በተለያዩ ዘመናት ከወጡ ከቀድሞ የአዲስ ዘመን ገጾች እየቀነጨብን ለአዲሱ ትውልድ የድሮውን የምናሳይበት፣ ለአንጋፋው ትውልድ ደግሞ የምናስታውስበት አዲስ ዘመን ድሮ ዓምድ ዛሬም የተለያዩ ጉዳዮችን ይዞ ቀርቧል:: ወደ ኋላ በረዥሙ ተጉዞም ከ1950ዎቹና በማስታወስ ማረፊያውን በ2000 ላይ አድርጓል። የንጉሱ ባለቤት እቴጌ መነን ያደረጉት አንድ የሻምፓይን ግብዣ ነበር። ትልቁ የውቅሮ ድልድይ ተሰርቶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ፣ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የቦረና ድርቅ ከዚህ ቀደምም በአንድ ወቅት ተከስቶ የነበረ ስለመሆኑም ይነግረናል። በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ የተጠመደ ፈንጅ ፈንድቶ የንጹሃኑን ሕይወት የቀጠፈበት አሳዛኝ ክስተት፣ ጋንሱ የተሰኘው ታዋቂው የቻይና የሙዚቃ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሚሊኒየሙ ሰሞን ድምቀት ሆኖ አልፏል። የአበበ ቢቂላ በባይሎጂስቶች መመርመር እንዳለበት የወጣ ዘገባም አለ። በተጨማሪ ደግሞ ‘ሰው ምን ይላል?’ ከሚለው ገጽ ላይ ለቅምሻ ያህል ተካቶ ቀርቧል::
የተደረገ የሻምፓይን ግብዣ
ስለ ልዕልትነታቸው በደህና መገላገል በእዚሁ ቀን ከጠዋቱ በአንድ ሰዓት ተኩል ላይ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል። ግርማዊት እተጌ መነን ስለ ልዕልት መድፈሪያሽ ወርቅ አበበ በደህና ሴት ልጅ መገላገል፣ ግንቦት አራት ቀን ትናንት ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ በገነተ ልዑል ቤተመንግሥት ለልዑላት ንጉሣውያን ቤተሰብና ደስታቸውን ለመግለጥ ለሄዱት ክቡራን ሚኒስትሮችና መኳንንት፣ ክቡራት፣ ወይዛዝርት የሻምፓይን ግብዣ አድርገዋል:: (አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 1951 ዓ.ም)
የውቅሮ ድልድይ ተሠርቶ ለተሽከርካሪ ተከፈተ
ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ መንገድ በ816 ኪሎ ሜትር በውቅሮ ከተማ የሚገኘው ትልቅ ድልድይ ባለፈው ጥቅምት 29 ቀን 1958 ዓ/ም ውሃ ሰርስሮ የድልድዩን መሠረት ለሁለት ስለከፈለው በጠቅላይ ግዛት የአውራ ጎዳና ሠራተኞች ችሎታ በደንብ ስለተሠራ የፈረሰው ድልድይ ከሠባት ወር በኋላ ተሽከርካሪዎች ሊተላለፉበት ችለዋል። (አዲስ ዘመን ታህሳስ 9 ቀን 1958 ዓ.ም)
በቦረና ዞን በእንስሳት ላይ የተከሰተውን የውሃና መኖ እጥረት ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ (ዋኢማ)፤-በእንስሳት ላይ የተከሰተውን የውሃና መኖ እጥረት ለማስወገድ የውሃና ሳር አቅርቦት እያከናወነ መሆኑን የኦሮሚያ አደጋ መከላከል ዝግጅትና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ::
…………..
ረዘም ያለ መንገድ መሄድ የሚችሉትን የቤት እንስሳት ከአከባቢው ማንቀሳቀስ መቻሉን ጠቁመው፣ ለጥጆችና ላሞች ባሉበት የውሃና ሳር አቅርቦት እየተደረገ ነው:: (አዲስ ዘመን ታህሳስ 7 ቀን 2000 ዓ.ም)
በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ላይ የተጠመደ ፈንጅ ፈንድቶ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ደረሰ
አዲስ አበባ-(ኢዜአ)፡-ከሁመራ መናኸሪያ ወደ ሽሬ ከተማ በመጓዝ ላይ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በሻዕቢያና ተላላኪዎቹ የተጠመደ ፈንጅ ከትላንት በስቲያ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ ፈንድቶ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሁመራ ዞን ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ::
ጽህፈት ቤቱ እንደገለጸው፣ በፈንጂው ጥቃት 8 ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ በ27 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሷል።
የኤርትራ ወጣቶችና ወታደሮች በብዛት እየከዱ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ያሳሰበው ሻዕቢያ በተደጋጋሚ ጊዜ በእራሱና በተላላኪዎቹ አማካኝነት በሁመራ አካባቢ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ሥፍራዎች የሽብር ጥቃት ሲሞክር መቆየቱን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። (አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2000 ዓ.ም)
ታዋቂው የቻይና ጋንሱ ሙዚቃ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ተገለጸ
አዲስ አበባ፡- ታዋቂው የቻይና ጋንሱ የሙዚቃ ቡድን አዲሱን ሚሊኒየም ምክንያት በማድረግ ከመጋቢት 11 እስከ መጋቢት 14 በአዲስ አበባና በመቀሌ የተለያዩ ዝግጅቶችን ያቀርባል::
የሙዚቃ ቡድኑ በኢትዮጵያ ተገኝቶ ትርዒቱን ማቅረቡ ሚሊኒየሙ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ መላው ዓለም የሚያከብረው መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ጠቁመዋል:: (አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2000 ዓ.ም)
የአበበ ቢቂላ ሰውነት በባይሎጂስቶች ይመረመራል
የሰውን ሕዋሳት የሚመረምሩ ሳይንቲስቶች የሁለት ጊዜ የማራቶን ባለድል የሆነው የአበበ ቢቂላን ሰውነት ለመመርመር አስበዋል:: ዶክተር ኢቢዎርዚግተን የዓለም የባይሎጂ ምርምር ዳይሬክተር የሆኑት የመቶ አለቃ አበበ ቢቂላ ሰውነት ለምርምር ቢቀርብ ማራቶን በቀላሉ እንዴት ለማሸነፍ እንደሚቻል ይታወቅ ነበር ብለዋል::
አበበ ቢቂላ ሁለት ጊዜ የማራቶን ባለድል የሆነበት ምክንያት፣ የሚኖርበት አካባቢ ደጋማ ስፍራ ስለሆነ ሰውነቱ ኦክስጂን የተባለውን አየር እንደልቡ ስላገኘ ነው ሲሉ ዶክተሩ አስረድተዋል::
ጤናማ አየርና ጤና ሰውነት ሲገናኙ ኃይልን ለማስገኘት እንደሚችሉ ተናግሮአል:: (አዲስ ዘመን ህዳር 20 ቀን 1958 ዓ.ም)
ሰው ምን ይላል?
ሴቶች ከሁሉም አብልጠው የሚጠብቁት ሚስጥር ምንድነው?
….ዕድሜያቸው…..
አንድ ሺህ ሰዎች ራቁታቸውን ከፊትህ ቆመዋል። 500 ሴቶችና 500 ወንዶች ሆነው አዳምና ሔዋን ከመካከላቸው ቢኖሩ ሁለቱን እንዴት ትለያቸዋለህ?
……..አዳምና ሔዋን ከሴት ማኅፀን ስላልወጡ እምብርት የላቸውም…..
ዘማች መምህር
ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ
አዲስ አበባ ነፍሳቸውን ይማርና አለቃ ገብርሃና የታወቁ ቀልደኛ ነበሩ ይባላል። እውነት ነው እንዴ? ከጨዋታቸው አንዱን ቢገልጡልኝ ‘የምታውቁት ነገር እንዳለ ‘ እያሉ ከሚጽፉት ታሪክ ውስጥ ይህም ለእኔ አንዱ ስለሆነ ደስ ይለኝ ነበር።
ወንድሙ እርገጤ (ከአርባ ምንጭ)
-ስለ አለቃ እኛም ሲሉ ሰማን እንጂ በርግጥ ቀልደኛ ናቸው ብለን አናረጋግጥሎትም። የጥንቱን የሌሎችን ቀልድ በአለቃ ላይ አድርገውታል። የአለቃን ቀልድ እስትናገኝ ቀጠሮ ብንጠይቆት እናስከፋዎት ይሆን?
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2015