ለ2024ቱ የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋቸው አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) የምድባቸውን አምስተኛ የማጣሪያ ጨዋታ የፊታችን ሰኔ 13 ያደርጋሉ:: ለዚህም ጨዋታ ዝግጅት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጓል:: የዋልያዎቹ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም ጥሪ ያደረጉላቸው ተጫዋቾች ከትላንት ጀምሮ ሪፖርት በማድረግ ዝግጅት እንደጀመሩም አሳውቀዋል::
በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምስተኛ የምድብ ጨዋታውን ከማላዊ አቻው ጋር ያደርጋል:: ይህን የማጣሪያ ጨዋታ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑን ዋና አሰልጣኝነት ቦታ የተረከቡት ኢንስትራክተር ዳንኤል የሚመሩ ይሆናል::
በ12 ምድቦች ተከፍሎ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምድብ አራት ከጊኒ፣ ማላዊና ግብፅ ጋር መደልደላ ይታወቃል:: እስካሁን አዘጋጇን ኮትዲቯርን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል:: ሌሎች የተቀሩት ኃላፊ ሀገራት በቀሩት ሁለት ምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚለዩም ይሆናል:: ኢትዮጵያም የማለፍ ዕድሏ አጣብቂኝ ውስጥ ቢገባም የማጣሪያ ጨዋታዋን ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር ታደርጋለች::
ኢትዮጵያ በምድቡ ካደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለችው አንዱን ሲሆን በሶስቱ ትሸንፋለች:: ብቸኛውን ድሏንም መቀዳጀት የቻለችው የመድረኩን የ7 ጊዜ አሸናፊ ግብጽን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 2ለ0 በሆነ ውጤት በመርታት ነበር:: ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ በማላዊ በጠባብ ውጤት ብትሸነፍም በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ግብፅን በመርታቷ የማለፍ ተስፋዋን አለምልማ የምድቡ መሪ እስከ መሆን ደርሳ ነበር:: በተከታታይ ከጊኒ ጋር ያደረገቻቸውን የምድቡን ሶስተኛና አራተኛ ጨዋታዎች በመሸነፏ ግን የማለፍ እድሏ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተል:: ይህም በምድቡ አምስተኛ ጨዋታ ብዙ ተስፋ እንዳይደረግ አድርጓል:: ኢትዮጵያ በነዚህ ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቿ መረብ ላይ 5 ጎሎችን አስቆጥራ 7 ጎሎች ተቆጥሮባታል:: በዚህም መሰረት በ3 ነጥብና በ2 የግብ እዳ የምድቡ ግርጌ ላይ ተቀምጣለች::
ኢትዮጵያ የምድብ አምስተኛ ጨዋታዋን ሰኔ 13 ከማላዊ ጋር በገለልተኛ ታደርጋለች:: ምድቡን አንደኛና ሁለተኛ ሆኖ በመምራት ላይ የሚገኙት ግብፅና ጊኒ እንዲሁ እርስ በእርሳቸው ይገናኛሉ:: ሁለቱ አገራት ምድቡን በእኩል ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው እየመሩ ሲሆን በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን የሚጨርሱ ከሆነ አንድ ጨዋታ እየቀራቸው ከምድቡ ተያይዘው የሚያልፉ ይሆናል:: የኢትዮጵያም የማለፍ ተስፋ በጣም ጥቂት ሲሆን ከሁለቱ አንዳቸው ሁለት ጨዋታ መሸነፍ እና ኢትዮጵያ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎቿን በሰፊ ውጤቶች ማሸነፍ የግዴታ ይሆናል::
ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ውስጥ አንድም የካፍ ደረጃን የሚያሟላ ስቴድየም ባለመኖሩ ሶስቱን የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎቿን በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር እያደረገች እንደሆነ ይታወቃል:: አምስተኛውም የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ እንዲሁ በሌላ ሀገር ስቴድም ይካሄዳል:: ለጨዋታውም ዝግጅት እንዲረዳ 7 አዳዲስ ተጫዋቾችን በማካተት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጓል:: የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህርዳር ከነማ እያንዳንዳቸው አምስት አምስት ተጫዋቾችን አስመርጠዋል::
ብሔራዊ ቡድኑ ሶስት ግብ ጠባቂዎችን በማካተት (ሰይድ ሀብታሙ ከባህርዳር ከተማ፣ ባህሩ ነጋሽ ከቅዱስ ጊዮርጊስና ቢኒያም ገነቱ ከወላይታ ድቻ) መርጧል:: የተከላካይ ክፍሉ ደግሞ ስምንት ተከላካዮችን (ዓለም ብርሃን ይግዛው፣ ሄኖክ አዱኛ፣ ረመዳን ሱፍ፣ ፍራኦል መንግስቱ፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ አስቻለው ታመነ፣ አማኑኤል ተረፈንና ያሬድ ባዬን) አካቷል:: በአማካይ ክፍሉ 7 ተጫዋቾች የተካተቱ ሲሆን (አለልኝ አዘነ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አበባው ሀጂሶ፣ ከነአን ማርክነ፣ ቢኒያም በላይ እና ወገኔ ገዛኸኝ) መካተታቸው ታውቋል:: የአጥቂ ስፍራ ለአምስት ተጫዋቾችን ጥሪ የተደረገ ሲሆን ዮሴፍ ታረቀኝ፣ ብሩክ ሙሉጌታ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ ሀብታሙ ታደሰን አቤሎ ማሙሽ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ናቸው::
ዋልያዎቹ ዝግጅታቸውን በአዳማ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን ጊዜያዊ አሰልጣኙ ኢንስትራክተር ዳንኤል የሚመሩት ቡድን በረዳት አሰልጣኝነት የባህርዳር ከነማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው፣ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝን አካቷል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2015