ግርማ ገለልቻ (የአባቱ ስም ተቀይሯል) የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት በሆነበት የሕዝብ ግንኙነት የሙያ መስክ አሥራ ሁለት ዓመታትን በሥራው ዓለም አሳልፏል፡፡ ከዝቅተኛ እርከን ተነሥቶ አሁን በዳይሬክተርነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም የደመወዙ ነገር በደረጃው እንዳይደሰት ምክንያት እንደሆነበት ይሰማዋል፡፡ አንድ ቀን የገጠመው ነገር እስኪፈጠር ድረስ ግን ካለመርካት አልፎ አማራሪና ብስጩ አልነበረም፡፡ ገጠመኙ የሚጀምረው በዳሬክተርነት ደረጃ በሚሠራበት መሥሪያ ቤት ውስጥ ነው፡፡
“እዚሁ ቤት የለውጥ ቡድን ሠራተኛ በሚል የሥራ መደብ የምትሠራ ልጅ ነበረች” ሲል ገጠመኙን መተረክ ሲጀምር ትንፋሹ የሚቆራረጥ ድምጸት አለው፡፡ “ሥራው ምንም ዓይነት ሙያ የማይጠይቅ በትንንሽ ሥልጠናዎች የሚሠራ ነው” እንደ ግርማ ገለጻ ልጅቱ አሥር ሲደመር ሁለት በሚባል ደረጃ የተማረች ናት፤ ሥራዋም በየመደቡ ያሉ ሠራተኞች በየስብሰባዎቻቸው የሚሞሏቸውን ቅጾች ማስሞላትና ለአለቆቿ ማቅረብ ነው፡፡ “ደመወዟ ቢበዛ አራት ሺ ብር ገደማ ቢሆን ነው”
ግርማ ትረካውን ቀጥሏል፡፡ “ታዲያ አንድ ቀን ሥራ ልለቅ ነው ብላ መልቀቂያ ስታዞር አግኝቻት የተሻለ በማግኘቷ ደስ ብሎኝ መልካም ዕድል እንዳልኳት አስታውሳለሁ፡፡ በዓመቱ አንድ ሥልጠና ላይ ድንገት ተገናኘንና ትንሽ ማውራት ቻልን፡፡ አዲሱ መሥሪያ ቤቷ መሬት አስተዳደር ነው፡፡ ስለደመወዝ መጠየቅ ጨዋነት ስለማይመስለኝ ምንም አላወራሁም”
የደመወዙ ነገር እስኪነሣባት ያልጠበቀችው ልጅት ሳትጠየቅ “ጥሩ ይከፈለኛል” ስትል የግርማን ልብ መጎንተል ጀመረች፡፡ ግርማ ራሱን እየነቀነቀ “ጥሩ” በሚል ምልክት ጉንተላውን ለመቋቋም ይሞክራል፡፡ እሷ በዚህ ሳታበቃ “እናንተ ጋ ይከፈለኝ ከነበረው አራት እጥፍ ይከፈለኛል” ስትለው ከእንቅልፍ የሚያነቃ ጥፊ እንደቀመሰ ሰው ብርግግ አለ፡፡ “ወዲያው ደግሞ” ይላል ግርማ “ድንጋጤው እንዳይታወቅብኝ ራሴን ለመቆጣጠር እየሞከርኩ ልክ እንደ ቅድሙ ጥሩ ነው እያልኩ በእርጋታ ራሴን መወዝወዝ ቀጠልኩ” የግርማ መፍዘዝ የጤና ያልመሰላት ልጅት “እንዴ ግርምሽ! አልገባህም መሰለኝ! አራት እጥፍ እኮ ነው ያልኩህ” በማለት ልታነቃው ስትሞክር ውስጡ እየደማ የተለጎመ አፉ “ጥሩ ነው” ከሚል ቃል ውጪ ምንም ሊወጣው አልቻለም፡፡
“ምንም እንዳልመሰለኝ ሆኜ ለመታየት ብሞክርም ከዚያ ቅጽበት በኋላ መንፈሴ ሥልጠናው ውስጥ አልነበረም፡፡ አካሌ አዳራሹ ውስጥ ቢሆንም መንፈሴ ግን ደመወዜና ደመወዟ ላይ ነበር፡፡ እቤት ገብቼም የተጣባኝ ሐሳብ አልፋታ አለኝ” የሚለው ግርማ “ምንድነው ነገሩ! እኔም የመንግሥት ሠራተኛ፣ ‹መሬት አስተዳደር› ተብየውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከእኔ በትምህርት ደረጃም ሆነ በሥራ ልምድ አራት እጥፍ የምታንስ ሠራተኛ ደመወዟ ከእኔ እጥፍ የሚሆነው በምን አመክንዮ ነው?”
ግርማ ነገሩ ምን ያህል እንደከነከነው በትረካው ጊዜ ከሚታይበት መብከንከንና ፊቱ ላይ በግልጽ ከሚነበበው ቁጭት ያስታውቃል፡፡ የግርማ ይህን ያህል መብከንከን የሚገርም አለመሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ለሠራተኞች ከደመወዝ በላይ ስሱ ነገር እንደሌለ የዓለም ሠራተኞች ተቋም ያረጋገጠው ከመሆኑም በላይ በደመወዝ የተነሣ ማንም ሠራተኛ በደል እንዳይደርስበት ለማድረግ ዓላማው አድርጎ እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሰው ሐብትና ሒሳብ ክፍል ልዩ ትኩረት የሚያደረገውም ደመወዝ ላይ ነው፡፡ ደመወዝ በስሕተት እንዳይቀናነስ ብቻ ሳይሆን ከሚከፈልበት ዕለት አንዲት ቀን እንዳይዘገይ ብርቱ ጥንቃቄ እንደሚደረግ የሰው ሀብት ባለሙያዎች ይገልጣሉ፡፡
ይህን ያህል ስሱና ቀልብ ቆንጣጭ የሆነው ደመወዝ ግርማን ያንገበገበውን ያህል ሌሎችንም እያንገበገበ ጉዳዩ የጋራ አጀንዳ ሆኗል፡፡ እኩል ደረጃ ይዘው በአንድ መንግሥት ሥር ባሉ የተለያዩ ተቋማት ደመወዝ ለምን ይለያያል? ከዚያም አልፎ ያነሠ ደረጃ ይዘው ሳለ የተመረጡ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የመቀጠር ዕድል የሚያገኙ ሰዎች የበለጠ የትምህርትና የሥራ ደረጃ ካላቸው ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ለምን የበለጠ ደመወዝ ያገኛሉ? የሚሉ ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ ሳያገኙ ዓመታት አልፈዋል፡፡
ግርማ ኢፍትሐዊው የደመወዝ ስኬል የሥራ ተነሳሽነቱን እንደጎዳበት ይገልጻል፡፡ “በፊት ደመወዜ ከኑሮዬ ጋር አልጣጣም አለኝ ብዬ ከማሰብና አማራጭ ገቢዎችን በትርፍ ሰዓቴ ለመጨመር ከማሰብ በቀር ሥራዬን በፍቅር ነበር የምሠራው፤ አሁን ግን የመበደል ስሜት ስለሚሰማኝ ሥራዬን እየጠላሁት ነው” ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ኢዮብ ኀይሉ “በደመወዝም ሆነ በሌላ መንገድ የሚደረግ የገንዘብ ጭማሪ ሠራተኛን የማነቃቃት አቅሙ በጣም ጊዜያዊ ነው፤ ሰው ማኅበራዊ ፍጡር በመሆኑ ገንዘብን እያሰበ ዘወትር ትጋቱን ሊጨምር እንደማይችል በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ሰው ራሱን ከሌሎች አንጻር የመመልከት ፍላጎት ያለው ማሕበራዊ ፍጡር ስለሆነ ከሌሎች ማነሡ ወይም በሌሎች እንደ ደካማ መቆጠሩ ይቆጨዋል፡፡ በተመሳሳይም በሌሎች ተቀባይነት የማግኘት፣ የመከበርና ከተቻለም በልጦ የመገኘት ፍላጎቱ ነው ሊያተጋው የሚችለው” በማለት ከተነተኑ በኋላ “ከዚህ አንጻር ካየነው የደመወዝ ጭማሪ ትጋትንና ምርታማነትን የመጨመር አቅሙ ዝቅተኛ ቢሆንም ፍትሐዊ ያልሆነ የደመወዝ ስኬል ግን በሠራተኞች ስሜት ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ሠራተኛውን የሚጎዳው የገንዘቡ መጠን ሳይሆን ራሱን ከሌሎች ጋር አነጻጽሮ ራሱን የሚያገኝበት የዝቅተኝነት ቦታ ነው” ሲሉ ንድፈ ሐሳቡን ከተነሣው ተጨባጭ የደመወዝ እኩልነት ጥያቄ ጋር ያዛምዳሉ፡፡
የመምህሩን ትንተና አረጋጋጭ የሚመስል ታሪኮችን የተለያዩ ሰዎችን ሳነጋግር አግኝቻለሁ፡፡ በአንድ ዓመት በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ የተመረቁ ወጣቶች እንደ ዕድላቸው መሬት አስተዳደር፣ ገቢዎች አስተዳደር፣ ዋና ኦዲተር ቢሮ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚንስቴር ተቀጥረው በዓመቱ ቢገናኙ በመካከላቸው ሰፊ ልዩነት ይገኛል፡፡ ዋና ኦዲተር ቢሮ የሚሠራ አንድ ባለሙያ እንደገለጸልኝ “ከሥራ ጫና አንጻር ካወዳደርክ ከበድ ያለ ሓላፊነት የተጫነብኝ እኔ ነኝ፤ ሥራውም ከፍተኛ ብቃትና ድካምን ይጠይቅብኛል፡፡ ደመወዜ ግን ከሁሉም ጓደኞቼ በታች ነው፡፡ እነሱ ዘና ብለው እየዋሉ አሪፍ ደመወዝ ይከፈላቸዋል፡፡ እኔ በየመሥሪያ ቤቱ ‹ስጠገረር› እየዋልኩ የደመወዜን መጠን ለመናገር አፍራለሁ”
ይህ ወጣት ባለሙያ አሁን ባንክ ለመቀጠር ማስታወቂያ እየጠበቀ መሆኑን የነገረኝ ሲሆን የባንኩ ቅጥር ከተሳካለት ብቻ እረፍት እንደሚያገኝ አልደበቀኝም፡፡ “የሚገርምህ እኮ፣ በደመወዝ የበለጡኝ ጓደኞቼ የግል ካምፓኒ ወይም ‹ኤንጂኦ› ተቀጥረው ቢሆን ያም ባይሆን የመንግሥት አትራፊ [የልማት] ድርጅት ውስጥ ሠርተው ቢሆን ችግር አልነበረውም፡፡ የሚያናድደው እኩል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሠርተህ ደመወዝህ ሲለያይ ነው”
የደመወዝ ነገር እንቅልፍ የነሣው ግርማ የልዩነቱን መንሥዔ ለማጣራት ሞክሮ ያገኘው መልስ ደግሞ የባሰውን አግራሞት አጭሮበታል፡፡ ብዙዎቹ እንደሚሉት የደመወዝ ስኬላቸው ከሌላው ‹‹ሲቪል ሰርቫንት›› በተለየ መልኩ ከፍ ያለላቸው መሥሪያ ቤቶች ለሙስና የተጋለጡ ስለሆነ በባለሥልጣናት አነጋገር “ኪራይ በስፋት የሚሰበሰብባቸው” ስለሆኑ ሠራተኛው ከሙስናው እንዲቆጠብ ለማድረግ በሚል የተደረገ እንደሆነ ይነገራል፡፡ “ይህ በጣም የሚያስቅ ሰበብ ነው” ይላል ግርማ፡፡ “አረ ለመሆኑ ለሙስና ያልተጋለጠ መሥሪያ ቤት የትኛው ነው? መሬት ብቻ ነው እንዴ ሙስና የሚሠራበት? መሬት አስተዳደርን ኦዲት የሚያደርገው መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ሙስና መሥራት ቢፈልጉ የበለጠ አይሞስኑም?”
በሌላ የዘገባ አጋጣሚ ያገኘኋቸው የዋና ኦዲተር ሠራተኞች እንደ መሬት አስተዳደር ያሉ መሥሪያ ቤቶችን ሲመረምሩ በጣም የሚያሸማቅቃቸው የደመወዙ ነገር መሆኑን ገልጸውልኛል፡፡ “ኦዲተሩ ምጽዋት የምታክል ደመወዝ ተከፋይ ሲሆን በተመርማሪው መሥሪያ ቤት ያሉ ሠራተኞች ደግሞ መለስተኛ ከበርቴዎች ሆነው ይገኛሉ፤ ለዚህ ብቸኛው መድኃኒት ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ እንደምንም ባንክ ወይም ኢንሹራንስ ሥራ አግኝቶ እብስ ማለት ነው፤ አለበለዚያ ኦዲት ባደረጉ ቁጥር በሰው ደመወዝ ሲቃጠሉ መኖር ነው” ያለኝም አለ፡፡
ቃለ መጠይቅ ተደራጊዎች ባብዛኛው እንደመሰከሩት ደመወዛቸው ስለበዛላቸው ተደስተው ከሙስና የራቁ ሠራተኞች ብዙ አይደሉም፡፡ “በመደበኛ ሥራቸው ላይ ሆነው በጎን ለሚከፍሏቸው ባለጉዳዮች የወረፋ ቅድሚያ ከመስጠት ጀምሮ ከግብር ጋር የተያያዘ ተጨማሪ ሥራዎችን እየሠሩ የሚጠቀሙ ሞልተዋል” ይላሉ፡፡ አንድ መረጃ ሰጪ እንዳለው የተመረጡ መሥሪያ ቤቶች በደመወዝ ከፍ እንዲሉ መደረጋቸው “ላለው ይጨመርለታል” እንደሚባለው ከትርፍ ሰዓት ሥራዎችና ከመደበኛው ሥራቸው ጋር ጎን ለጎን ከሚሠሩት ‹‹ቢዝነስ›› ተጨማሪ እንጂ ሙስናውን የሚያስቀር ሆኖ አላየንም”
ይህ ልዩነት የተከሰተበትን ምክንያትና መፍትሔውን በተመለከተ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ለማነጋገር ሞክሬ ነበር፡፡ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመጀመሪያ የስልክ ግንኙነት መሥሪያ ቤታቸው መረጃ የሚሰጠው በደብዳቤ ሲለመን ብቻ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ በተከታታይ ላደረግነው ሙከራ ስልክ ባለመመለስ ራሳቸውን ዝግ አድረገውብናል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ቢሮም በቀጠሮ ሲያመላልሰኝ ቆይቶ በመጨረሻ የቢሮው ምክትል ሓላፊ አቶ መልካሙ ዘሪሁንን አገኘኋቸው፡፡ ሓላፊው ማን እንደሆንኩና ለምን እንደመጣሁ ስነግራቸው እንደ መበሳጨት አደረጋቸውና የኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰሯን “ለምን አመጣሽብኝ” ሲሉ ተቆጡ፡፡ የመጣሁት ራሴ መሆኔንና በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሐሳብ ብቻ ባጭሩ ከነገሩኝ እንደሚበቃ አስረዳሁ፡፡ “ጉዳዩ ገና በሒደት ላይ ያለ ስለሆነ መረጃ ልሰጥ አልችልም” አሉ፡፡ “የደረሰበትን ደረጃም ቢሆን ቢነግሩኝ መልስ ይሆነኛል” አልኳቸው፡፡ “እሱንም ቢሆን ከዋና ሓላፊዋ ጋር ተወያይቼ ሲፈቀድ ነው” የሚል አዲስ ማፈግፈጊያ አመጡ፡፡ “እንግዲያውስ ዋና ሓላፊዋን ያገናኙ” ስል ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰሯን ጠይቄ ወደ ሌላ ቢሮ አመራን፡፡
የዋና ሓላፊዋ ቢሮ ስንደርስ በየት በኩል እንደቀደሙኝ ሳላውቅ ምክትል ሓላፊው አቶ መልካሙ ቢሮው ውስጥ ሲንጎማለሉ ደረስኩ፡፡ ለጥያቄዬ “ዋና ሓላፊዋ ዶክተር ፍሬ ሕይወት ገብረ ሕይወት አሁን ወጡ” በማለት ጸሐፊያቸው መልስ ሰጡኝ፡፡ ምክትል ሓላፊውም መረጃ ሊሰጡኝ እንደማይችሉ በድጋሚ አረጋግጠውልኝ ወጡ፡፡ ‹እዚያው ጊቢ ውስጥ ናቸው› የተባሉት ዋና ሓላፊዋም ከአንድ ሰዓት በላይ ብጠብቃቸው አልተመለሱም፡፡
ይህን ያህል አስፈሪ የሆነው ጉዳዩ ‹የደመወዝ ነገር› ስለሆነ ይሆን? እያልኩ በማብሰለስልበት ሰሞን ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ በምክር ቤት ተገኝተው ነገሩን እያብራሩ መልስ ሰጡበት፡፡ አጋጣሚው እያስገረመኝ ባለሙያዎቹና የሚመለከ ታቸው ሓላፊዎች የፈሩትን የደመወዝ ጉዳይ በጠቅላይ ሚንስትሩ ቃል ከማሳረግ ውጪ የተሻለ መደምደሚያ አይኖርም ስል አሰብኩ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ ጥቅምት 8 ቀን 2011ዓ.ም በምክር ቤት ተጠይቀው ሲያስረዱ የጀመሩት ‹ጄኢጂ› በመባል የሚታወቀውን ጥናት ምንነት በማስረዳት ነው፡፡ ጥናቱን የደመወዝ ጭማሪ ብሎ መተርጐም ትክክል እነዳልሆነ ጠቁመው የጥናቱ ዓላማ የመንግሥት ሠራተኞች አንድ ዓይነት ደረጃ ይዘው የተለያየ ደመወዝ የሚያገኙ መሆናቸውን ለማስቀረትና እኩል ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸው ደመወዝ እኩል አለመሆኑ ያስከተለውንም ችግር “የተረጋጋ የሥራ ከባቢ እንዳይኖር አድርጓል፤ የሠራተኞች ፍልሰት እንዲጨምርም ምክንያት ሆኗል” ሲሉ አስረዱ፡፡
“የሆነ ሆኖ የደመወዝ ጥያቄ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ የሆነ የገቢ ማነስና የኑሮ ውድነት አለ፤ የቤት ኪራይ በየጊዜው እየጨመረ ነው፤ የምግብና ትራንስፖርት ወጪዎች እየጨመሩ ስለሆነ ሠራተኞች ይቸገራሉ” በሚል የችግሩን ስፋት ሕዝቡ ውስጥ ገብተው እንዳዩት በሚመስል መጠን ገልጸው ችግሩን የተገነዘበው መንግሥት የደመወዝ ማስተካከያውን ተግባራዊ እንዳያደርግ የከለከሉትን ዐበይት ምክንያቶች እንደሚከተለው አስረዱ፡፡
የጄኢጂ ደመወዝ ማሻሻያ ጥናት ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ብሎ ያቀረባቸው አማራጭ የጭማሪ መጠኖች አሉት፡፡ ዝቅተኛ የተባለው ጭማሪ ሰላሳ ሰባት ቢልዮን ብር የሚጠይቀን ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ ከመቶ ቢልዮን ብር በላይ ይጠይቃል፡፡ “ይህንን እንዳናደርግ ደግሞ ከፍተኛ የበጀት ጫና አጋጥሟል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት በሚልዮን የሚቆጠር ሰው ሲፈናቀል ለመጠባበቂያ የያዝነውን ሀብት ወስዶብናል”
ከዚህ ቀደም በድርቅ ምክንያት ሲታገዙ የነበሩ ሰዎች አሁንም እየታገዙ መሆኑ፣ መንግሥት ገቢ የመሰብሰብ አቅሙን አለማሳደጉ የፈጠረው የበጀት ክፍተት፣ ከውጪ አበዳሪ ተቋማትና አገሮች የተቀበልነውን ዕዳ እንድንከፍል የሚደረግብን ጫና፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ የፈጠሩትን የበጀት ጫና አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ወቅት አገሪቱ የገባችበት የገንዘብ ጫና በመዘርዘር ሳይወሰኑ ተስፋዎቹንም ጠቁመዋል፡፡ “ባለፉት ወራት የምግብ ዋጋ ግሽበት እየቀነሰ ነው፤ በዚህ ከቀጠለ በጣም ጥሩ ይሆናል” ካሉ በኋላ “የደመወዝ ጭማሪ ካደረግን እንደገና ዋጋ ግሽበቱ ይጨምርና ደመወዝ የተጨመረላቸውን ጨምሮ የሚጎዳ ይሆንብናል” ሲሉ ደመወዝ ጭማሪ ከሚያስገኘው ጊዜያዊ ደስታ ውስጥ የተደበቀ አደጋ እንዳለ ሠራተኛው ሊያስታውስ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ መሠረት ባለፈው ዓመት በነበረው አገራዊ ቀውስ ምክንያት የመጠባበቂያ በጀቱ በጣም ዝቅተኛ ከሚባልበት ደረጃ በመውጣት አሁን ቢያንስ “ተቀባይነት ያለው” የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም የተነሣ ማክሮ ኢኮኖሚው እያገገመ ይገኛል፡፡ ሙሉ በሙሉ አገግሞ እስኪስተካከል ድረስ የደመወዝ ማሻሻያ ማድረግ የባሰ ቀውስ መፍጠር ይሆናል፡፡ ከተረጋጋ በኋላ ግን የደመወዝ ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው ተገቢ ጥያቄ ስለሆነ ልንመልሰው ግዴታ ይሆናል፡፡ እስከዚያው ግን ዜጎች ጉዳታቸውን ችለው፣ በተሻለ ብቃት ሊሠሩና ይህን የለውጥ ጊዜ ሊያሸጋግሩ ብሎም ለውጡ እንዳይቀለበስ ሊያደረጉ ይገባል የሚል የመሪነት ሐሳባቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጠቅላይ ሚንስትሩ ሐሳብ ተስፋ የሚያጭር እንደሆነ ያነጋገርኳቸው ሠራተኞች ነግረውኛል፡፡ “በዚህ ዓመት ሊሆን እንደማይችል እውነታውን መስማት ራሱ አንድ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ያለፉትን ዓመታት የቆየነው ‹በዚህ ዓመት ይተገበራል› በሚል የፖለቲከኞች ሐሰተኛ ማባበያ ነበር” ይላል ግርማ፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ ሐሳብ ትክክለኛ መሆኑን ያመነው ግርማ የተሻለ ደመወዝ የሚያበላውን ሥራ ማፈላለጉን ሳይተው እስከዚያው የያዘውን በተሻለ ተነሳሽነት ለመሥራት የሚያስችል ስሜት እንደተፈጠረበት ይናገራል፡፡
ዘመን መፅሄት ጥቅምት 2011
ዳዊት አብርሃም