረጹ ግራ ቀኙ ታይቶ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያመጣ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ መሆን አለበት። ስለዚህ ከውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት አኳያ በጣም ብዙ የሚቀሩን ስራዎች አሉ።
ለምሳሌ ወንዞቻችንን በተመለከተ እንዲሁም ተፋሰሶችን በተመለከተ ማስተር ፕላን እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን አለን፤ ማስተር ፕላን ያላቸውን መከለስ፤ በትክክል በሚፈለገው መልኩ እንዲሄድ ማድረግ ተገቢ ነው። የሌላቸውን ደግሞ እንዲንዲኖራቸው ማድረግ፤ ያሉንን ዋና ዋና ተፋሰሶችንና ንዑስ ተፋሰሶችን ማስተሳሰር፤ እንዲሁም በዙሪያቸው ያሉት የልማት ፕሮግራሞች ምን እንደሚመስሉ መረዳትም የራሱ የሆነ ፋይዳ አለው። በጥቅሉ የብዝሃ ሴክተር ቅንጅት ስርዓት መዘርጋት መቻል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቂ ዝናብም ሆነ በቂ ውሃ አላት፤ ይህን ውሃ በአግባቡ ይዞ ወደ ምግብ እና ወደ ኢነርጂ ለመቀየር ምን ያህል እየተሰራ ነው?
አቶ አበራ፡– መጀመሪያ ኢነርጂው ላይ ምን ተሰራ? ላልሽው፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ያላት አጠቃላይ የተፈጥሮ ጸጋ ብዙ ነው፤ ጸሐይን ብቻ ብንወስድ ከዚህ አኳያ ብዙ መጠቀም የሚያስችለን ሀብት ነው ማለት ይቻላል። አውሮፓውያኑን ብንወስድ በየጊዜው የበረዶ ግግር የሚያጠቃቸው ናቸው። በእነርሱ አካባቢ ጸሐይ ብርቅ ነው። እንደ እድል ሆኖ ጸሐይ ከወጣ ከወጣችው ጸሐይ ሙቀቷን ለመቋደስ ሰው ሁሉ ጎዳና ወጥቶ ይቆማል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ስንመለከት በጋ ከክረምት ተመጥኖ የተሰጣት አገር ናት ማለት ይቻላል። ከፍተኛ የሆነ እምቅ የጸሐይ ኃይል አቅም ብቻ ሳይሆን የነፋስም የእንፋሎትም ኃይል አለን። የሃይድሮፓወርን እንኳ ሳንጨምር በእነዚህ ታዳሽ ኃይል ብቻ እንኳ መስራት ብንችል ከፍ ያለ ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ትንንሽ ግድቦችን በመገንባትና የጸሐይንና የነፋስ ኃይልንም በመጠቀም 300 እና 400 አባወራዎችን በቀላሉ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ሰፊ ነው። በዚህ ረገድ ያለን ሀብት ገና አልሰራንበትም፤ አልተነካምም።
ያለን የጸሐይ አቅም ሰፊ ሆኖ ሳለ በእስካሁኑ ሒደት ያለን አሸጎዳና አዳማ ላይ ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ያሉ አሉን። ይህም ወደ ሶማሌ፣ አፋርና ድሬዳዋ አካባቢ ሲሆን፣ ይህም ወደማጠናቀቂያው የተቃረበ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አሰላ ግንባታው እየተካሔደ ነው። ነገር ግን ካለን እምቅ ሀብት የተነሳ ይህ በቂ አይደለም። የወደፊቱ የአስር ዓመት የልማት ግባችን ላይ በብዙ የተካተተበት ፕሮግራም ነው። ምክንያቱም ትኩረት አድርገን የምንሰራው በታዳሽ ኃይል ነውና።
አዲስ ዘመን፡- በዝናብ የሚገኘውን ውሃ በአግባቡ ይዞ ከመጠቀም አኳያ የሕዝቡ አረዳድ ምን ላይ ነው ያለው?
አቶ አበራ- የዝናብ ውሃ እንደዘበት በጎርፍ መልክ እብስ እንዲል ከማድረግ ይልቅ ከጣሪያችን የሚፈሰውንም ጭምር ሰብስቦ መጠቀም ወሳኝ ነው። ይህ ሲሆን ውሃን ከብክለትም ከብክነትም መታደግ ይቻለላል። አነስተኛ ግድብ በቤታችን ሊኖረን በሚያስችል መልኩ ብንሰራ እኛም መጠጣት፣ ከብቶቻችንንም ማጠጣት እንዲሁም ለምርታማነት መጠቀም የሚያስችለን ነው። ይህ ብቻ በቂ ነው ማለት ሳይሆን ውሃ በሌለበት ወሳኝ ጊዜ እንድንጠቀም የሚያስችል ይሆናል። በቀጣዩ የዝናብ ወቅት ደግሞ እንዲሁ ውሃ በመያዝ ለሚያስፈልገን ማዋል እንችላለን።
በእርግጥ እንዲህ አይነቱን ስራ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትም ጀምረናል። በዚህ ዓመት ከ120 በላይ ሳይቶች ተመርጠዋል። ቦረና እና ጎንደር ላይ የጀመርን ሲሆን፣ የቴክኖሎጂውን ውጤታማነት ማረጋገጥ ችለናል። በጣም ትርጉም ያለው ስራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቶሎ ወደየስፍራው ለማስገባት እየተሰራ ነው። ይህ ስራ ቀደም ሲል እንደነበረው አይነት የውሃ ማቆር ሳይሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ እና አገልግሎቱም ሰፋ ያለ ነው። በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለሙከራ ብለን የሰራናቸው በአሁኑ ወቅቱ ፋይዳቸው ላቅ ያለ ሆኖ አግኝተነዋል።
በኢነርጂው ዘርፍ ባዮጋዝ ከዚህ ቀደምም የነበረ ነው። ምናልበባት የአቅም ውስንነት ካልገደበን እና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ካለመቻላችን በስተቀር ለዘርፉ የሚሆን ግብዓት አለ። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት የመብራት ታሪፍ በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ ሕዝቡም በዚያው ልክ ሮሮ እያሰማ ይገኛል። በከተማ ከየመጸዳጃ ቤቱ የሚወጡ ፍሳሾች ከገጠር ደግሞ ከየከብቱ የሚገኘው ለበባዮ ጋዝ ትልቅ ግብዓት ነው። የአደጉ አገራት በዚህ ቴክኖሎጂ መጠቀም ከጀመረሩ ዘመናት ተቆጥረዋል። በጥቅሉ ግን በኢነርጂ ዘርፍ የፖሊሲ ለውጥ ከማድረግ ጀምሮ ትልቅ ስራ እየሰራን ነው፤
ይሁንና ፖሊሲ መለወጥ ብቻ በራሱ ውጤት አይደለም። ዋናው ውጤት የሚባለው በዘርፉ ያለውን ኢንቨስትመንት መሬት ላይ ማውረድ ነው። ለምሳሌ ከመንግስታት ጋር የሚደረጉ የልማት ድጋፍና ትብብሮች በእነዚህ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ እንዲያተኮሩ እንፈልጋለን።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም ጭምር ትኩረት የሰጡት የኃይል ዘርፍ ላይ በጣም መስራት አለብን የሚል ነው፤ እሱ ላይ እስካልሰራን ድረስ ከችግራችን ልንላቀቅ አንችልም። የኃይል ዘርፉ ማደግ፣ መለወጥና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እስካልተሰራ ድረስ ኢኮኖሚያችንን በምንፈለገው መልኩ ማሳደግም መለወጥም አንችልም።
በውሃው ዘርፍ ላይም እንዲሁ ነው። በውሃው ዘርፍ ላይ ለምሳሌ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ አለ፤ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ አለ፤ እንደሚታወቀው ደግሞ የውሃ ሀብት አስተዳደር በጣም ሰፊ ነው። የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽንም ጭምር አቅፎ ይይዘዋል። ስለዚህ ሁለቱ ዘርፎች ተናበውና ተቀናጅተው ነው እየሰሩ ያሉት። በአሁኑ ወቅት ፖሊሲያችንን ስንከልስ በዚህ አንግል ነው።
ከዓመታት በፊት አስርና ሃያ ሜትር ድረስ ተቆፍሮ በቀላሉ ውሃ ማግኘት ይቻል ነበር። አሁን አሁን ግን 150 ሜትር ርቀት ላይ ተቆፍሮ ውሃ ማግኘት አይቻልም። ስለዚህ ያለው አማራጭ የገጠር ውሃ አማራጮችን ማየት ነው። በተለይ ወንዞችን መመልከት ያስፈልጋል። በእርግጥ ደግሞ ወንዞችን ሙሉ በሙሉ ገድቦ ከታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ለግጭት ማነሳሳት ተገቢ አይደለም። ነገር ግን በፖሊሲያችን ላይ የተቀመጠው የመጠጥ ውሃ በመጀመሪያ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ እንደሆነ ነው። ከዚህ በዘለለ መስኖው፣ ኢንዱስትሪውና ሌላ ሌላው ይመጣል ማለት ነው። ይሁንና የሚቀረን ብዙ ስራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀጣይ ስራ ምን ላይ ያተኮረ ነው? ከቀጣናው አገራት ጋርስ ያለው ትብብር ምን ይመልሳል?
አቶ አበራ፡- በውሃው ዘርፍ ላይ የውሃ ሀብት አስተዳደርና የውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ አጠቃላይ እንደአገር ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ከሶማሌ እስከ ጋምቤላ፣ ከትግራይ እስከ ቤኒሻንጉል ያለውን ጽንፍ በአግባቡ አጥንቶ እና የሌሎች ሴክተሮችን የውሃ ጥያቄ ለምሳሌ የግብርና ሚኒሰቴር የውሃ ጥያቄ፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የውሃ ጥያቄ እና የሌሎችም የውሃ ጥያቄዎች የሚያቀርቡ ሴክተሮች አሉ፤ ከዛ አኳያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ፖሊሲ ከሌሎች ሴክተሮች ፖሊስ ጋር የተጣጣመና የተናበበ ነው ወይ? በሚል ስራ እየተሰራ ነው።
አንዱ በቅርቡ በእቅድና ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ የሚመራ የ22ቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ የልማት ፖሊሲ የማናበብ (አላይንመንት) ስራ ተሰርቷል። የትኛው ፖሊሲ ከየትኛው ፖሊሲ ጋር ይጣጣማል? ይገናኛል? ወይም ደግሞ ይጣረሳል? የሚለውን የማስታረቅና የማናበብ ስራዎች ተሰርተዋል። ይህ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ፖሊሲና ስትራቴጂ በሌለበት ሌሎች ፕሮግራሞችን ማስፈጸም አይቻልም።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ውሃ እያጠጣች ነው። ይህ የአገራት ትብብርን ምርጫ የሌለው ብቸኛ የጋራ ስራችን ነው ብለን ነው የምናምነው። እኛ ዘንድ ያሉ ውስንነቶችና ችግሮች በተለይ ያልመለስናቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው፤ ነገር ግን የጂቡቲ ሕዝብ ወንድም የሆነ ጎረቤት ሕዝብ ነው። ጂቡቲ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ 28 የውሃ ጉድጓዶች አሏቸው። ከ28ቱ 11ዱ ጉድጓዶች በአሁኑ ወቅት ውሃ ያመርታሉ።
ቀሪዎቹ መጠባበቂያ ናቸው። እያንዳንዳቸው ጉድጓዶች በሜትር ፐርሰከንድ በሊትር ከ40 እና ከ50 በላይ ውሃ ይሰጣሉ። ይህ የከርሰ ምድር ውሃ ነው። ተገቢ ጥናት በጥንቃቄ የተሰራ ስራ ነው። እነርሱ ከ650 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለዚህ ፕሮጀክት ወጪ አውጥተውበታል። ይህ ውሃ በጄኔሬተር እየተገፋ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሄድ ነው። ውሃውን ወደጂቡቲ ለመግፋት በቀን በርካታ ሺ ሊትር ነዳጅ ይጠቀማሉ። ይህ የሚሆነው እስከተወሰነ ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ከተወሰነ በኋላ በራሱ ግፊት የሚሄድ ነው።
ወደ ሌሎቹ ስንመጣ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ከቃሪያና ከሽንኩርት አቅም የሚያስገቡት ከዑጋንዳ ነው። ከዑጋንዳ ለማስገባት ዞሮ የሚገባው በኬንያ በኩል ነው። እኛ ግን ያለነው አፍንጫቸው ስር ነው። ለምንድን ነው ከደቡብ ሱዳን ጋር ፈጣን የሆነ ያጋራ የትብብር ስምምነት ተፈራርመን መሰረተ ልማቶችን ዘርግተን ነዳጃችንን ከደቡብ ሱዳን የማናስገባው? ምክንያቱም 300 እና 400 ኪሎ ሜትር የማይሞላ ርቀት ላይ ነው ያለነው፤ ጨክነን ያንን መዘርጋት ለምን አልቻልንም። በተለይ ደግሞ አጠቃላይ የገቢና ወጪ ምርታችን ጂቡቲ ላይ እንደመሆኑ ምን ያህል ማነቆ ውስጥ እንዳለን እናውቃለን። ያንን ሊተካ የሚችል አማራጭ እድሎችን ሊፈጥሩ የሚችሉ አቅሞች አሉ። ስለዚህ እዛ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል። በመሆኑም የብዝሃ ሴክተሮች ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በደንብ የተናበበ የተሰናሰለ የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ አበራ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015