
ሳዑዲ አረቢያ ከነዳጅ ምርቷ በቀን አንድ ሚሊዮን በርሜል እቀንሳለሁ ማለቷን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ። ሌሎች የዓለማችን ነዳጃ አምራች አገራትም በተመሳሳይ የነዳጅን ዋጋን ለማረጋጋት በማሰብ የምርት አቅርቦታቸውን ለመቀነስ ተስማምተዋል።
ሳዑዲ አረቢያ በቀጣዩ ሐምሌ ወር በየቀኑ አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከምርት አቅርቦቷ ላይ እንደምትቀነስ የገለጸች ሲሆን የነዳጅ ላኪዎች ሀገራት ማህበር ወይም ኦፔክ+ እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ዕለታዊ የነዳጅ አቅርቦት በአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በርሜል እንደሚቀንስ ገልጿል። ኦፔክ+ የዓለምን 40 በመቶ የነዳጅ ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን ውሳኔው በዓለም የነዳጅ ምርት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል።
የሳዑዲን ውሳኔ ተከትሎ በእስያ ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በሁለት ነጥብ አራት በመቶ አሻቅቦ በበርሜል 77 ዶላር ሆኗል። በሩሲያ የተመራውና 7 ሰዓታት የፈጀው ስብሰባ እያሽቆለቆለ ለመጣው የነዳጅ ዋጋ መፍትሄ ለመስጠት ያለመ ነው። የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንድር ኖቫክ እንደገለጹት ከሆነ ኦፔክ+ የምርት አቅርቦቱን ለመቀነስ ከወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ከእለታዊ ምርቱ ሶስት ነጥብ 6 ሚሊዮን ነዳጅ ምርት መቀነስ ችሏል።
የኦፔክ አባል ሀገራት እና አጋሮቻቸው ዕለታዊ የነዳጅ አቅርቦታቸውን በሁለት ሚሊዮን በርሜል ለመቀነስ ቀደም ብለው ተስማምተው ነበር። ይህ ምርት የዓለም የነዳጅ ፍላጎትን በሁለት በመቶ የሚቀንስ ነው። አዲሱ ውሳኔ ቀደም ብሎ የነበረውን እስከ ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ያራዘመ መሆን የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ገልጸዋል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር የዕለታዊ የነዳጅ ምርትን በአንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን በርሜል ለመቀነስ የተስማሙ ሲሆን ውሳኔው ከባለፈው ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ታስቦ ነበር። የሳዑዲ ኢነርጂ ሚንስትር ልዑል አብዱላዚዝ ቢን ሰልማን የነዳጅ ምርት አቅርቦቱን የመቀነሱ ውሳኔ አስፈላጊ ከሆነ ከሐምሌም በኋላ ሊራዘም ይችላል ብለዋል። ውሳኔውም የዓለም የነዳጅ ዋጋን እንደሚያረጋጋ ገልጸዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት የነዳጅ አምራች ሀገራት በነዳጅ ዋጋ አለመረጋጋት እየተፈተኑ ነው። ምዕራባውያኑ ኦፔክ+ የነዳጅ ዋጋን በማሻቀብ ዋጋን ባልተገባ ሁኔታ ለመቆጣጠር እንዲሁም የዓለም ኢኮኖሚን ቸል እያለ ነው ሲሉ ይከሳሉ። በተጨማሪም ማህበሩ ሩሲያ ዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት ከተጣሉባት ማዕቀብ በተቃራኒ ይወግኑላታል ሲሉም ይወቅሳሉ።
በምላሹ የኦፔክ ውስጥ አዋቂዎች ባለፉት አስርት ዓመታት የምዕራባውያን የገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ንረት እንዲከሰትና ዋነኛ የኤክስፖርት ምርታቸው በሌሎች እንዲወሰን እያደረጉ ነው ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015