“ፈቸት” ከቃሉ ትርጉም ስንነሳ መፈታት ማለት ነው፡፡ በጉራጌ ማህበረሰብ የጋራ ጸሎት (ፈቸት) የተጣሉ ካሉ እርቅ ሰላም እንዲወርድ፣ ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዲቀንሱና ፍቅርና አንድነትን እንዲጎለብት ወደ ፈጣሪ በህብረት በመሆን በአካባቢው ባሉ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት በማድረግ ጸሎት የሚያደርጉበት ሰርዓት ነው፡፡ ይሄ ባህላዊ የጸሎት ስነስርዓት ደግሞ ህብረተሰቡም ተስማምቶበት ሀይማኖት ዘር ሳይለይ ሁሉም አንድ ሆኖ በጸሎቱ ውጤታማ ሆኖ ቆይቷል። ይሄ ባህል ዛሬም በአካባቢው ችግሮች ሲገጥሙ ለእርቀ ሰላመ እየዋለ ይገኛል።
በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን የሰሩት የጉራጌ ባህል ጥናት የጥናት ባለሙያ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መንግስቱ ሀይለማሪያ እንዳሉት ፈቸት በአጠቃላይ እንደ አንድ ማህበረሰብ የሚደረግ አይደለም፤ፀሎቱ ከአንድ ቤተሰብ እስከ ትልቅ ሊሄድ ይችላል፡፡
ባለሙያው አቶ መንግስቱ እንደሚሉት ጎሳ ወይም “ጥብ ” ይሰበሰቡ እና በውስጣቸው የተከሰተ ችግር ካለ ወይም በአካባቢ ብሎም በአገር ደረጃ ችግር ከተፈጠረ እሱን ፈጣሪ እንዲመልሰው እና ሰላም እንዲሆን ፀሎት የሚደረግበት ስርዓት ነው፡፡ ጸሎቱ የየትኛውም ሀይማኖት በጋራ የሚያደርገው ሲሆን ከጸሎቱ በኋላ መስዋት የሚቀርበው ከብት ሆነ ሌላ ለምግብነት የሚውሉ ነገሮች እንደየ ሀይማኖቱ ስርዓት ይዘጋጃል፡፡ጸሎቱ በቤተክርስቲያን አልያም በመስኪድ ከሚካሄዱ ፀሎቶች ይለያል፤ ጸሎቱን ልዩ የሚያደርገው አካታችና ለወገንና ለአገር የሚጸለይ የጋራ ጸሎት በመሆኑ ነው፡፡
የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ ባሳለፍነው ወር ተሰብስቦ በእርቅ ሰላም ዙሪያ በተደረገው ውይይት በሁሉም ቀበሌዎች ምንም አይነት ልዩነት ሳይፈጠር ሁሉም ነዋሪ በአንድነት በመሰብሰብ በተለይ የጉብር የማህበረሰብ ደስ በሚል ሁኔታ አንድነታቸው የበለጠ እንዲጠናከር እና በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በህብረት ሰብሰብ ብለው የጋራ ጸሎት በማድረግ ፈጣሪን ተማጽነዋል፡፡ ይህንን እንደ ማሳያ ማየት ይቻላል፡፡
ባለሙያ ሲያስረዱ አሁን አሁን በሀገሪቱ ብሎም በየአካባቢው ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት በተለያዩ ሰው ሰራሽ አደጋ እያጣን እንደሆነም የሚታወቅ ሲሆን ይህንን በማህበረሰባችን ላይ እያደረሰ ያለውን አደጋ ፈጣሪ ምህረቱንና ይቅር ባይነቱን በማውረድ እንዲታደግልን በአካባቢያችን የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች የሀይማኖት አባቶች ጸሎት ወይም ዱአ በማድረግ በሀገር ላይ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ወሳኝና ጊዜው የሚጠይቀው ነው፡፡
በቅርቡም ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም በሚል በወልቂጤ ከተማ የጉብርየ ክፍለ ከተማ ማህበረሰብ የጸሎት መርሃ ግብር (ፈቸት) አካሂደዋል።
የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ ታዋቂ ሽማግሌዎች የጆካ ተሰብስበው በተለያዩ ሀገራዊና አካባቢያዊ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ለውሳኔ ተፈጻሚነት መልእክቶች እስከ አካባቢና መንደሮች ድረስ የሚወርዱ መሆኑን ይታወቃል ሲሉም አቶ መንግስቱ ይገልጻሉ።
የጉራጌ ዞን የህዝብ ግንኙት በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው በጉብርየ ክፍለ ከተማ በጋራ ጸሎት ወይም ፈቸት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የዞኑ ማህበረሰብ የሚታወቀው ሌላውን ማህበረሰብ የሚያቅፍ፣ የሰው የማይነካ የትኛውንም አካል እንደራሱ የሚያይ ማህበረሰብ መሆኑን ነው የተናገሩት::
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በብሔር ተኮር ግጭቶች የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ንብረቶች ወድመዋል፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬቸው መፈናቀላቸውንም አስታውሰዋል። ይህን አይነት ተግባር ዞኑን የማይመጥን መሆኑን በመረዳት በቃ ሊባል እንደሚገባም ማስረዳታቸውን የክልሉ ህዝብ ግንኙነት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የሀገሪቱ ህዝቦች እርስ በእርስ የሚያስተሳስሩ በርካታ ማንነቶች እንዳሉ ይታወቃል፤ ለዘ መናት የቆየው የሀይማኖት መከባበር፣ የአኩሪ ባህሎች እና ታሪኮች ባለቤቶች መሆናቸውን በማንሳትም ይሄ የነበረ ማንነት ሊጠፋ እንደማይገባም አስገንዝበዋል::
የሰላም ዋጋ ትልቅ ነው። ሰላም ከሌለ እንደፈለጉ ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ ነው። ሰላም ትልቁና ውዱ ሀብታችን በመሆኑ ሁሉም ለሰላሙ ዘብ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል::
የከተማውም የዞኑን ብሎም የሀገሪቱ ሰላም በጋራ መጠበቅ እንደሚገባ ተናግረው ዞኑ በልማት ሌሎች የደረሱበት ለማድረስ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እገዛ ይፈልጋል። በዞኑ የተጀመረውን የሰላምና የልማት ስራዎች ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ግርማ ንዳ በዝግጅቱ የመስተንግዶ አባል ሲሆኑ የጉራጌ ማህበረሰብ በየወሩ የጆካ የባህላዊ ዳኝነት ስፍራ ስብሰባ ያደርጋል። በዚህም ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ሽማግሌዎች በወቅታዊ እና በሌሎች የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ስብሰባ ያደርጋል፡፡
ሰላም በየአካባቢው እንዲሰፍን በተለይ ብሔር ከብሔር ጋር ያለውን ግጭት ጥሩ እንዳልሆነና በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሉትን ሁኔታዎች በሙሉ ለማብረድ ጸሎት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ፈቸት (ጸሎት) በአካባቢ ደረጃ እና ወቅታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ በጦርነት ወይም በመጥፎ ነገር ምላሽ በመስጠት ሳይሆን ወደ ፈጣሪን በመለመን፣ ጸሎት በማድረግ የአካባቢው ማህበረሰብ በአጠቃላይ የሚመለከተው ሁሉ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች እንዲሁም ሴቶች ሁሉም በፍቅር፣ በአንድነትና በመግባባት ጸሎት አድርገዋል። በጉብርየ ክፍለ ከተማ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ስትሆን ሰብሰብ ተብሎ ፈቸት ወይም ጸሎት በሚደረግበት ጊዜ አንድነትን ለማምጣት፣ ስምምነት ለመፍጠር፣ እንዲሁም መተጋገዝ እና መረዳዳትን ሊያመጣ በሚችል ደረጃ ሁሉም አንድነቱን በማሳየት በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ተሰባስቦ የተደረገው ዱአ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል።
የአካባቢው ሽማግሌ አቶ ሙርጋ ሸጎ እንደሚሉት ለሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም መሆኑን አሳስበዋል። ሰላም ከሌለ ሀገር የለችም ማለት ሲሆን በጉብርየ ክፍለ ከተማ ሰላም ማስፈን የመጀመሪያ ተግባራቸው አድርገው በመንቀሳቀስ ጸሎት በማድረግ መላው ህዝብ በፍቅር አንድ እንዲሆን የማድረግ ስራ መሰራቱን ነው የሚናገሩት፡፡
የጉብርየ ክፍለ ከተማ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወክሉ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ናት። ተማሪዎች በነጻነት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ ህዝቡም ሰላም ካላገኘ መስራት እንደማይችል ተናግረው በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ አካባቢውን በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ሰላም ማስፈኑ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ፈቸት የተደረገበት ምክንያት በአካባቢው የተለያዩ ሰላም የሚያሳጡ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ፣ ዝናብ ሲጠፋ ሁከት ሲኖር የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲፈጠሩ የጉራጌ ማህበረሰብ የጆካ ላይ ቁጭ ብሎ ምን እናድርግ? ይህን አደጋ በምን እንወጣው ብሎ ውይይት ያደርግና ጸሎት ወይም ፈቸት ያደርጋል፡፡ ለየግለሰቡ፣ ለማህበሩ፣ ለጎሳው፣ ለከተማው እንዲሁም ለአገሪቱ እንደ ፈቸት ያሉ ሰላምን እርቅን የሚሰብኩ እና ህብረተሰቡን እጅ ለእጅ የሚያስተሳስሩ ባህሎችን በመጠቀም ለሰላም በሰላም ለመኖር እንገልገልባቸው፡፡ ሰላም !
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
አብርሃም ተወልደ