በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 4 2015 ዓ.ም በመከላከያ ፋውንዴሽን አዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ቀጣና አራት (ሪጅን4) የጎልፍ ስፖርት ቻምፒዮና በስኬት ተጠናቋል፡፡ የኢትዮጵያ ጎልፍ አሶሴሽን ከዝግጅቱና ውድድሩ በርካታ ልምዶች መውሰዱንም ገልጿል፡፡
ቻምፒዮናው በኢትዮጵያ ጎልፍ ስፖርት አሶሴሽን፣ በመከላከያ ፋውንዴሽን እንዲሁም በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት የተካሄደ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ወክሎ በውድድሩ የተሳተፈው ቡድንም ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ተፎካካሪ እንደነበረ ታውቋል። ይህም ቻምፒዮናውን ከማዘጋጀት ከተገኘው ተሞክሮ በተጨማሪ ለኢትዮ ጵያ ጎልፍ ስፖርት ተወዳዳሪዎች ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲኖራቸው ማስቻሉ ተጠቁማል፡፡
ከዚህ ቀደም እንዲዚህ ዓይነት ትልቅ ውድድር አዘጋጅቶ እንደማያውቅ ያስታወሰው አሶሴሽኑ፤ በቀጣናው ከተዘጋጁ ውድድሮች የኢትዮጵያ ከፍተኛ እንደሆነም ገልጿል፡፡ ይህም በትልቅነቱ በቀጣና ደረጃ ከተዘጋጁ ቻምፒዮናዎች ክብረወሰን በመያዝ ኢትዮጵያ የተሻለ አዘጋጅ ሀገር ሆና እንድትመረጥ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡ የአፍሪካ ጎልፍ ኮንፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ የተሳካ የውድድር ዝግጅት አድናቆቱንና ምስጋናውን መግለፁም ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ለውድድሩ ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ተዘጋጅታ ማስተናገዷ ቻምፒዮናው የተዋጣለት እንዲሆን ማድረጉን አሶሴሽኑ ገልጿል፡፡
“ጎልፍ በኢትዮጵያ ይስፋፋል፤ ኢኮኖሚያችንንም ይደግፋል” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው ይህ ቻምፒዮና ዋና ዓላማው ታዋቂ የጎልፍ ተጫዋቾችን በቀጣናው አገራት ማፍራት ነው። የጎልፍ ስፖርትን በመላው ሀገሪቱ በማስፋፋት ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው፡፡
በዘንድሮው ቻምፒዮና በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አራት ስር የሚገኙ ዘጠኝ አገራት ለተሳትፎ ቢጠበቁም 5 ሀገራት ብቻ ውድድሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡ እነዚህም አገራት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ርዋንዳ፣ ታንዛኒያና ዩጋንዳ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ እራሷ ደጋሽ በሆነችበት ውድድር ስኬ ታማ ዝግጅት ብታደርግም በውድድር ተሳትፎ ግን ተወዳዳሪዎች ውጤት ሊቀናቸው አልቻለም። ያም ሆኖ የተገኘው አራ ተኛ ደረጃ አበረታች ነበር። ኢትዮጵያውያን ጎልፍ ተጫዋቾች በዓለም አቀፍ ደረጃ የመወዳደር ልምድ ባይኖራቸውም በችሎ ታቸው እና ለማሸነፍ ያደረጉት ፉክክር ሁሉንም ተሳታፊዎች አስገርመዋል።
የቻምፒዮናው አሸ ናፊ ኬንያ ስትሆን፤ ሁለ ተኛ ዩጋንዳ፣ ሶስተኛ ርዋንዳና አዘጋጇ ሀገር ኢትዮጵያ በአራተኝነት መፈጸም ችላለች። ከዚህም አሶሴሽኑ ብሔራዊ ቡድኑን ለማብቃት ሰፊ ስራ መስራት እንዳለበት ልምድ መወሰዱን ጠቁሟል። ጥሩና ልምድ ያለው ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ብዙ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚኖርበትም አስቀምጧል፡፡
የአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ አሰልጣኝና ተጫዋች አክሊሉ ኃይሌ፣ ብሄራዊ ቡድኑ ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም ጥሩ ዝግጅቶችን ማድረጉን ያስረዳል። ብሔራዊ ቡድንን በመወከል በምስራቅ አፍሪካ መጫወት ከጀመረ አስር አመት እንዳስቆጠረ ገልጾም፤ በዚህም ብዙ ልምድ ማካበት እንደቻለ ተናግሯል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከተወዳዳሪዎቹ ጋር ለመፎካከር ቢሞክርም በልምድ ማጣት ብልጫ እንደተወሰደበት የሚናገረው አክሊሉ ፤ ለዚህም እንደ ምክንያት ሊወሰድ የሚችለው በቂና ደረጃውን የጠበቀ የጎልፍ ሜዳ አለመኖር መሆኑን ጠቁሟል። ኢትዮጵያ ውስጥ የጎልፍ ሜዳ እጥረት በመኖሩ ብሔራዊ ቡድኑ ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ እንዳይሆን ምክንያት ሊሆን ችሏል ሲልም አክሏል።ከሌሎች ሀገራት ጋር ተፎካካሪ ለመሆን ብዙ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል ባይ ነው፡፡ ስፖርቱ እንዲስፋፋ ትኩረት ተሰጥቶ የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች መሰራትና ተተኪዎችን በስፋት ማፍራት ላይ መስራት ያስፈልጋል ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጎልፍ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ሞሲሳ ዝግጅቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የአፍሪካ ቀጣና አራት የጎልፍ ተጫዋቾች ስብስብ ለኢትዮጵያ ጎልፍ እድገትና ለምናፈራቸው ታዳጊ ጎልፍ ተጫዋቾች የቃልኪዳን ማህተም ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ቻምፒናውን ማዘጋጀቷ ለጎልፍ ስፖርት ታላቅ የምስራችና መሰረት እንደሆነም ጠቁመዋል። የውድድሩ ዝግጅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጎልፍ ፍኖተ ካርታ ውስጥ የመካተቷ ማስረጃ እንደሚሆንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በራሱ ሜዳ እንደመጫወቱ ትልቅ እድል የነበረው ቢሆንም፤ የዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ ማጣቱ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ሌሎች ሀገራት በርካታ ውድድሮችን የሚወዳደሩ በመሆናቸው ጥሩ ልምድና የአሸናፊነት ስነልቦና የበላይነት ሊወስዱ ችለዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ብዙ የጎልፍ ተጫዋቾችን ለማፍራት ብዙ ሜዳዎችን ለመገንባት ትኩረት መስጠት እንዳለባት የአፍሪካ ጎልፍ ኮንፌዴሬሽን አስተያየት መስጠቱንም ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2015