ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ለሜቻ ግርማ ከወራት በፊት በፈረንሳይ ሌቪን የቤት ውስጥ ውድድር ያሻሻለው የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረወሰን ፀድቋል። ለሜቻ ለሃያ አምስት ዓመታት ሳይደፈር የቆየውን የርቀቱን የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን በ7:23.81 መስበሩ የሚታወስ ነው፡፡ የቀድሞው ክብረወሰን በኬንያዊው አትሌት ዳንኤል ኮመን እኤአ በ1998 ሃንጋሪ ቡዳቤስት ላይ 7:24.68 ሰዓት የተያዘ ነበር፡፡
በተለያዩ ውድድሮች የሚሰበሩ የዓለም ክብረወሰኖችን እውቅና ለመስጠት ወይም ለማፅደቅ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ ውጤት እስኪረጋገጥ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድበት የዓለም አትሌቲክስም የለሜቻን የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን ከትናንት በስቲያ ማፅደቁን አስታውቋል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ውጤታማ እየሆኑበት በሚገኘው የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር ትልቅ ትኩረት እያገኘ የመጣው ወጣቱ አትሌት ለሜቻ የርቀቱን የዓለም የቤት ውስጥ ክብረወሰን በገባው ቃል መሰረት ባለፈው አርብ በፈረንሳይ ፓሪስ ዳይመንድሊግ ውድድር መስበሩ ይታወቃል። እጅግ ስኬታማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ይህ ድንቅ አትሌት በወራት ልዩነት ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችን በመስበሩም አድናቆት እየጎረፈለት ይገኛል፡፡
ለሜቻ የውድድር ዓመቱ አራተኛ የዳይመንድ ሊግ መዳረሻ በሆነችው ፓሪስ ባለፈው አርብ ያስመዘገበው የዓ ለም ክብረወሰን 7:52.11 ሲሆን ይህም ከቀድሞው ክብረወሰን በ1.52 ሰከንድ የተሻለ ሆናል። የቀድሞው ክብረወሰን በትውልደ ኬንያዊው የካታር አትሌት ሴይፍ ሳኤድ ሻሄን 7፡53፡63 በሆነ ሰዓት እኤአ 2004 ላይ የተመዘገበ ነበር።
በ2019 የዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በርቀቱ ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ውን የብር ሜዳሊያ ያስመ ዘገበው አትሌት ለሜቻ ግርማ ከዚያ በኋላ በተለያዩ መድረኮች ማንፀባረቁና ተጨማሪ ታሪክ መስራቱን ቀጥሏል። በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክም የርቀቱን የብር ሜዳሊያ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበ ሲሆን በተመሳሳይ ባለፈው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም ተመሳሳይ ድል አስመዝግቧል።
ወጣቱ አትሌት በርቀቱ ስኬታማ የሆነው ድንገት በታላላቅ ውድድሮች ብቅ ብሎ ቢሆንም ከዓመት ዓመት ብቃቱን እያሳደገ ዘንድሮ የተለየ አቅም መፍጠር ችሏል።
ይህም ከጥቂት ወራት በኋላ በቡዳፔስት በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከወዲሁ ለወርቅ ሜዳሊያ እንዲታጭ አድርጎታል፡፡
ለሜቻ በፓሪስ የዓለም ክብረወሰን ከማሻሻሉ አስቀድሞ የገባውን ቃል በተግባር ማሳየቱ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር፡፡ እሱም ከድሉ በኋላ ‹‹በውጤቱ ተደስቻለሁ፣ ከሶስት ቀናት አስቀድሞ ክብረወሰኑን እንደማሻሽል ስናገር ነበር፣ ወንድሜ አሰልጣኜም ጭምር ነውና ክብረወሰኑን በእጄ እንደማስገባ ያለውን እምነት ነገረኝ፣ እኔም አምኜው አሳካሁት›› ያለ ሲሆን ዘንድሮ የብቃቱ ጥግ ላይ እንደመገኘቱ ተጨማሪ ታሪኮችን ሊሰራ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡
ለሜቻ ልምምድ ሲያደርግ ጥሩ ስሜትና ጥሩ አቋም ላይ እንደነበር፣ በተጨማሪም በዕለቱ በስታዲየሙ በርካታ ተመልካቾች መመልከቱን ተናግሯል፡፡ ከዚህ ድል በኋላም በዘንድሮ የሃንጋሪያ ዓለም ቻምፒዮና በርቀቱ ለማሸነፍ እንደሚፈልግ አስረድቷል፡፡
የሦስት ሺ ሜትር የቀጥታና የመሰናክል ሩጫ ባለክብረወሰኑ የ22 ዓመቱ ለሜቻ፣ በቀጣይ በግል ውድድሮች፣ በዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በፓሪስ ኦሊምፒክ ከፍተኛ ግምት ካገኙ አትሌቶችም ቀዳሚው ነው፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2015