የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ:: ክለቡ የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮና በመሆን የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆኗል።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ 7ኛ ዓመት የ2015 ዓ.ም የክለቦች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በአዲስ አበባ ትንሿ ስቴድየም በጠንካራ ፉክክሮች ታጅቦ ፍሜውን አግኝቷል:: ሁለተኛ ዙር የእጅ ኳስ የክለቦች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ከ15ኛ እስከ 18ኛ ሳምንት ከግንቦት 26- ሰኔ 3/ 2015 ዓ.ም ጠንካራ ፉክክሮችን ያስተናገደ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ችሏል።
የማጠቃለያ ውድድሩ በአንድ ሳምንት ገደማ ቆይታው ባስተናገዳቸው ውድድሮች የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጠንካራ ፉክክሮች ተስተናግዷል:: የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ያሳዩት ጠንካራ ፉክክር ማን ቻምፒዮን ይሆናል የሚለውን እሰከ ሊጉ ፍጻሜ ድረስ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎት ቆይቷል። ክለቦቹ ያሳዩት የተፎካካሪነት ደረጃ እጅግ ማራኪና አጓጊ ነበር።
ስምንት ክለቦችን ለአንድ ዓመት ሲያፋልም የቆየው የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ መቻል፣ ኦሜድላ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤት፣ ከምባታ ዱራሜ፣ ባህርዳር ከነማ እና ፋሲል ከነማ ጠንካራ ፉክክር አድርገውበታል። በመጨረሻም ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ልምድ ያካበተው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ30 ነጥብ ከማቻል ጋር እኩል ሆኖ በጎል ክፍያ ብቻ በመብለጥ ቻምፒዮንነቱን አረጋግጧል። መቻልን ተከትሎም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ክለብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል::
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ክለብ መቻልን ከመሳሰሉ ጠንካራ ተፎካካሪዎች የገጠመውን እልህ አስጨራሽ ፉክክር በድል በመወጣት የተዘጋጀውን የዋንጫና የወርቅ ሜዳለያ ከክብር እንግዶች ተቀብሏል:: ክለቡ ሊጉን ከተቀላቀለ ስድስት ዓመታትን ብቻ ቢያስቆጥርም ለተከታታይ 4 ጊዜያት ቻምፒዮን በመሆን ትልቅ ታሪክ ጽፏል:: በዘንድሮው ውድድር ዋንጫውን ከፍ ከማድረጉም በተጨማሪ ኮከብ አሰልጣኝና ኮከብ ተጨዋችም ማስመረጥ ችሏል።
የቻምፒዮኑ እጅ ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ አቶ ሙሉጌታ ግርማ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው በመመረጣቸውና ክለባቸው ቻምፒዮን በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀው፣ የክለቡ ስኬት ታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ ጠንካራ ስራ በመስራቱና ተተኪ ስፖርተኞችን በየጊዜው ማፍራት በመቻሉ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ሙልጌታ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለክለቡ የሚያደርጉት ድጋፍ በዋናነት ክለቡን በተከታታይ ዓመታት ቻምፒዮን እንዲሆን እንዳስቻለውም አስረድተዋል። የእጅ ኳስ ክለቡ ተጫዋቾችም ድካማቸው በቻምፒዮንነት መፈፀሙ እንዳስደሰታቸው ገልፀውም በቀጣይ የክፍለ ከተማው አስተዳደር የክለቡን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የክፍለ ከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጠብቀው አመሸ በበኩላቸው፣ የእጅ ኳስ ክለቡ የበለጠ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል እንደ ከዚህ ቀደሙ የበጀት እና ሙያዊ ድጋፍ እንዲሁም መሰረታዊ ነገሮች ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለክለቡ ባስረከቡበት ወቅት፣ ክለቡ ከአገር አልፎ በአፍሪካ ኢትዮጵያን በመወከል እየተወዳደረ ያለ እንደመሆኑ ሊመሰገንና ሊበረታታ እንደሚገባው ተናግረዋል።
የቂርቆስ የእጅ ኳስ ክለብ ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ የእጅ ኳስ ክለቦች ቻምፒዮና ውድድር ላይ በተከታታይ ዓመታት መሳተፍ የቻለ ሲሆን በቅርቡም በግብፅ በተካሄደው የአፍሪካ የእጅ ኳስ ቻምፒዮና ውድድር ላይ ተሳትፎ የሚያበረታታ ውጤት በማስመዝገብ ተመልሷል። የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን ክለብ በአፍሪካ ደረጃ በሚካሄዱት የክለቦች ቻምፒዮና ውድድሮች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ዘንድሮም የሚቀጥል ይሆናል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015