የኢትዮጵያ ብስክሌት ቻምፒዮና በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ የውድድር መርሃ ግብሮች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ብስክሌት ቻምፒዮና ነው፡፡ ይህ ውድድር ዘንድሮ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ የብስክሌት ማህበር የተመዘገበም ነው። ቻምፒዮናው እንደሁልጊዜውም ብሄራዊ ቡድኑን የሚወክሉ ብስክሌተኞች የሚመረጡበት እንደሆነም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ውድድሩ ምንም እንኳን ዓመታዊ ቻምፒዮና ቢሆንም በክልሉ በጦርነት ምክንያት የተጎዳውንና ተቀዛቅዞ የሚገኘውን የብስክሌት ስፖርት ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴው እንዲመለስ እና እንዲነቃቃ ታስቦ የሚደረግም ነው፡፡
ፌዴሬሽኑ ቻምፒዮናውን ለማካሄድ ዝግጅቱን ከትግራይ ክልል ብስክሌት ፌዴሬሽን ጋር እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድሉ ለሁሉም ክልሎች የተሰጠና ክልሎችም የማዘጋጀት ፍላጎት ቢኖራቸውም ካለው ሁኔታ አንጻር እድሉ ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ክልሉ ውድድሩን ለማካሄድ በጸጥታው ረገድ ኃላፊነት የወሰደ ሲሆን፤ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝና በሰላም እንዲጠናቀቅም አረጋግጧል፡፡
ቻምፒዮናው ከሰኔ 14-18 2015 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከተለያዩ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ክለቦች በሁለቱም ጾታ ከ170 እስከ 200 ብስክሌተኞች የሚሳተፉም ይሆናል፡፡ በሶስት የእድሜ እርከኖች ተከፍሎ ሁለት ዓይነት ውድድሮችም ይስተናገዱበታል፡፡ አንደኛው የውድድር ዓይነት የግል ሰዓት ሙከራ፤ ሁለተኛው ደግሞ የጎዳና ውድድር ነው፡፡ የዕድሜ እርከኖቹም አዋቂ፣ ወጣት እና ከ23 ዓመት በታች በሚል ተከፋፍሏል። በግል የሰዓት ሙከራ ተወዳዳሪዎች በየ ሁለት ደቂቃ ልዩነት የሚለቀቁ ሲሆን፤ ብቻቸውን እየጋለቡ በምን ያህል ሰዓት እንደሚጨርሱ ሙከራ ይደረጋል፡፡
በአዋቂ ወንዶች የግል ሰዓት ሙከራ 30 ኪሎ ሜትር ሲሆን፤ የወጣት ወንዶች የግል ሰዓት ሙከራ ደግሞ 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ይሆናል። በአዋቂ ወንዶች ምድብ የጎዳና ውድድር 120 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች 100 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ በአዋቂ ሴቶች ምድብ የጎዳና ውድድር 80 ኪሎ ሜትር፤ የግል ሰዓት ሙከራ ደግሞ 20 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ በሴት ወጣቶች ምድብ የጎዳና ውድድር 60 ኪሎ ሜትር ሲሆን የግል ሰዓት ሙከራም 10 ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ርቀቱ እንደ አስፈላጊነቱ ሊጨምር አሊያም ሊቀንስ ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም ሞላ፤ የክልሉ ብስክሌት ፌዴሬሽንም ሆነ ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስፖርቱ ካበረከቱት አስተዋጽኦና በተለያየ ጊዜ ብሄራዊ ቡድኑን በመወከላቸው በትግራይ መቐለ ከተማ ለማካሄድ በስራ አስፈጻሚ መወሰኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም መሰረት ከክልሉ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጋር ንግግር ከተደረገ በኋላ ለማዘጋጀት ኃላፊነት ሊወስዱ ችለዋል፡፡ ቻምፒዮናው በትግራይ ክልል መካሄዱ ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን፤ የተሻለ የብስክሌት እንቅስቃሴ ሲደረግበት የነበረ እንደመሆኑ ለብስክሌት ስፖርት እድገት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ማድረግ ችሏል፡፡
‹‹ብስክሌት በትግራይ ባህል ነው›› የሚሉት ኃላፊው ‹‹በሁለት ዓመቱ ጦርነት ብስክሌት ስፖርት ተጎድቷል። በክልሉ እንዲካሄድ የተወሰነውም ይሄንን ለማነቃቃት ነው፡፡ ውድድሩ ሲካሄድ በክልሉ ያሉ ክለቦችና ፌዴሬሽኑ ተነቃቅተው ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ታስቦ እንዲዘጋጅ ተወስኗል፡፡ በክልሉ ስፖርቱ ከፍተኛ ተወደጅነት ስላለው ጥሩ ዝግጅት እንደሚኖር እምነቴ ነው›› ብለዋል፡፡
በውድድሩ የሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎችም ውጤታቸው በዓለም አቀፉ የብስክሌት ማህበር ድረ ገጽ ላይ የሚለጠፍ ይሆናል፡፡ የብስክሌት ስፖርት በባህሪው የድምር ውጤት በመሆኑ ለኦሊምፒክ፣ ዓለም ቻምፒና እና አፍሪካ ቻምፒዮና ለመሳተፍ ከሚደመሩት አንዱ ውድድር ይሆናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቻምፒዮና የብሄራዊ ቡድን መመረጫ ውድድር ነው፡፡
በተለያዩ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎችም በቻምፒዮናው ለመሳተፍ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ መሆኑን የተነገረ ሲሆን፤ በተለያዩ የዓለም ክለቦች በስፔን፣ ፈረንሳይ በጣሊያንና አሜሪካ ክለቦች የሚወዳደሩ ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች ይገኙበታል፡ ፡ በመሆኑም ጥሩ የውድድር ጊዜን በማሳለፍና ብሄራዊ ቡድኑን የሚወክሉ ብስክሌተኞች ተመርጠው ለዓለም አቀፉ የብስክሌት ማህበር በማስተላለፍ ውድድሩ እንደሚቋጭም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015