ከወራት በኋላ የ2024 ኦሊምፒክን በታሪኳ ለሶስተኛ ጊዜ የምታዘጋጀው ፓሪስ ነገ ትልቁን የዳይመንድ ሊግን ውድድር ታስተናግዳለች። የዳይመንድ ሊጉ አራተኛዋ መዳረሻ ከተማ በሆነችው ፓሪስ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ከመላው ዓለም የተወጣጡ በርካታ ምርጥ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ይፋለማሉ። ይህም በውድድሩ በበርካታ ርቀቶች የዓለም ክብረወሰን ሊሰበር ይችላል የሚል ቅድመ ግምትም እንዲያገኝ አድርጎታል። የዓለም ከዋክብት አትሌቶች በዚህ ውድድር ሁለት ወራት ብቻ ለቀረው የቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮና አቅማቸውን የሚፈትሹበት መድረክ መሆኑን ተከትሎም አዲስ ነገር ይታያል በሚል ይጠበቃል።
ውድድሩ ከሚካሄድባቸው በርካታ ርቀቶች በተለየ መልኩ የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ ከወዲሁ መግዛት የቻለው በሴቶች መካከል የሚደረገው የ5ሺ ሜትር ውድድር ነው። በዚህ የውድድር ዓመት በተካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በዚህ ርቀት የሚደረገው የመጀመሪያው ሩጫም ነው። በውድድሩ እንደሚካፈሉ ያረጋገጡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደግሞ የርቀቱ ኮከቦች እንደመሆናቸው ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ሊያገኙ ችለዋል። በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለውጤት ሲጠበቁ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በሁለቱም ጾታ በዚሁ ርቀት የክብረወሰን ባለቤቶች መሆናቸው ደግሞ ለዚህ አንዱ ምክንያት ነው። በወንዶች በኩል ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እአአ በ2005 የፓሪስ ዳይመንድ ሊግን 12:40.18 በሆነ ሰዓት በመግባት እስካሁንም ያልተፋቀ ታሪክ አኑሯል።
ሌላኛው በቦታው የተመዘገበ ሰዓት ደግሞ ከ10 ዓመታት በኋላ በፈጣኗ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እአአ በ2015 የተያዘ ነው። አትሌቷ የገባችበት 14:15.41 የሆነ ሰዓት እስካሁን የሚደፍረው ባለመገኘቱ የቦታው ክብረወሰን እንዲሁም የግሏም ፈጣን ሰዓት ነው። ነገ በሚደረገው የፓሪስ ዳይመንድ ሊግ ደግሞ በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው የሀገሯ ልጅ አዲስ ድል ለማስመዝገብ የምትሮጥ ይሆናል። የዓለም የ10ሺ ሜትር አሸናፊዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለዓመታት በገንዘቤ ዲባባ የተያዘውን ይህንን የቦታውን ፈጣን ሰዓት እንደምታሻሽልም ይጠበቃል።
ለተሰንበት እአአ በ2020 ቫሌንሲያ ላይ ያስመዘገበችው 14 ደቂቃ ከ06 ሰከንድ ከ62 ማይክሮ ሰከንድ የሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን ነው። ይህም አትሌቷ በውድድሩ ላይ ከሚካፈሉ ተፎካካሪዎቿ ጋር ሰፊ ልዩነት ያለው በመሆኑ አሸናፊነትና የቦታውን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ እንድትጠበቅ አድርጐታል። በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች በርቀቱ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት የያዘችው አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ስትሆን፤ ከለተሰንበት በ6 ሰከንዶች የዘገየ ሰዓት ባለቤትም ናት። ለምለም ኃይሉ፣ ትዕግስት ከተማ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ድርቤ ወልተጂም በፓሪስ ዳይመንድ ሊግ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መሆናቸው ታውቋል። ይኸውም ለአትሌቶቹ የቡድን ጥንካሬ በመስጠት ሩጫቸውን በድል እንዲያጠናቅቁ የማድረግ አቅም እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ለኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች የዘወትር ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑት ኬንያዊያን አትሌቶችም በዚህ ውድድር በስፋት የሚካፈሉ ሲሆን፤ ፌይዝ ኪፕዮጎን ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡን ትኩረት የሳበች ሆናለች። አትሌቷ ከቀናት በፊት በሮም(ፍሎረንስ) ዳይመንድ ሊግ በ1ሺ500 ሜትር ተሳትፋ የዓለም ክብረወሰንን በመስበር ማሸነፏ የሚታወስ ነው። በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እአአ ከ2015 አንስቶ ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በአንድ ሰከንድ በማሻሻል 3:49.11 በሆነ ሰዓት ያስመዘገበችው ይህች አትሌት፤ ከቀናት በኋላ በድጋሚ በፓሪስ 5ሺ ሜትር ተሳታፊ እንደምትሆን አረጋግጣ ነበር። በከፍተኛ የብቃት ጥግ ላይ የምትገኘው አትሌቷ 14ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ከ93ማይክሮ ሰከንድ የሆነ ፈጣን ሰዓት አላት። ማርጋሬት ቺሊሞ እና ባትሪስ ቼፕኮች በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ ሌሎች ኬንያዊያን አትሌቶች ናቸው።
በፓሪስ ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል አንዱ የወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ነው። በዚህ ውድድር ላይም የርቀቱ ምርጥ አትሌት ለሜቻ ግርማ ተካፋይ መሆኑ ታውቋል። ዶሃ ላይ በነበረው የዳይመንድ ሊጉ የመክፈቻ ውድድር በ3ሺ ሜትር ተሳታፊ የነበረው ወጣቱ አትሌት የሀገሩን ልጆች በማስከተል በአሸናፊነት ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በነገው ውድድር ደግሞ በዓለም ቻምፒዮንና እንዲሁም በኦሊምፒክ መድረኮች 3 የብር ሜዳሊያዎችን ባጠለቀበት 3ሺ ሜትር መሰናክል ይሮጣል። ለሜቻ ባለፈው ዓመት ኦስትራቫ ላይ 7:58.68 የሆነ የግሉን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን፤ ይኸውም በውድድሩ ተሳታፊ ከሚሆኑ አትሌቶች ሁሉ የተሻለው ነው። አትሌቱ ባለው ልምድ የፓሪስ ዳይመንድ ሊግ አሸናፊ እንደሚሆንም ቅድመ ግምቱን አግኝቷል። የሀገሩ ልጅ ኃይለማርያም አማረም የውድድሩ ተካፋይ ነው። በኬንያዊያን በኩል ከሚሳተፉት ቤንጃሚን ኪገን እና አብርሃም ኪብወት የመሳሰሉ አትሌቶችም ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቀውም ይገመታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2015