ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ የዓለም ሕዝብ ፊት በክብር እንድትቆም ያደረጉ በርካታ ባለውለታዎች አሏት። በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በየዘመናቱ በትውልድ ቅብብሎሽ ስመ ገናናነቷን ጠብቃ እንድትራመድ እልፍ ጀግኖች ዋጋ ከፍለዋል። ከነዚህም ባለውለታዎች መካከል “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ “እንደሚባለው የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ተሳታፊ ቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ በቅጽል ስሙ (ጋንች) ተጠቃሽ ነው።
የቶኪዮ እና ሜክሲኮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ እንዲሁም የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነው ቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ (ጋንች) ለኢትዮጵያ ቦክስ ስፖርት እድገት ፋና ወጊ በመሆን የሚይተካ ሚናን ተጫውቷል። በኢትዮጵያውያን የቦክስ አድናቂዎች ዘንድ ትልቅ ስም መገንባት የቻለ ቦክሰኛም ነው።
ቦክሰኛው የተወለደው እአአ በ1941 ሲሆን የቦክስ ስፖርትን አሐዱ ብሎ የጀመረው ፊልም በማየት ነበር። የቦክስ ፌዴሬሽንና ክለቦች ከመቋቋማቸው በፊት ባለተሰጥዖ መሆኑን አሳይቷል። በአማተር ደረጃ በርካታ ብሔራዊ ሻምፒዮናዎችን አሸንፏል። በቀለ ዓለሙ (ጋንች) የቦክስ ክለቦች ባለመኖራቸው ለበርካታ ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ስም ይወዳደር ነበር። በዘመኑ በዓለም አቀፍ መድረክ ታላቅነትን የማስመዝገብ አቅም ያለው ከፍተኛ ቦክሰኛ መሆኑንም አሳይቷል። አፍሪካውያን ከነጮች ጋር በስፖርት መሳተፍ ይቅርና አብሮ መታየት ወንጀል በሆነበት ዘመን እሱ ግን በቦክስ ሪንግ ውስጥ ያስመዘገበው ድንቅ ሥራና ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቦክስ አድናቂዎች ዘንድ እውቅና አስገኝቶለታል።
በቀለ አፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱ የቦክስ ውድድሮችን በመሳተፍ የአፍሪካ ቦክስ ሻምፒዮን መሆን ችሏል። የአህጉሪቱን የቦክስ ስፖርት እንዲነቃቃና እንዲስፋፋም አድርጓል። ከአህጉሪቱ በጣም ከባድ የሆኑትን የመካከለኛ ሚዛን ቦክሰኞች በመፋለምም ጥንካሬውን አስመስክሯል።
እአአ ለ1960 የሮም ኦሊምፒክ ሀገሩን ለመወከል የተመረጠ ቢሆንም በወቅቱ የቦክስ ልዑክ በመቀነሱ ምክንያት ሳይሳተፍ ቀርቷል። ቢሆንም በቀለ ውስጥ ባለው እንከን የለሽ ችሎታውና በራስ መተማመን ተመስግኖ ታላቅ አድናቆትን አግኝቷል። ለጥቁሮች አይሆንም፤ ከነጭ ቦክሰኞች ጋር መፋለም ንቀት ነው ተብሎ ለነጮች ብቻ የተባለውን የቦክስ ስፖርት ጥቁሮችም አቅም እንዳላቸው በማሳየት በቃላት ሊገለጽ የማይችል ውለታን ውሏል።
በቀለ ቦክስን አጠናክሮ በመቀጠል እአአ በ1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎውን ማድረግ ችሏል። ወደ ውድድሩ ቀለበት ሲገባ ያለውን ፍትሐዊነት የጎደለው አመለካከት አይቶ ተስፋ አልቆረጠም። ሪንጉ ውስጥ ገብቶ በኩራት ተቧቅሷል። አሠልጣኝና ትጥቅ ባይኖረውም ተስፋ ሳይቆርጥ ተሳትፎውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ልምዱንና በራስ መተማመኑን በመጠቀም በ1968 የሜክሲኮ ኦሊምፒክ በመካከለኛ ሚዛን ዲቪዚዮን ከታላቋ ብሪታኒያ ተፋላሚ ጋር ተፋልሟል፣ ውጤት ባይቀናውም። በቀለ በኦሊምፒክ ለመሳተፍ ያደረጉው ጉዞ ቀላል አልነበረም። ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ እና የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ ተሳታፊ ለመሆን ሁሉንም ችግሮች መታገል ነበረበት። የገንዘብ እጥረቶችን፣ የባለሥልጣናት ድጋፍ እጦትን፣ የግብዓት እጥረትንና የወቅቱን የነጮች እይታን ማሸነፍ ነበረበት። መንፈሱ በዚህ ባለመታወኩም ጠንክሮ ሠልጥኖ ግቡ ላይ ነበር ትኩረት ያደረገው።
የእሱ ስኬት በኢትዮጵያም ሆነ በአጠቃላይ በአህጉሪቱ ያሉ ወጣት ቦክሰኞችን አነሳስቷል። ምንም እንኳን ንቁ የቦክስ ሕይወቱ ከብዙ ቆይታ በኋላ ቢያበቃም፤ በቀለ አፍሪካውያን ወጣቶችን ማበረታታቱን ቀጥሏል፤ ለስኬቶቹም እውቅና አግኝቷል። ይህም በአህጉሪቱ ከተፈጠሩት ታላላቅ ቦክሰኞች አንዱ በመሆን አሻራውን አስቀምጧል።
በቀለ ዓለሙ አስደናቂ የቦክስ ዓለም መሪነት ጉዞን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል ነገር ግን ታሪኩ ትውልድን በማነሳሳቱ ቀጥሏል። የእሱ ስኬቶች በትጋት እና በማያወላውል ቁርጠኝነት ሊከፈት ለሚችለው አቅም ምስክር ሆነው ይቆያሉ። በስፖርታዊ ጨዋነት ያበረከተው ትሩፋት በቁጥር አይገመትም። ፈር ቀዳጁ ቦክሰኛ የኢትዮጵያን ቦክስ በዓለም አቀፍ ካርታ ላይ አስቀምጦ ለታላላቅ አትሌቶች አርዓያ ሆኗል።
የቀደሙት ስፖርተኞች ምንም እንኳን ፈር ቀዳጆችና ግንባር ቀደም መሆን ቢችሉም ከራሳቸው ሀገርን በማስቀደም የሚችሉትን አበርክቷል። ለስፖርቱ ከከፈሉት ዋጋ አንጻር ያገኙት ትርፍ የሕዝባቸውን ፍቅርና አድናቆት ብቻ ነው። በመሆኑም ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርም ሆነ ለራሳቸው የሚበቃ በቂ ገንዘብ ማፍራት አልቻሉም። ከዛም አልፎ የጤና ችግር እንኳን ሲገጥማቸው መታከሚያ ገንዘበ በማጣት አጋዥ ፍለጋ እጃቸውን ሲዘረጉ ይስተዋላል።
እንዳለመታደል ሆኖ ፈር ቀዳጁ ቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ (ጋንች) ዕጣ ፋንታም ከዚህ የተለየ አልሆነም። ጠንካራ ቡጢ የሚሰነዝሩ ክንዶቹ ዝለው ዛሬ ላይ የአልጋ ቁራኛ ሆኗል። በጠና ሕመም ውስጥ ሆኖም የያኔው ፈርጣማ ክንዱ ከስፖርት ቤተሰቡ እርዳታ እንዲጠይቅ ተገዷል። በአሁኑ ወቅት ሕመሙ ስለጸናበት በቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተኝቶ እየታከመ ይገኛል። ይህን ታላቅ አርዓያና የሀገር ባለውለታ ለመታደግም የሁሉንም ስፖርት ቤተሰብ ርብርብ ያስፈልጋል።
በቀለ ዓለሙ የሕክምናው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ኅብረተሰቡ እና በጎ ፍቃደኞች እንዲረዱት እና የሕክምና ወጪውን እንዲሸፍንለት ይጠይቃል። በዓለም ዙሪያ ያሉ የቦክስ አፍቃሪዎች ለበቀለ ዓለሙ (ጋንች) የሕክምና ገንዘቡን በማዋጣት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። አሁን የስፖርት ማኅበረሰቡ ከጎኑ በመቆም ለሕክምና የሚያስፈልገውን ገንዘብ አስተዋፅዖ በማድረግ ድጋፉን የሚገልጽበት ጊዜ ነው። የቦክሰኛው የጤና ሁኔታ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ማንኛውም ድጋፍ የወደፊት ሕይወቱን ለማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የአገር ባለውለታን ማስታወስ ነው።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም