ወቅቱ የህዝቡን ችግር መፍታት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችና የፈጠራ ሀሳቦች እየወጡ ያሉበት ነው:: ችግሮችን መነሻ በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል በሚደረገው አገራዊ ጥረት አገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅመው ፈጠራዎችና የፈጠራ ሀሳቦችን ለሚያቀርቡ የፈጠራ ባለሙያዎች እውቅና መስጠት፣ መደገፍና ማበረታታት አስፈላጊና ወሳኝ ነው::
በቅርቡም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀው 3ኛው የክህሎት ውድድር ለዚህ አንድ ማሳያ ነው:: ‹‹የክህሎት ልማት ከሥልጠና በላይ ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው 3ኛው የክህሎት ውድድር በርካታ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶች ለእይታ ቀርበውበታል:: ይህም አገር በቀል እውቀቶች፣ የፈጠራ ሀሳቦችና የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን በማበረታታት ረገድ አበረታች ጅምር ነው::
በክህሎት፣ በቴክኖሎጂና በተግባራዊ ጥናትና ምርምር ዘርፍ በተካሄዱ ውድድሮችም ከሶስት መቶ በላይ ሰልጣኞች፣ አሰልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች ተሳትፈዋል:: 113 የሚደርሱ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ ቀርበው በብዙ ሺ በሚቆጠሩ ሰዎች መጎብኘታቸውንም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል::
በክህሎት ውድድሩ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች ያላቸውን ፈጠራና ሀሳብ ለእይታ አቅርበዋል:: ለውድድር ይዘዋቸው ከቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች መካከልም ጥቂቶቹን በመዳሰስ ከፈጠራ ባለሞያዎቹ ጋር ቆይታ አድርገናል::
የድሬዳዋ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህር ዮናስ ጥዑም ‹‹ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎላ/Prosopis juliflora ››/ በተለምዶ ‹‹የፈረንጅ ብስኩት›› የተሰኘውን የአረም አይነት ለማጥፋት የሚያስችል የፈጠራ ቴክኖሎጂን ይዘው ቀርበዋል:: ይህ የአረም አይነት በአፋርና በሱማሌ ክልል በስፋት የሚገኝ ሲሆን፤ ልክ እንደ ዛፍ አይነት ነው:: አረሙ የከርሰ ምድርን ውሃ በስፋት ይመጣል፤ እሱ ባለበት አካባቢ ሌላ ተክል አይበቅልም፤ ሰፊ የእርሻ ቦታዎችን የሚይዝ ነው ሲሉ ይናገራሉ::
ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ አረሙን ወደ ተለያዩ ነገሮች በመቀየር መልሶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ማድረግ የሚያስችል ነው የሚሉት መምህር ዮናስ፤ የፈጠራ ቴክኖሎጂው ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ መስራት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤት እንደሆነም ይገልጻሉ:: እሳቸው እንዳሉት፤ አዲሱ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ማሽን ኦክስፋም (OXFAM) ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባባር የተሠራ ሲሆን፤ ለህብረተሰቡ ተላልፎ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል::
አረሙን ፍሬ ከብቶች ይመገቡታል:: ፍሬው በጣም ጠንካራ ስለሆነ ከብቶች ከበሉት በኋላ በሆዳቸው ውስጥ ስለማይፈጭ ተመልሶ በእበት/ እዳሪ/ መልኩ ይወገዳል:: ይህ ከከብቶቹ የተወገደው የአረም ፍሬ የከብቶቹ እበት እንደ ማዳበሪያ ስለሚሆንለት በደንብ እንዲበቅልና እንዲስፋፋ ያደርገዋል:: በአፋር ክልል በአረሙ ላይ የተካሄደው ጥናት እንደሚያመላክተው፤ አረሙ በዓመት ከ20 ሺ እስከ 50 ሺ ሄክታር ስፋት ያለውን መሬት የማዳረስ አቅም አለው::
በፈጠራ የተገኘው ማሽን ደግሞ አረሙን በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ አረሙ እንዲጠፋ የሚያስችል መሆኑን የጠቀሱት መምህር ዮናስ፣ አረም የሆነው ዛፍ ከተቆረጠ በኋላ የሚጣል ምንም የሚጣል ነገር እንደሌለም ይናገራሉ::
ከዚህ የፈጠራ ማሽን አንዱ ማሽን ከሰሉን የሚፈጭ ሲሆን ሌላው ደግሞ ዘሩን የሚያመክን መሆኑን ይገልጻሉ:: የፈጠራ ማሽኑ አንደኛው ክፍል የአረሙን ግንድ ያከስላል፤ ከሰሉ ደግሞ ወደ ወፍጮ ማሽን እንዲገባ በማድረግ ይፈጫል:: ሁለተኛው የማሽን ክፍል ዘሩ ወይም ፍሬውን መፍጨት ያስችላል:: በማሽኑ የተፈጨውን ከሰል ከማጣበቂያ ጋር በመቀላቀል እንደ ብሪኬት አይነት አራት ማዕዘን ከሰል የሚያመርት ነው:: ይህ በተለምዶ ከምናውቀው የከሰል የጊዜ ቆይታ ይልቅ ብዙ ሰዓት መቆየት የሚችል ነው:: እንደ ባዮ ጋዝ ያለው የካርበን መጠን አነስተኛ ሲሆን፤ እሳቱም ልክ እንደባዮ ጋዝ አይነት እንደሆነ ይናገራሉ::
ሌላኛው በማሽኑ የሚመረተው መኖው ነው፤ ማሽኑ ፍሬውን በመፍጨት ብቻውን ወይም ከበቆሎ ጋር በማደባለቅ ለከብቶች መኖነት እንዲውል ማድረግ የሚያስችል ነው:: ከአረሙ የሚዘጋጀው ይህ መኖ የወተት ምርት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያስችላል ያሉት መምህር ዮናስ፤ መኖውን ብቻ አልያም ከበቆሎ ጋር ቀላቅሎ በመፍጨት ማቅረብ ይችላል ይላሉ:: አረሙ ብዙ ያልታየና ገና ያልተነካ በመሆኑ ቴክኖሎጂው ሲስፋፋ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ያስችላል ሲሉም ነው ያብራሩት::
እሳቸው እንደሚሉት፤ የአረሙ ዘር ስለመከነና ስለተፈጨ ከብቶች በመኖነት ሲመገቡት ምንም አይነት ጉዳት አያስከትልም:: መኖውን ከብቶቹ ሲመገቡት ከፍተኛ የወተት መጠን ማግኘት ይቻላል:: ይህም በአለማያ ዩኒቨርሲቲ በጥናት የተረጋገጠ ስለመሆኑ መምህር ዮናስ ተናግረዋል::
ይህ የፈጠራ ውጤት ሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ማርማርሳ ቀበሌ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የቀረበ ሲሆን፤ 20 ለሚደርሱ ዜጎችም የሥራ እድል ፈጠሯል:: የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከልም ስድስቱ ሴቶች ናቸው፤ ስለቴክኖሎጂው አጠቃቀም ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል::
ከዚህ በፊት አረሙን ዛፍ ቆርጦ ለማጥፋት ብዙ ሙከራ ቢደረግም፣ ዘሩ በጣም ጠንካራና ቶሎ የማይፈጭ በመሆኑ ማጥፋት ሳይቻል መቅረቱን ያነሱት መምህር ዮናስ፤ አሁን ላይ የተሰራው የፈጠራ ቴክኖሎጂ አረሙን መፍጭት የሚችል ነው ብለዋል:: ማሽኑ የአረሙን ዛፍ የተለያዩ አገልግሎቶች መስጠት እንዲችል አድርጎ በመጠቀም በአንዱ ማሽን ማቴሪያሎችን ብቻ በመቀያየር ሁለት ነገሮችን መፍጨት ይቻላል:: በአንድ ጊዜ እስከ አራት ሜትር ኪዮብ ወይም 1332 ኪሎ ግራም የሚፈጭ ሲሆን፤ ቴክኖሎጂው በኤሌክትሪክም በሶላር የሚሰራ ነው::
አረሙ በስፋት የሚገኙባቸው የሶማሌና አፋር ክልል አካባቢዎች ይሁኑ እንጂ በሌሎች ክልሎችም አለ:: ዛፉ እስከ 15 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን እሾኩ ደግሞ ከሶስት እስከ አምስት ሳ.ሜ የሚረዝምና መርዛማ ነው:: ስሩም ከሶስት እስከ አምስት ሜትር ድረስ ጥልቀት አለው::
‹‹ይህንን ቴክኖሎጂ ለመስራት በተለይም ዘሩን (ፍሬውን) የሚፈጨውን ማሽን ለማግኘት ብዙ ሙከራዎች አድርገናል›› የሚሉት አሰልጣኙ፤ በውጤቱም ዘሩን ማምከን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማግኘት ችለናል ነው ያሉት:: አሁን ላይ ከአውሮፓ ህብረት የመጡ አካላት ቴክኖሎጂውን አይተው አስፋፍተው ለመስራት እንዲያስችል ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመሳተፍ እየሰሩበት ይገኛሉ::
ቴክኖሎጂውን ከቴክኒክና ሙያ ባሻገር በኢንተርፕራይዞችም ሆነ በሌሎች አካላት መስፋፋትና ወደ ተጠቃሚው ማድረስ ያስፈልጋል የሚሉት መምህሩ፤ ቴክኖሎጂው ችግር ፈቺና የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ወስዶ ሊጠቀምበት ይችላል ብለዋል::
የአረሙ ተክል ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ የታወቀው በ1980ዎቹ እንደሆነ የሚናገሩት አሰልጣኙ፤ በግብጽ፣ በዩጋንዳና በሌሎቹም አገራት ላይ መኖሩን ጠቅሰዋል:: ‹‹እኛ እንዳየነው አፍሪካ አገራት የከሰል ፕሪኬቱን ለማምረት የሚጠቀሙት በእጅ ነው፤ እኛ ግን ይዘን የቀረብነው ቴክኖሎጂ ቢስፋፋ በአፍሪካ አገራት ላይ ኤክስፖርት ማድረግ እንችላለን›› በማለት ቴክኖሎጂው ከአገር ውስጥ ባለፈ በውጭ አገር ተፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል::
ሌላኛው በክህሎት ውድድሩ ሥራቸውን ይዘው የቀረቡት አሰልጣኝ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሻሻመኔ ክላስተር የመጡት አሰልጣኝ መሐመድ ሙዴ ናቸው:: አሰልጣኝ መሐመድ፤ ገብስ መፈተጊያ ማሽን (barley grinding machine) በመባል ስያሜ የተሰጠውን የፈጠራ ቴክኖሎጂ ይዘው ነው የቀረቡት::
እሳቸው እንደሚሉት፤ እንደሚታወቀ በአገራችን በተለይ ገብስ አብቃይ በሆኑት አካባቢዎች ያሉ እናቶች ወይም ሴቶች ገብስ ለመፈተግ የሚጠቀሙት ሙቀጫ ነው፤ አንድ ኪሎ ገብስ ለመፈተግ 20 ደቂቃዎች የሚወስድባቸው በመሆኑ ጊዜያቸው በከንቱ ሲባክን እንዲሁም ገብሱን ለመፈተግ የሚያወጡት ጉልበት ከፍተኛ በመሆኑ ለጉዳት ሲዳረጉ ኖረዋል:: አሁን ላይ በኮሌጁ የተሠራው የፈጠራ ቴክኖሎጂ የእናቶች ወይም የሴቶችን ድካም ከመቀነስ ባለፈ ጊዜን የሚቆጥብ ሲሆን፤ በ20 ደቂቃ ውስጥ አንድ ኩንታል ገብስ መፈተግ የሚያስችልም ነው::
ቴክኖሎጂው በተለይ ገብስ በብዛት በሚመረትበት አካባቢ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው የሚሉት አሰልጣኝ መሐመድ፤ ‹‹በእኛ አካባቢ ከገብስ ብዙ የምግብ አይነቶች እንደ ቆሎ፣ ቅንጬና የመሳሰሉትን ለማዘጋጀት በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑ አበርክቶው የጎላ ነው›› ይላሉ:: በገጠር አካባቢ ያሉ እናቶችና ሴቶችም ከገብስ ምግቦችም ለማዘጋጀት ገብስ ለመፈተግ የሚያወጡት ጉልበትና ድካም ይህንን ቴክኖሎጂ ለመሥራት ምክንያት መሆኑንም ገልጸዋል:: ‹‹እኛ የእናቶቻችንና የእህቶቻችንን ድካም መቀነስ የሚያስችል ፈጠራን በመስራት የመፍትሔው አካል መሆን እንችላለን በሚል ሀሳብ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችለንን ሥራ ነው የሰራነው ›› በማለት የቴክኖሎጂውን አስፈላጊነት አሰልጣኝ መሐመድ አስረድተዋል::
አሁን ላይ የፈጠራ ሥራው ለህብረተሰቡ ተላልፎ በሻሸመኔ አካባቢ ያሉ ወረዳዎች እየተጠቀሙበት ነው የሚሉት አሰልጣኝ መሐመድ፤ ሁሉም ጋ ባይደርስም አንዱ ከአንዱ እየሰማ ማሽኑን በመግዛት እየተጠቀመ እንደሆነም ጠቁመዋል::
በአካባቢው አንዳንዶች ገብስ ለመፈተግ ማሽን ይጠቀሙ እንደነበርም ጠቅሰው፣ ይህም በውጭ ምንዛሪ በውድ ዋጋ የሚገዛ እንደሆነ ነው የገለጹት:: በአማካኝ እስከ ሁለት መቶ ሺ ብር ድረስ ወጪን እንደሚጠይቅ ይናገራሉ::
አዲሱ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ዋጋ ተተምኖለት በ35ሺ ብር ለህብረተሰቡ መቅረቡን ገልጸው፣ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ዋጋው እጅግ ተመጣጠኝ እንደሆነ ይናገራሉ:: ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ከውጭ ከሚመጣው ቴክኖሎጂ የተቀዳ (ኮፒ) መሆኑንም ጠቅሰው፣ በአገር ውስጥ ግብዓች የተሠራ ነው ብለዋል::
አሁን ላይ ከተሜውም ቢሆን ገብስ በወፍጮ ቤት ለማስፈተግ የሚያወጣው ወጪ ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉት አሰልጣኝ መሐመድ፤ በወፍጮ ቤት አንድ ኪሎ ገብስ ለመፈተግ ከሰባት ብር በላይ እንደሚጠየቅም ይገልጻሉ:: ማህበረሰቡ ማሽኑን በግልም ሆነ በጋራ እየገዛ እየተገለገለበት መሆኑን ተናግረዋል፤ ማሽኑ ረጅም ጊዜ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸው፣ ህብረተሰቡ በሚፈልገው መጠንና ሁኔታ አሻሽሎ መስራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል::
‹‹እኛ እንደ ኮሌጅ ይህንን ሥራ ካቀረብን ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ህብረተሰቡ በሚፈልገው ልክ እያበዙ ለህብረተሰቡ መሸጥ ይችላሉ ›› የሚሉት አሰልጣኝ መሐመድ፤ ማሽኑ በማንዋል (በእጅ) ና በኤሌክትሪክ የሚሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፤ በሁሉም አካባቢ የሚገኝ ህብረተሰብ እንደፈለገው ሊጠቀምበት እንደሚችል ነው የገለጹት::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ይህ ማሽን ህብረተሰቡ ዘንድ ደርሶ ተጠቅሞበት ድካም ሊቀንስ የቻለ በመሆኑ እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት ይኖርባቸዋል:: ስለዚህ የኮሌጁ የፈጠራ ውጤት የሆነውን ቴክኖሎጂ በሁሉም አካባቢዎች እንዲስፋፋ ለማድረግ ከሚመለከተው አካል ሁሉ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል::
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው 3ኛው የክህሎት ውድድር አዳዲስ፣ ችግር ፈቺና እሴት ጨማሪ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ የበቁበትና የክህሎት ውድድርን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ከፍተኛ ፉክክር የተስተናገደበት መሆኑን አስታውቀዋል::
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሥልጠና ተቋማት ብቻ እንዳልሆኑም ጠቅሰው፣ የማምረቻ ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል:: ተቋማቱ ከኢንዱስትሪና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር እንዲተሳሰሩ የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል:: በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተመረቱ ተቀራራቢ ቴክኖሎጂዎች ተሰባስበው የሚጎለብቱበትና የተመረጡ ቴክኖሎጂዎች በስፋት የሚባዙበት የክረምት መርሃ ግብር በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንም ጠቁመዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2015