“ዲያስፖራ” የሚለው ቃል በግርድፉ “በውጭ የሚኖሩ ትውልደ . . .” የሚል መሰረታዊ ሀሳብን የያዘ፣ ቃል ሳይሆን ጽንሰ-ሀሳብ ነው። ምንም እንኳን “ዲያስፖራ” የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ ቀደምት ጥናቶች ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚል ባይገኝም፣ በውጭ የሚኖሩ “ትውልደ ኢትዮጵያዊያን” ግን በዚሁ በዲያስፖራ ረድፍ ስር እየተካተቱ መጠራታቸውን እየተመለከትን ነው። መመልከት ብቻ ሳይሆን የማዕረግ ያህል ሁሉ እየተቆጠረ ከድምጽ አወጣጥ ጀምሮ እስከ ቃሉ ቅላፄ ድረስ በክብር ተግባራዊ ሲደረግ እያየንና እየሰማን እንገኛለን። ይህ ብቻም አይደለም፣ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት የተዘጋጀ “የዲያስፖራ ፖሊሲ” ብቻ ሳይሆን በፖሊሲው መሰረት ጉዳዩን የሚከታተል፣ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም (በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ያለ)ም አላት።
ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ፤ “እኛ ኢትዮጵያዊ እንጂ ዲያስፖራ አይደለንም።” የሚል ወገን እንዳለም እዚህ ላይ ሳይጠቅሱ ማለፍ ስራችንን ያዛባዋል። (ይህ እውነት የሚመስልበትና “ዲያስፖራ” የሚለው በጥንት ከባርነት ጊዜ ጀምሮ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ወደ አሜሪካ የሄዱትን የሚመለከት ከመሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያን ስደትን የጀመሩት አሁን፣ በዘመነ ደርግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሲመረመር፤ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሌላ ዓለም ሄደው ጥገኝነት መጠየቅ የጀመሩትም በዚሁ የፖለቲካ ዘመን ነው የሚሉም አሉና ይህንንም ሳይጠቅሱ ማለፍ አያስኬድም ብቻ ሳይሆን ታሪክንም ማወላገድ ነው።)
“ግራም ነፈሰ ቀኝም ነፈሰ / ታፈሰ ተሰማ ልብሱን ለበሰ” እንደ ተባለው፣ ምንም ተባለ ምን የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን በሌላው ዓለም እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ኪነጥበብን እንዴትና ለምን አላማ እየተገለገሉባት እንደሆነ መመልከት፤ እንዲሁም፣ እያደረጉት ያለ አስተዋጽኦ ካለ መፈተሽ ነው።
በተለያዩ የአለማችን ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን (የሌሉበት የለም ነው የሚባለው) ሁሉም እንደየፍላጎቱና አቅሙ ለአገሩ የሚያደርገውን እያደረገ ይገኛል። ምናልባት በአንዳንዶች፣ በተለይም ከምጣኔ ሀብት (ባለሙያዎቹ “ሬሚታንስ” የሚሉት) ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶች ቢኖሩም፤ በፖለቲካው መስመር የሚፈለግም፣ አንዳንዴ የማይፈለግም ጡዘት ቢኖርም፤ ምንም አይነት ምክንያት በሌለው ጉዳይ እዛው እርስ በእርስ የመጋጨት ሁኔታዎች ቢስተዋሉም፤ . . . ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ሆነው አገራቸው ከአእምሯቸው፤ ስሟ ከከንፈራቸው አትጠፋም። ይህ በማንም፣ በሁሉም የተመሰከረለት እድሜ ጠገብ እውነታ ነው በአንጋፋ ዲፕሎማቶች ሳይቀር።
ከእነዚህ የኢትዮጵያን ዲያስፖራ ከሚያደንቁት፣ ከሚያሰጋቸው፣ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከማይደራደራቸው እውቅና ስመጥር ዲፕሎማቶች አንዱ በ1950ዎቹ(?) በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን አበጥረው የሚያውቁት፣ የአገራቸው ፖለቲካ ፊት መሪና ዘዋሪ (በተለይ በውጭ ጉዳይ፣ በአፍሪካ ጉዳዮች እንዲሁም በቀንዱና አካባቢው)፤ የ“Historical Dictionary of Ethiopia” (መጽሐፉን ልብ ይሏል) ደራሲ ወዘተርፈ የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሺን ሲሆኑ፤ በአንድ ወቅት፣ ለውጡ ሊመጣ አካባቢ በአንድ ግዙፍና ተደማጭ መድረክ (ዝግጅቱ ዩቲዩብ ላይ አለ) ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤
“[. . .] የኢትዮጵያን ዲያስፖራ፣ እዚህ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ሳያስቡ፤ እነሱን ሳያካትቱ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ማሰብ እማይሆን ነገር ነው” ነበር ያሉት። ይህ ውጭ ስላሉትና ከላይ ስለተነጋገርነው ጉዳይ በቂ ማረጋገጫ ነውና ወደ ተነሳንበት እንመለስ።
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በሙያ፣ በተሰማሩበት የስራ መስክ . . . ከፋፍሎ ማየት የማይታሰብ ሲሆን፣ ከምክንያቶቹም አንዱ ብዙ ስለሚሰራ ነው፤ ጠዋት አስተናጋጅ ከሆነ ማታ ታክሲ ይዞ ሊታይ ይችላልና ነው። ከዚህ አኳያ የዲያስፖራውን ተሳትፎ በታትኖ ከማየት ይልቅ ከኪነጥበብ (ሙዚቃ፣ ሥዕል፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ቅርጻ ቅርጽ . . .) አኳያ ምን ምን ተግባራት እየፈፀመ እንደሆነ ማየት ሲሆን፤ በተለይም የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ወደ ሆነው ወደ ሥነ ጽሑፍ በማድላት አንዳንድ ሀሳቦችን እንደ መነሻ ይሆኑ ዘንድ እናሰፍራለን። ማሳያ ይሆኑን ዘንድም በጉዳዩ ላይ ገፋ አድርገው ከሄዱት ኢትዮጵያዊያን ስራዎች እየጠቀስን ሃሳባችንን መሰረት እናሲዛለን።
እርግጥ ነው፣ ኢትዮጵያዊያን ስለ አገራቸው ተኝተው አያድሩም። በድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ሀሳባቸው ሁሉ እዚህ ነው። ይህ ደግሞ በእኛ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የናኘና እውቅናን ያገኘ ሲሆን፣ እንደውም “እንደ ኢትዮጵያዊያን ተደራጅቶ ለአገሩ የሚተጋ ዜጋ በዓለም የለም” እስከ መባልና መጻፍ ድረስ የዘለቀ ተግባር ነው።
ኪነጥበብን ከዲያስፖራው ጋር አያይዘን ከተመለከትን አስቀድሞ ወደ አእምሯችን ጓዳ ከተፍ የሚለው የድምፃዊዎቻችን ያልተቋረጠ ኪነጥበባዊ ተግባር ነው። ይህን ደግሞ ተስፋዬ ገብሬ (ነፍሱን ይማረውና)፣ አስቴር አወቀ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ አብዱ ኪያር . . . እና የመሳሰሉ ድምፃዊያንንና ስራዎቻቸውን በማስታወስ ይህንን እዚሁ ላይ አቁሞ ወደሚቀጥለው መሄድ ይቻላል።
ወደ ሥዕሉ ዓለም ስንመጣም ከገብረክርስቶስ ደስታ ዘመን ጀምሮ (ከዛም በፊት ሊኖር ይችላል) ያለውን ማንሳትና መነጋገር ይቻላል። ወደ ሥነ ጽሑፋችን እንምጣ። መቼም ሥነ ጽሑፍ ዘውጎቹ ብዙ ናቸው እና ከታሪክ እንጀምር።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መጽሐፍ በመጻፍ በኩል ያለ አቻ ዓለምን እየመሩ ነው ማለት ይቻላል። መነሻችን “ዲያስፖራ” እሚለው እስከ ሆነ ድረስ ማለት ነው። ይህንን ስንል ከብዛት አኳያ እንጂ ሌላ አይደለም። አሁንም ይህንን ስል “ጥራት”ን እያጣጣልኩ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ሌላውን ሁሉ ትተን ወደ ድህረ-ኢሕዴግ ዘመን ስንምጣ በርካታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሕይወት ታሪካቸውን፣ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን፣ የሕይወት ገጠመኞቻቸውን፣ የቤተሰብ ሁኔታና ይዞታቸውን፣ ለአገራቸው ስለሚመኙት የፖለቲካ ሥርዓት፣ የዲሞክራሲ አይነት፤ ግጥሞች፣ አጫጭር እና ረዣዥም ልቦለዶች፣ ታሪኮች፤ ተረቶች ወዘተርፈ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል።
ከክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” (እንደ ብቸኛ ማጣቀሻ ተቆጥሮ አመታትን የዘለቀ፣ ጠብሰቅ ያለና የተማሪዎችን እንቅስቃሴና የኢህፓን ትግል ከነ“ድክመት”/ጥንካሬው የሚገላልጥ መጽሐፍ)፣ ከሕይወት ተፈራ “Tower in The Sky” (በኋላ “ማማ በሰማይ ስር” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተመለሰና ከክፍሉ ታደሰ ጋር በትይዩ የሚታይ ሆኖ ጌታቸው ማሩ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ)፤ ከወደ ዚምባቡዌ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም “ትግላችን” (ቅጽ አንድ)፤ . . . ጀምረን ብንቆጥር እዛ ብቻ ሳይሆን እዚህ አገር ቤት ድረስ ገብተው እጅግ አነጋጋሪ፣ ተጠቃሽ፣ አወያይ . . . የነበሩ ስራዎችን እናገኛለን።
ወደ ልቦለዱና ሥነግጥሙ ዓለምም ስንመጣ ያውና ተመሳሳይ ሲሆን፣ ብዙዎች ብዙ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል።
ኃይሉ ገብረዮሐንስ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ አቶ አሰፋ (በእንግሊዝ አገር ይኖሩ የነበሩና GMT በሚል ምህጻረ ቃል የሚታወቁ) እና ሌሎችም በስደት ዓለም ላይ ሆነው ስለአገራቸው ብዙ ሲያስቡ፤ ብዙ ሲያልሙ፤ ብዙም ሲጨነቁ የኖሩና ያንን ጭንቀታቸውን፣ ህልማቸውን ወደ ጽሑፍ በመቀየርና በፈጠራ በመከሸን ለአንባቢያን ሲያቀርቡ፤ ሕዝብን ሲያነቁ፤ የሥነጽሑፍ ውኃ ጥምን ሲቆርጡ ነው የኖሩት። የዛሬው ተጠቃሻችንም እንደዛው።
(በመሰረቱ እዚህ ያሉትን እዚህ ከሌሉት ኢትዮጵያዊያን ጋር ስራዎቻቸውን ለያይተን ማየት ያስፈለገበት ትልቁ ምክንያት የሙያ ጉዳይ ሲሆን፤ ሙያው ጉዳዮችን ከሥነልቦና፣ አካላዊና ህሊናዊ ግንኙነት፤ እንዲሆንም፣ ቀጥታ ተሳትፎና አድራጊ ተደራጊነት ጋር የተያዙ በርካታ ሰዋዊ ባህርያት በመኖራቸው ሲሆን፤ የስፍራና ጊዜ ጉዳይም እንደዚሁ ከግምት ውስጥ የሚገቡ መሰረታዊያን ናቸው። በመሆኑም በአንድ ጀምሎ ማየቱ ስራዎቻቸውን ከማደብዘዝ ያለፈ ፋይዳ የሌለው መሆኑን በቅንፍ አስቀምጠን ወደ ተነሳንበት እንመለስ።)
ከላይ ለተንደረደርንበትም ሆነ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ኪነጥበባዊ ተሳትፎ እዚህ እንድናነሳና ይህችን ሀሳብ እንድንለዋወጥ ምክንያት የሆኑን ከወደ ጀርመን (ፍራንክፈርት) ያገኘናቸው (በስራዎቻቸው አማካኝነት ማለት ነው) “እንግዳችን” ሁለገብ (ከርዕሰ-ጉዳይ አኳይ) ገጣሚ ደሳለኝ ከበደ ናቸው።
ደራሲና ገጣሚ ደሳለኝ ከበደ ድህረ 1983 ዓ/ም ከአገራቸው የወጡ ሲሆን፣ ትዳር መስርተው፣ ልጆች አፍርተውና በርካታ መጻሕፍትን ለአደባባይ አውለው ጀርመን አገር በመኖር ላይ ይገኛሉ።
ደራሲና ገጣሚ ደሳለኝ ከበደን ከመጻሕፍቶቻቸው መረዳት እንደሚቻለው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንደ አስካሪ አልኮሆል ራሳቸው ላይ የወጣ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለአፍታ እንኳን የማይደራደሩ፤ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ “በአገርህ ላይ ክፉ አትይ፣ ክፉ አትስማ፣ ክፉ አትናገር” ያሉትን አይነት ተግባር በመፈፀም ላይ ያሉ፤ ለትውልድ አብዝተው ተቆርቋሪና ተጨናቂ፣ የአገራቸውን ባህል፣ ታሪክ፣ ስነምህዳር . . . ላላወቃትና ላልተገነዘባት ወገን ለማስገንዘብ ሌት ተቀን የሚጥሩ፤ ለአያት ቅድመ አያቶቻቸው ክብር ዘብ የሚቆሙ፤ ለጦር ሜዳ ውሎአቸውና ጀግንነታቸው ታሪክን በማጣቀስ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ፤ የቀድሞ የአገሪቱ መሪዎች ለሰሯቸው፣ ለሞከሯቸው፣ አቅደዋቸው ለነበሩት ስራዎች አድናቆትንና እውቅናን በመስጠት ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚተጉ፤ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ ፍቅር በእጅጉ የሚመኙ፤ ውድቀቷን ከመስማትም ሆነ ከማየት ፈጣሪ እንዲታደጋቸው ሌት ተቀን የሚፀልዩ ሰው ናቸው። ስራዎቻቸውን ስንመረምር እንደተረዳነው።
ይህ፣ ከዚህ በላይ ስለ ደራሲና ገጣሚ ደሳለኝ ከበደ የገለፅነው የተጋነነ የሚመስለው ካለ ከስራዎቻቸው መካከል ይበልጥ የሚገልጿቸውን፣ “የፍራንክፈርት ግጥሞቼ ፩” እና “የፍራንክፈርት ግጥሞቼ ፪”ን፣ በተለይም በ“ለእምዬ ኢትዮጵያ” የሚጠናቀቀው “ኢትዮጵዊነት ነው”፤ “ኢትዮጵያዊነት” እና ሌሎቹንም መመልከት ይቻላል።
ከላይ “ሁለገብ” ያልናቸው ሰውየው በዝርውና በግጥም ከመጠበብም ባለፈ ወደ ሳይንሱ ዓለምም የዘለቁ (ሙያቸው ባይሆንም)፣ ዘልቀውም ለአገሬ ወጣቶች ይበጅ ይሆናል፤ ለመጪው ትውልድ ይሆን ይሆናል፤ በአገሬ ሳይንስ ይስፋፋ ዘንድ የመሰረት ድንጋይ በመሆን ያገለግል ይሆናል፤ ለችግርና መከራ እጅ ላለመስጠት ጥሩ ምክር ይሆናል፤ በጥረት የፈለጉበት መድረስ እንደሚቻል ማሳያ ይሆናል፤ ለአገርና ወገን አስተዋፅኦ ለማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ እንደ መነሻ ይሆናል በማለት የአልበርት አንሽታየንን ከ-እስከ “አልበርት አንሽታየን” በሚል ርዕስ በአማርኛ አሳምረው ያቀረቡ ሰው ናቸው።
በስራዎቻቸው ውስጥ አብዝተው ኢትዮጵያ፣ ወጣቱ ትውልድ፣ አባቶቻችን፣ ስልጣኔዎቻችን፣ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶቻችን፣ የስልጣኔ አሻራችን፣ ቀደምትነታችን . . . እና የመሳሰሉት የማይጠፉት አቶ ደሳለኝ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በ“የፍራንክፈርት ግጥሞቼ ፩” እና “የፍራንክፈርት ግጥሞቼ ፪” መጻሕፍቶቻቸው መግቢያ ላይ ገልፀውት ስንመለከት ከላይ ላልንላቸው ደጋፊ ሆኖ እናገኘዋለን።
በስራዎቻቸው ውስጥ ሳይጠቀሱ የማይታለፉት አክሱም፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ፋሲል ግንብ፣ ሶፎ ኡመር ዋሻ፣ መቅደላ . . .፤ እንዲሁም፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አእዋፍ እና እፅዋት (ቀይ ቀበሮ፣ ዋሊያ)፤ ስመጥር ጸሐፍት (ጎሞራው (ለምሳሌ “ይድረስ ላንተ ጎመራው” ግጥም)፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ፕ/ር ማሞ ሙጨ . . .)፣ የአገር ባለውለታዎች፤ አርበኞች፤ ጋራ ሸንተረሮች፣ ስለ ስደትና ስቃዩ . . . በእውነት ሰውየው ምን ያህል አገራቸውን እንደሚወዱ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል አገራቸውንም እንደሚያውቁ ማሳየት ብቻ ሳይሆን፤ ስራዎቻቸው፣ በተለይ ውጭ አገር ተወልደው እዛው ላደጉ ኢትዮጵያዊያን፣ በመማር ላይ ላሉ ህፃናት ስለ አገራቸው በሚገባ እንዲያውቁ ከማድረግ አኳያ የሚኖራቸው ድርሻ ቀላል አይደለምና አቶ ደሳለኝን ከደራሲ/ገጣሚነታቸው ባለፈ የአገራቸው አምባሳደርም ናቸው ማለት ይቻላል።
የስራዎቻቸውን (በተለይም የግጥሞቻቸውን) መሰረት ከቃላትም በዘለለ በምስል፣ ፎቶግራፍ ማስደገፍን ምርጫቸው ያደረጉት አቶ ደሳለኝ፣ ከላይ እንዳልነው ምናልባትም ከአገሩ ውጭ የሆነ ሰው ስለ አገሩ አንድ ራሱን የቻለ አእምሯዊ ምስል እንዲፈጥርና አገሩን እንዲያውቃት አስበው ይሆናልና ስራዎቻቸው አምስቱንም የስሜት ህዋሳት የሚያረኩ ወደ መምሰሉ የተቃረቡ ናቸውና ሰውየው የዋዛ አይደለም።
እዚህ አዲስ አበባ፣ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል አምስቱንም ስራዎቻቸውን ያስመረቁት ገጣሚ ደሳለኝ ከበደ በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ ጎምቱ ጎምቱ ኢትዮጵያዊያን ከአገር ውስጥም ከተለያዩ አገራት በመምጣትም የተገኙ ሲሆን፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ ስለ አቶ ደሳለኝ ብርታት፣ ትጋትና ትኩረት አድናቆታቸውን ሰጥተው እንደነበረ በወቅቱ በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ከነበሩ ሰው መረዳት ተችሏል።
ስናጠቃልለው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መጽሐፍ በመጻፍ በኩል የሚታሙ አይደሉም። በኪነጥበቡ፣ በተለይም በሥነጽሑፉ ዓለም ብቻ ሳይሆን በጥናትና ምርምሩም ነብር ስለመሆናቸው ከበፊቱም ጀምሮ የተመሰከረላቸው ናቸው። በመሆኑም፣ በዚሁ ይቀጥሉ ዘንድ አደራ እያልን ትኩረታቸውን አገራቸውን ማስተዋወቅ፣ ትውልድ መገንባት፣ አገር ፍቅርን ማስረፅ፣ አርአያ ግለሰቦችን ማንገስ፣ አገርን ማስተዋወቅ . . . ላይ ሊያደርጉ፤ በያሉበትም የየአገራቸው አምባሳደር እንዲሆኑ እያሳሰበ ኢትዮጵያን ማሻገሩ ላይ አንድ ልብ ሆነን ልንሰራ ይገባል እንላለን። ለመሰናበቻ ከገጣሚ ደሳለኝ ከበደ ግጥሞች አንዱን፣ ከ“የፍራንክፈርት ግጥሞቼ ፪”፡-
አንተ የዛሬው ሰው! አንተ የነገው ሰው!
ኢትዮጵያዊነትክን እንዴት ነው እምትገልጸው!?
ለትውልድ ለሁሉም እውነቱ የቱ ነው?
የአብሮነት ታሪክህ የነፃነት ዋጋው፣
ፓን-አፍሪካኒዝም ምንጩና መነሻው፣
ጠይቀህ መርምረህ ታሪኩን እወቀው፣
ኢትዮጵያዊነትህ ለአፍሪካ ኩራት ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2015