«እሳት አመድ ወለደ» በጣም ከሚያናድዱኝና መራራውን እውነት አባብለው ከሚግቱኝ ብሂሎች መካከል አንደኛው ነው። ሰው ግን እንዴት በራሱ ላይ ይተርታል? አንዳንድ ብሂሎቻችንኮ ወይ ቅዱሳን መላዕክት ከሰማይ አይተው ታዝበውን አልያም ሌላ ፍጥረት ከሌላ ስፍራ መጥቶ የሰጠን ነው የሚመስሉት። አለ አይደለ? አንዱ ገለልተኛ አካል የተናገረብን እንጂ የእኛው ሰዎች የተናገሯቸው አይመስለኝም።
ይህኛው ያልኳችሁ ብሂል ደግሞ መከራከሪያ የሚሆን ሃሳብ እንኳ ነው የሚያሳጣው። እንዴት? እና እሳት ሌላ ምን ይወልዳል? በእርግጥ እንደ አጠቃቀሙ የበሰለ ምግብ ሊያዘጋጅ ይችላል ወይም ሙቀትን ይፈጥራል። ብቻ ምሳሌ እስከ ፍጻሜው ስለማይጸና ወደ ዝርዝር ነጥቦች ሳንዘልቅ ወደ ነገሬ ልግባ።
አንዳንድ ተመራማሪዎች «መሪ ይወለዳል ወይስ ይፈጠራል?» ሲሉ በሁለቱ ሀሳቦች ዙሪያ ይከራከራሉ። ቀዳሚዎቹ መሪነት በተፈጥሮ እንደሚገኝ ጸጋ፣ ስዕል እንደመሳል ወይም ግጥም እንደመጻፍ ያለ የሚታደሉት ነው ይላሉ። ተከታዮቹና መሪ ይፈጠራል የሚሉት ደግሞ በስልጠናና በሂደት አንድን ሰው መሪ ማድረግ ይቻላል እንጂ፤ መሪነት በጸጋ ብቻ የሚገኝ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።
እነዚህ ምሁራን በዚህ ጉዳይ ላይ በበቂ ሁኔታ ተከራክረዋል ብዬ ስለማምን፤ አሁን ላይ ነገሩን መከራከሪያ ለማድረግ አልፈልግም። ያሳሰበኝ ግን የጀግና ነገር ነው። ጀግንነት በፀጋ የሚወርሱት ነገር ነው ወይስ በሕይወት ልምድ የሚያገኙት? የሚለው ነገር ያሳስበኛል። በተለይ እንዲህ በአርበኞች ቀን ላይ ሲሆን፤ ከተወረሰ ጀግንነታችን የት ሄደ? በስልጠና ከተገኘ ምነው አልሰለጠንን? ስል እንድጠይቅ እገደዳለሁ።
ጀግንነት በእርግጥ ጦርነት ላይ ስለመዝመትና ስለመዋጋት ብቻ አይደለም። በቀደመው ዘመን እንደዛ መሆኑ ትክክል አልነበር ማለት ግን አንችልም። ያኔ በትምህርት አዋቂ ሆኖ አራት ዓይና ከመባል በላይ በጦር ደርጅቶ ግዛትን ማስከበር ነበር ጀግንነት። ይህም ደግሞ ለኢትዮጵያ ትርፍ እንጂ ብዙ ኪሳራን አላመጣም። ተሳሳትኩ? እንዲህ ዛሬ ላይ ብዙ የተማሩ ሰዎች ባሉበት ያለውን እርስ በርስ መጠላላት ስትመለከቱ፤ ያኔ እንኳን ጀግንነት የጦረኞች መጠሪያ ሆነ አያስብላችሁም?
እንካችሁ! በአንድ የዓድዋ ድልን በሚዘክር የውይይት መድረክ ላይ በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያን ይዘውት ስለነበረው መሣሪያ ተነሳ። በውይይቱ መነሻ ሃሳብ ሲያቀርቡ የቆዩት መምህርም ኢትዮጵያን ይዘውት የነበረው መሣሪያ ከጣልያኖቹ ጋር ሲነጻጸር ብዙም ልዩነት ያልነበረው እንደሆነ ጠቀሱ። እንዴት? በጊዜው ፈረንሳይም ሆኑ እንግሊዝ የመሣሪያ ሽያጭም ሆነ ድጋፍ አናደርግም ብለው አልነበር? አዎን! ይሁንና ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱና የመሳሰሉት እንደውም ራሳቸው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ ከዛም እነ አጼ ቴዎድሮስ ጭምር እርስ በርስ ለነበራቸው አንባጓሮ አስቀድመው ከውጭ ያስመጧቸው፣ ነጮቹም «የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው» ብለው እርስ በእርስ ሊያባሏቸው ያስታጠቋቸው መሣሪያ ነበር። «ማርያምን ባትመጣ ትጣላኛለህ» ብለው እምዬ ምኒልክ በአዋጅ ሲጣሩ፤ መሣሪያዎቹም ከዘማቹ ጋር አብረው ዓድዋ ላይ ተገኙ።
ምን ልላችሁ ነው! አንዳንዴ ከኪሳራም ትርፍ ይገኛል። እና እሱን እናቆይና ልብ ብላችሁ ከሆነ በዚህ ጊዜ በአገራችን እግር ኳስም አለ ተብሎ አንድ ጎል ያገባ ጀግና እየተባለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በቃ! ጀግንነት እንደ ዘመኑ ነው። እንደው ግን ያኛው ጀግና አላማራችሁም? ይቅር እንደው ጸጉሩን አያጎፍር፣ ሎቲ አያንጠልጥል፣ ሹሩባ ተሠርታ መቀነቷን ታጥቃ ቆፍጠን አትበል፣ እንደው ይቅር መሣሪያ አይታጠቅ ዱላ አይጨብጥ፣ አገልግል ይዛ ከዘመተው ኋላ በለው እያለች አታበረታታ፤ ግን እንደው ለአገሩ ሲል የህሊናውን ቃል የሚያከብር ጀግና አላማራችሁም?
ነገሩ ከአለባበስ አይደለም፤ በእርግጥ ሌላውን የምናከብረው መጀመሪያ ራሳችንን ስናከብር ነው። ቢሆንም ግን ይሁን! ሱሪውን ታች ያወረደና ቀሚሷን ከፍፍፍ ያደረገች፤ ጸጉሩ ጃርት የመሰለና የሌላ ሰው ጸጉር የተከለች፤ ቋንቋውን የማያውቅ፣ አማርኛ የጠፋባት… ይሁኑ! ምን ሆናችኋል! ፋሽን እና ጀግንነትን አይምታታብና! ብቻ እንደዛም ሆኖ አገር መውደድ በራሱ ጀግና ያሰኛልና እንደው አገሩን የእውነት የሚወድ አላማራችሁም?
ኢትዮጵያን ደጋግመው የሚጠሯትን ሰዎች አብዝተን የምንከታተለውና የምንወደው ለዛ ይመስለኛል፤ አገሩን የሚወድ ሲጠፋ። እንደው እሳት ከአመድ የባሰ ምን ይወልድ ይሆን? ለአገራቸው እስከሞት ሕይወታቸውን የሰጡ ጀግኖች በኖሩባት አገር ስሟን መጥራት እንኳ አቅቶን ጀግና ከዛ ሲጀምር? መቼስ መውቀስ ቀላል ነው!
እሺ ይህስ ደግሞ ይቆየን፤ ኢትዮጵያዊ በመሆን ብቻ ጀግና እንባላለን። በዚህ መሰረት ከሆነ ከጀግንነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አብሮ የሚሰጥ ፀጋ ሆነ ማለት ነው። እናም መሪ ይወለዳል እንደሚሉት ሁሉ ጀግና ይወለዳል ማለት ነው። የምናውቃቸውና የማናውቃቸው ጀግኖች ሁሉ ከየት ተገኙ? ሲባል ጀግና ሆነው ተወልደው ይሆናል መልሱ።
«ማንም በእናቱ ሆድ ውስጥ አልተማረም!» እያለች የቤት ውስጥ ሙያን ያስተማረችን እናቴ እንዲህ ስል ብትሰማ እንደምትታዘበኝ እያሰብኩ ልቀጥል። በእርሷ መሰረት ከሆነ ደግሞ ጀግና የሚፈጠር ነው። ዳግም እንደ አዳም የሚፈጠር ሳይሆን ማኅበረሰብ፣ ቤተሰብ፣ ሕዝብና ስርዓት የሚፈጥረው ነው፤ ጀግና። ወይም ደግሞ በዛ መልኩ ለመፈጠር ፈቃደኛ የሆነ ነው።
እንግዲህ በዚህ መልክ ጀግና ይወለዳልም፤ ይፈጠራልም ሊባል ነው ማለት ነው። ይሁንልሽ በሉኝና ከምንኮራባቸውና ስማቸው መጠሪያ ከሆነን፤ ብሎም ከምንመካባቸው ቀደምት ኢትዮጵያውያን እኛ መወለዳችን ግን አይገርማችሁም? ወይ ጀግኖቹ በአርበኝነትና በዘማችነት ተሰውተው አገር ሲያተርፉልን እኛን ሳይወልዱ ቀርተው መሆን አለበት!
ጀግና የት ይገኛል? በዚህ ጥያቄ መካከል «ሴት የላከው ሞት አይፈራም!» የሚለው ብሂል ደጋግሞ ትዝ ሲለኝ ነበር። ይሄ ሴት ልካው ሞት ያልፈራውን ሰው የትኛው እንደሆነ አውቄ አይደለም፤ ነገሩ ሰው ለወደደው ምንም ነገር ሊሆን ይችላል የሚል መሆኑን ግን አውቃለሁ። ለምሳሌ እናት ለልጇ፣ ወንድ ለወደዳት ሴት፣ ባለሙያ ለሥራው፣ አክቲቪስት ለፌስቡክ አካውነቱ፣…ወዘተ። አርበኛም ለአገሩ እንደዛው ነበር።
እና ለካ የጀግና እናት ወዲህ ናት፤ ጀግና የሚወልደው ከፍቅር ነው። አርበኞችን የወለደው የአገር ፍቅር ነው፣ ታጋዮችን የወለደው የአገር ፍቅር ነው፤ አንዳንድ አክቲቪስቶችንም የወለደው የአገር ፍቅር ነው። በፍቅር ትዳር የሚመሰረትና ቤተሰብ የሚመራ ብቻ የሚመስለው ይኖራል፤ ኧረ ጀግናም ይወለዳል ማለት ነው። ታዲያ በዚህ ሃሳብ ጀግና ይወለዳል ወይስ ይፈጠራል የሚል ጠያቂ ከመጣ፤ በሁለቱም ጀግና ይገኛል ብለን በኩራት እንናገራለን ማለት ነው። ትስማማላችሁ አትስማሙም? ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
ሊድያ ተስፋዬ