ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? መቼም በጣም ጥሩ ነው የሚል መልስ እንደምትሰጡኝ አምናለሁ። ምክንያቱም ጎበዝና ቤተሰቡን የሚሰማ ልጅ በትምህርቱ ውጤታማ አለመሆን አይችልም። ይህ ደግሞ ዘወትር ደስታን ይፈጥርለታል። ደስታ አለ ማለት ደግሞ ምኞት ሁሉ ጥሩ ይሆናል። ከዚህ አንጻርም ትምህርት እንዴት ነው ስትባሉ ሁልጊዜ መልሳችሁ በጣም ጥሩ ነው የሚል ይሆናል።
ልጆች ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ሀሳብ የምታውቁት ቢሆንም ቀናችሁን ምክንያት አድርጎ ማንሳት ጠቀሜታው የጎላ ነውና ስለ ሰኔ 9ኝ እናወራለን። እንደምታውቁት ሰኔ 9 የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ይከበራል። ይህ ቀን እንዴትና ለምን ተመረጠ ካላችሁ ትንሽ ነገር በጉዳዩ ዙሪያ ያነበብኩትን ላካፍላችሁ።
ቀኑ ታስቦ የሚከበርበት ምክንያት በአፓርታይድ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ መብታቸው እንዲከበር የጠየቁ ሕፃናት በግፍ ስለተጨፈጨፉ እነርሱን ለማሰብ በሚል ነው እንዲከበር በአዋጅ ጭምር የተቀመጠው። ስለዚህም በየዓመቱ ጁን 16 ቀን በእኛ ደግሞ ሰኔ 9 ዕለቱ ታስቦ ይውላል። የአፍሪካ ሀገራት ሕጻናትም ቀኑን በተለያየ ዝግጅት ያከብሩታል። እኛ ሀገርም ቢሆን እንዲሁ ቀኑን በማሰብ በተለያየ መሪ ሀሳብና ዝግጅት ይከበራል።
ቀኑ ታስቦ እንዲከበር ውሳኔውን ያስተላለፈው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲሆን፤ በ26ኛ መደበኛ የሀገራትና የመንግሥታት የመሪዎች ጉባኤያቸውም ነው ውሳኔን እንዲያስተላልፉ የሆኑት። ዓመቱ ደግሞ ጁላይ 1990 ነው። የአፍሪካ ሕጻናት መብቶች ደህንነት ቻርተር ከኖቬበር 29 ቀን 1999 ጀምሮ ቻርተሩን ባፀደቀው ሀገሮች ሥራ ላይ ውሏል። ይህም ቻርተር በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኦክቶበር 2 ቀን 2002 ከፀደቀ በኋላ የመቀበያ ሰነዱ በቻርተሩ አንቀጽ 47(2) መሠረት ዲሴንበር 27 ቀን 2002 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቢሮ ገቢ ሆኗል። ስለሆነም በቻርተሩ አንቀፅ 47(3) መሠረት ከጃንዋሪ 2003 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ውሏል። በዓሉም መከበር የጀመረው ከዚህ ዓመት ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ለመሆኑ ልጆች ይህ ቀን መከበሩ ምን ጥቅም አለው ማለታችሁ አይቀርም። ጥቂት ስለበዓሉ መከበር ደግሞ እናንሳ። አንዱ የሕፃናትን ደህንነትና ጥቅም ማስጠበቅ ማስቻሉ ሲሆን፤ እንዴት ካላችሁ የእያንዳንዱ ሀገር ግዴታ እንዲሆን በተፈራረሙት ቻርተር አስቀምጠዋልና በቻርተሩ ላይ ያለውን ተግባር እንዲከውኑ ስለሚገደዱ መብታቸው የተከበረ መሆኑን ለማረጋገጥ ያስችላል። ለሕጻናት ጉዳይ ሁሉም ሀገር የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥም ያደርጋል።
በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ከችግራቸውም ለመውጣት የሁሉም አካላት ተሳትፎን ለሚሹ ልጆች በቀላሉ እንዲደረስላቸው ዕድል ይሰጣል። ማኅበረሰብን መሠረት ያደረገ ድጋፍ ለማድረግም ወሳኝነት አለው። ይህ ሲባል ሕፃናት ቀያቸውን ሳይለቁ በሚኖሩበት አካባቢ ደስተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ ያግዛቸዋል። በማኅበረሰብ ላይ የተመሠረተ የሕፃናት እንክብካቤ እንዲኖርም ያስችላል። በተጨማሪም ቀኑ ሲታሰብ በርካታ ሕፃናትን ለመድረስ እድል ያመቻቻል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ልጆች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልዩ ተሰጥዖዋቸውን እንዲያወጡበት ያደርጋቸዋል። ምክንያቱም ዕለቱ ሲከበር የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያደርጉት የበዓሉ ባለቤት የሆኑት ሕጻናት ናቸው። እናም ወግና ባሕላቸውን አውቀውና ጠብቀው የአዲስ ፈጠራ ባለቤት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ልዩ ፍላጎታቸውን እንዲያውቁም ዕድል ይሰጣቸዋል።በተመሳሳይ የፈጠራ ሥራቸውን በማሳየት ወላጆች እንዲሁም ማኅበረሰቡ እንዲደግፋቸውና እንዲደሰትባቸውም ያደርጉበታል።
ራሳቸውም ቢሆን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥሩበታል። ምክንያቱም በዕለቱ በሚፈጠረው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሠረታዊ መብትና ግዴታቸውን እንዲያው ቁበት ይሆኑበታል። ፍላጎቶቻቸውን ተረድተው በቀጣይ እንዲያጎለብቱበት መንገድ ይጠርግላቸዋል።
ልጆች ለመሆኑ ሰኔ 9 ቀን የአፍሪካ ሕፃናት ቀን ሆኖ ሲከበር ዘንድሮ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ ታውቃላችሁ ? በአፍሪካ ደረጃ 33ኛ ጊዜ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ በተለየ መሪ ሀሳብና ዝግጅቶች ይከበራል። እናም ይህ ሁሉ ጥቅም እንዳለው አውቃችሁ በዓሉን በፍቅርና በደስታ ማክበር ይኖርባችኋል። መልካም በዓል በማለት በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ጉዳይ እስከምንገናኝ ለዛሬ የያዝኩትን ሀሳብ ልቋጭ። መልካም ሰንበት!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም