የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሃንጋሪዋ ቡዳፔስት ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚካሄድ ይታወቃል። በአትሌቲክስ ስፖርት ትልቅ በሆነው ውድድር ተካፋይ የሚሆኑ ሃገራትም በተወሰኑ ርቀቶች የሚያሰልፏቸውን አትሌቶች በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ሃገራት መካከል የምሥራቅ አፍሪካዎቹ ኬንያ እና ዩጋንዳ ይገኙበታል። በአንጻሩ ሌላኛዋ በመድረኩ ትልቅ ግምት የሚሰጣትና ከምሥራቅ አፍሪካ ውጤታማ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በምትታወቅበት 10ሺ ሜትር ርቀት በተያዘው ወር አጋማሽ የሰዓት ማሟያ ውድድሯን በስፔን የምታከናውን ይሆናል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በ10ሺ ሜትር ርቀት የሚደረጉ ሩጫዎች ከበርካታ ውድድሮች መሰረዛቸው ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሰዓት ማሟያና የአትሌቶች መምረጫ ውድድሩን በሆላንድ ሄንግሎ ሲያከናውን መቆየቱ የሚታወስ ነው። ከዚህ ዓመት አንስቶ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በራሱ አቅም በሃገር ውስጥ እንደሚያካሄድ እና ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 52ኛውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተካሄደበት ወቅት አስታውቆ ነበር።
የሰዓት ማሟያ ውድድሩን በተያዘው ሰኔ ወር 11 ቀን 2015 ዓ.ም፤ በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ስታዲየም ለማድረግም ነበር ያቀደው። ውድድሩ ሃዋሳ የሆነበት ምክንያትም የአዲስ አበባ ከተማ አቀማመጥ በአንጻራዊነት በከፍታ ቦታ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ለአትሌቶች ከባድ ስለሚሆንባቸው ነው። ለዚህም ደረጃውን የጠበቀና በዓለም አትሌቲክስ የተመዘገበ መም በመኖሩ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሞ ነበር።
ይሁንና በቅርቡ ሪፖርተር ጋዜጣ ባስነበበው መረጃ የሰዓት ማሟያ ውድድሩ በድጋሚ ከሃገር ውስጥ ወደ አውሮፓ ሃገር ተዘዋውሯል። በዚህም መሠረት ውድድሩ በመጪው ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡባዊ የስፔን ክፍል በምትገኘው ነርጃ፣ ኤንሪክ ሎፔዝ ኩንካ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል። ለውጡ የተደረገበትን ምክንያት ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም በስፔን የሚገኙ ማናጀሮች ለፌዴሬሽኑ ያደረጉትን ግብዣ ተከትሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከውሳኔ ላይ መድረሱን የተለያዩ መረጃዎች ጠቁመዋል። በመሆኑም በሁለቱም ጾታዎች በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ከሳምንታት በኋላ በስፔን በሚደረገው ማጣሪያ የሚለዩ ይሆናል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ከቀናት በፊት ለማጣሪያ ውድድሩ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባስመዘገቡት ሰዓት መሠረት ለተመረጡ አትሌቶች ጥሪ አድርጓል። አትሌቶቹ ለፌዴሬሽኑ ሪፖርት በሚያደርጉበት ወቅትም ፓስፖርታቸውን ይዘው እንዲቀርቡ በማስታወቂያው የተጠቆመ ሲሆን፤ ይህም ማጣሪያው ከሃገር ውጪ እንደሚሆን ቀደም ሲል ፍንጭ የሰጠ ነበር።
ፌዴሬሽኑ በሁለቱም ጾታዎች ስድስት ስድስት አትሌቶችን እንዲሁም አንድ አንድ ተጠባባቂዎችንም ለማጣሪያው ውድድር ጥሪ አድርጓል። በዚህም መሠረት በሴቶች አትሌት ሚዛን ዓለም ባላት 29 ደቂቃ ከ59ሰከንድ የሆነ ፈጣን ሰዓት በቀዳሚነት የተመረጠች አትሌት ሆናለች። እጅጋየሁ ታዬ፣ ቦሰና ሙላቴ፣ ፋንታዬ በላይነህ፣ ፌቴን ተስፋ እና ጽጌ ገብረሰላማ ለማጣሪያው የተጠሩ አትሌቶች ናቸው። አትሌት ሠናይት ጌታቸው ደግሞ በተጠባባቂነት ወደ ስፔን የምትጓዝ ይሆናል።
በወንዶች በኩል ደግሞ የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮኑ አትሌት በሪሁ አረጋዊ እና የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ ባላቸው ተቀራራቢ ሰዓት በቀዳሚነት ጥሪ የቀረበላቸው አትሌቶች ሆነዋል። አትሌት ታደሰ ወርቁ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ያሲን ሃጂ እና ጭምዴሳ ደበሌም እንደየሰዓታቸው ለማጣሪያው የተጋበዙ አትሌቶች ናቸው። አትሌት ገመቹ ዲዳ ደግሞ በተጠባባቂነት ተይዟል።
በ10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ደግሞ በኦሪጎን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርቀቱ ሻምፒዮን መሆኗን ተከትሎ በቀጥታ ተሳታፊ እንደመሆኗ በማጣሪያው ላይ አትካፈልም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2015