የኢትዮጵያ እጅ ኳስ 7ኛ ዓመት የክለቦች ፕሪሚየርሊግ የማጠቃለያ ውድድር በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በጠንካራ ፉክክሮች ታጅቦ በመካሄድ ላይ ይገኛል:: የማጠቃለያ ውድድሩ በመጪው ሰኔ 3/2015 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል::
ሁለተኛ ዙር የ2015 ዓ.ም የእጅ ኳስ የክለቦች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ከ15ኛ እስከ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከግንቦት 26/2015 ዓ.ም ጀምሮ በጠንካራ ፉክክሮች በትንሿ ስታድየም ቀጥሏል:: ስምንት ክለቦችን እያፋለመ የሚገኘው ይህ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዓመቱን በሙሉ ጠንካራ ፉክክር እያስተናገደ መጠናቀቂያው ላይ ደርሷል:: ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ መቻል፣ ኦሜድላ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤት፣ ከምባታ ዱራሜ፣ ባህርዳር ከነማ እና ፋሲል ከነማ እጅ ኳስ ክለቦችን እያፋለመ ይገኛል::
በውድድሩ መክፈቻ እለት በተደረጉ ጨዋታዎች ፌደራል ማረሚያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና መቻል ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወሳኝ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል:: ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ትላንትና እና ከትላንት በስቲያም ጨዋታዎች ቀጥለው ሲካሄዱ የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል:: ከትላንት በስቲያ በተደረጉ ግጥሚያዎች ፌደራል ማረሚያ ፋሲል ከነማን፣ መቻል ባህርዳርን በመርታት ድል ተቀዳጅተዋል:: ትላንት ቀጥሎ በተደረጉት ጨዋታዎችም እንዲሁ ኮልፌ ቀራኒዮ ከምባታ ዱራሜን ቂርቆስ ኦሜድላን ማሸነፍ ችለዋል:: ፕሪሚየር ሊጉን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ30 ነጥብና 162 ግቦች አንደኛ ሆኖ ሲመራ መቻል እጅ ኳስ ክለብ በተመሳሳይ ነጥብ በጎል ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፤ ባህርዳር ከተማ ደግሞ በ18 ነጥብ ሶስተኛ ነው::
የማጠቃለያ ውድድሩ ለአንድ ሳምንት ገደማ የሚቆይ ሲሆን በቆይታውም በሚከናወኑ ውድድሮች የሊጉ አሸናፊ የሚለይበት ይሆናል:: ተወዳዳሪ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች እያሳዩ ባለው ጠንካራ ፉክክር አንገት ለአንገት ተናንቀው በጠባብ ውጤት መሸነፋቸው በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ማን ቻምፒዮን ይሆናል የሚለው ጉዳይ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጓል:: በዚህ መሰረት ውድድሩ ፈጣንና ጉልበትን የሚጠይቅ እንዲሁ እጅግ ማራኪ ጨዋታን በመጫወት ተመልካቹን ቁጭ ብድግ እያደረገ ቀጥሏል:: እስከ አሁን የሊጉ አሸናፊ ክለብ ባለመለየቱ እስከ መጨረሻው ዕለት ክለቦች በከፍተኛ ፉክክር እንደሚቀጥሉም ይጠበቃል::
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ፣ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ እየተካሄደ ያለበትን ሁኔታ ሲያብራሩ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ክለቦች ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ:: ካለፈው ዓመት የተሻለ ቴክኒክና ታክቲክ፣ ጥሩ እንቅስቃሴ፣ ጥሩ ጨዋታዎች መታየት እንደቻሉም አቶ ሞላ ተናግረዋል:: ይኸውም በሊጉ የክለቦች ነጥብ ተቀራራቢ እንዲሆንና ከላይ ያሉ ክለቦች እኩል ነጥብ ይዘው በጎል ክፍያ ብቻ ተበላልጠው ሊጉን እንዲመሩ አድርጓል::
እንደ አቶ ሞላ ገለጻ፣ ለፉክክሩ ጠንካራ መሆን የክለቦቹ ከፌዴሬሽኑ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት ዋንኛው አነቃቂ ጉዳይ ነው:: በዚህም ከፍተኛ የሆነ ልምድና ተሞክሮ ሊወሰድበት ተችሏል:: የተሳትፎ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የተሻሉና ጠንካራ ችሎታ ያላቸው፣ ብሔራዊ ቡድንን መወከል የሚችሉ በርካታ ተጫዋቾች እየወጡበት ያለ መድረክ ሊሆንም ችሏል:: በአጠቃላይ እየተካሄደ ያለው ውድድር ኢትዮጵያ በየትኛውም ውድድር መሳተፍ እንድትችል የሚያደርግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝም አክለዋል::
ፕሪሚየር ሊጉን የሚያሸንፈው ክለብ ዋንጫና ሜዳሊያ ከመውሰዱ የዘለለ ጥቅም ባያገኝም በአፍሪካ ደረጃ በሚካሄዱት የክለቦች የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድሮች ተሳትፎን እንደሚያደርግ ተገልጿል:: ፌዴሬሽኑ ለአሸናፊዎች ሽልማት ጠቅላላ ጉባኤው በሚወስነው መሰረት እንደሚሰጥም ጠቁሟል::
ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ እረፍት አድርጎ ነገ በሶስት ጨዋታዎች የሚቀጥል ይሆናል:: በዚህም መሰረት ፋሲል ከነማ ከከምባታ ዱራሜ፣ ኦሜድላ ከፌደራል ማረሚያ እና የሊጉ መሪ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ከሚገኘው ባህርዳር ከነማ ይጫወታሉ:: ዓርብ እንዲሁ በአንድ ጨዋታ ሲቀጥል፤ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፋሲል ከነማ ይጫወታሉ:: ቅዳሜ ሰኔ 3 በመዝጊያው ዕለት ሁለት ጨዋታዎችን በማድረግ ፍጻሜውን የሚያገኝም ይሆናል:: ባህርዳር ከነማ ከፌደራል ማረሚያ እና ኦሜድላ ከከምባታ ዱራሜ በሚያደርጉት ጨዋታም የ2015 ዓ.ም የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሚጠናቀቅ ይሆናል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2015