በቴሌቪዥን መስኮት ምስል የመመልከት ሃሳብ ገና በሀገራችን ሳይጸነስ፣ በሬዲዮ ሞገድ እንኳን ድምጽ መስማት ብርቅ ከመሆን አልፎ እንደ ተአምር ይቆጠር ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ለሕዝብ መረጃ በማድረስ ብቸኛው ባለውለታ አዲስ ዘመን ነበር።
የኢትዮጵያ የነጻነት ድል ብስራት አብሳሪ ሆኖ ብቅ ያለ ዘመን ተሻጋሪ ሚዲያ አዲስ ዘመን ነበር። የኢትዮጵያ የነጻነት ጎህ የወራሪውን ምኞት ቀዶ ንጉሱም በማግስቱ አሃዱ ብለው ዳግም ሲጀምሩ የመጀመሪያዋ ሃረግ አዲስ ዘመን ነበረች። ይሄው ዛሬም ሃረጉ ሳይበጠስ እንደስሙ አዲስ እንደሆነ አለ። በመላው ኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያልረገጠው መሬት ያልዳሰሰው እውነታ የለምና መለስ ብለን እነዚህን እውነታና ክስተቶች እንቃኛቸዋለን። በ60ዎቹ መገባደጃ ከወጡት መረጃዎች መካከል የተመራረጡን እንዲሁም ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ከሆነው ‘ሰዎች ምን አሉ?’ ከተሰኘው ገጽ ላይ አንዲት መረጃ በማከል እናስታውሳቸው፡፡
ትእዛዙን ማን ሰጠው?
የኢንዶ ጨርቃ ጨርቃ ፋብሪካ የአንድ ሰው ንብረት የነበረበትንና በረጅም ጊዜ ውል ተከራይቶ ሲጠቀምባቸው የቆየውን ቤቶች ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም የከተማን ቦታና ትርፍ ቤት የመንግስት ባደረገው ዓዋጁ መሠረት ለማስረከብ ፍቃደኛ ሆኖ ባለመገኘታቸው ርክክቡም እንዳይፈጸም ግልጽ ያልሆነ ተፅዕኖ በማድረግ ላይ በመሆኑ በአቃቂ ወረዳ በበሰቃ ከተማ የ08 ቀበሌ የከተማ ነዋሪዎች የህብረት ስራ ማህበር ችግር የገጠመው መሆኑን የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ጌታነህ ደሰኛው አስታወቁ።
በአሁኑ ጊዜ በዚሁ ቀበሌ ሆነ በአቃቂ ከተማ በደረሰው የቤት እጥረት በርከት ያሉ የመንግስት ሠራተኞች አልቤርጎ ተከራይቶ ከመኖራቸውም ሌላ በቅያሬ ወደ ወረዳዉ የሄዱት የፖሊስ ሰራዊት አባሎች በጣቢያው ውስጥ አልጋ ዘርግቶ እንደሚኖሩ የቀበሌው ማህበር ገልጦ፣ የእነዚህ ባዶ ቤቶች ርክክብ ቢከናወን የደረሰውን የቤት እጥረት ችግር ለማቃለያ እንደሚረዳ አስረድቷል።
የኢንዶ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካም ቤቶቹን ባለማስረከቡ የቀበሌው ስራ እስኪያጅ ኮሚቴ አባሎቹ አዋጁን በትክክል በስራ ላይ እንዲያውል አላደረጋቹህም በሚል ከቀበሌው ኗሪዎች ዘንድ ተቃውሞ መደረጉን ሊቀመንበሩ ጨምሮ ገልጸዋል። ለጉዳዩ መነሻ የሆነው በቀበሌው ክልል ውስጥ የሚገኘው የቀድሞ የመኮንን ኃይልሥላሴ ቤትና ቦታ የነበረውን የኢንዶ ኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሐምሌ 1 ቀን 1953 ዓ.ም በመንግስት ንብረት መስሪያ ቤት በኩል በተፃፈ ውል ቀድሞ ለተሰሩት ቤቶች በየወሩ 300 ብር ሊከፍሉና በቦታውም ላይ በጊዜው ለነበሩት የውጭ ሀገር ዜጎች ማረፊያ ቤት ለመስራት እንዲችል ስምምነት አድርጎ ነበር።
(አዲስ ዘመን ታኅሳስ 24 ቀን 1967ዓ/ም)
በአድኅርያን ተንኮል የተጣሉ ሶስት ጎሣዎች በዘማቾች ጥረት ታረቁ
በሸዋ ክፍለ ሀገር በየረርኔ ከረዩ አውራጃ በአድአ ወረዳዎች በሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ በቦራ ወረዳ ሕዝቦች መካከል አድርኅያን በፈጠሩት ተንኮል በጎሳ ልዩነት ተጣልተው የነበሩ የሶስት ወረዳ ሕዝቦች በዘማቾች ከፍተኛ ጥረት ባለፈው እሁድ ታረቁ።
ቁጥራቸው ወደ አራት መቶ የሚጠጋው የሶስቱም ወረዳዎች ሕዝብ ተወካዮች ባለፈው እሁድ አማካኝ በሆነው ስፍራ ላይ ተገናኝተው ገለልተኛ በሆነው የሀገር ሽማግሌዎች በዘማቾች አማካኝነት በአካባቢው ሕዝብ ባህል መሰረት ሁለተኛ በጠብ ላለመፈላለግና በአንድነትና በፍቅር ለመኖር እጆቻቸው መሬት በመያዝ በአዋሽ ወንዝ ዳር ተማምለው ስምምነት አድርገዋል። እንዲሁም በአድኅርያን ተንኮል ሕዝቡን ያጋጩና ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በገበሬ ማህበራት አማካይነት በመጠቆምና በመያዝ ለህግ ለማቅረብ ከሁለቱም ወገን 5 5 ተወካዮች በሕዝቡ ስም ስምምነት ፈርመዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄደው አብዮት ጥቅማቸው የተነካባቸው በቀድሞ ጉልበተኞችና ባላባቶች ሰፊውን አፈር ገፊ ገበሬ ለመለያየት በጠነሰሱት ተንኮል የሎሜና የአድአ ወረዳ ሕዝብን ከቦረና ወረዳ ሕዝብ ጋር ጎሣ ልዩነት የተመሰረተ ግጭት ፈጥረው እንደነበር ታውቋል። (አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 1968ዓ/ም)
አሻጥረኛ ነጋዴ በሕዝብ ተጋለጠ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
በአዲስ አበባ ከተማ በልደታ ወረዳ የ04 ቀበሌ ነዋሪዎች ባለፈው እሁድ ባደረጉት ጠቅላላ ስብሰባ ለሕዝብ ደህንነትና የፅዳት ቁጥጥር ሥራ ለሚቀጠሩ ሰዎች የቀበሌው ነዋሪዎች እንደየአቅማቸው በየወሩ ቋሚ መዋጮ ለማድረግ ወሰነዋል።
በዚህ ዕለት አንድ የቀበሌው እህል ነጋዴ የተደጋገመ ጥፋት በመፈጸማቸው የቀበሌው ፍርድ ሸንጎ በወሰነው መሰረት በጠቅላላው ስብሰባ ላይ ቀርቦ ጥፋታቸውን በመግለጽ ሁለተኛ አይለመደኝም በማለት ላለፈው ጥፋታቸው ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል። ባለፈው ክረምት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያወጣውን የዋጋ ተመን አስበልጠው በመሸጣቸው ተከሰው አንድ መቶ ብር የተቀጡት አቶ ፉሌ ቢርመጂ የተባሉት እኚሁ ነጋዴ አሁን ደግሞ እንደገና ግልፅና ስውር አሻጥር መፈጸማቸውን እራሣቸውም ከማመናቸውም በላይ የቀበሌው ሊቀመንበር ድርጊቱን ለስብሰባው በዝርዝር ገልጸዋል።
(አዲስ ዘመን ታኅሳስ 13 ቀን 1967 ዓ/ም)
ሰዎች ምን ይላሉ?
አንዳንድ አዝማሪዎች የባህል ቅርስ የሆኑትን አንዳንድ ዘፈኖችን መሰረታቸውን በማስለቀቅ ያለአግባብ ሲጠቀሙበት ይታያሉ። ለምሳሌ መሐሙድ አህሙድ “ሳምራ” የተባለውን የሴት ዘፈን ሰሞኑን መዘፋፈን ጀምሯል። ዘፈኑን በሠርግ ጊዜ ሴቶች የሚያዜሙት እንጂ የወንድ ልጅ ሎጋው ሽቦ ስላልሆነ በባህል ቅርስነቱ በኩል ቢታሰብበት መልካም ነው። ከዚሁ ዘፈን አንድ ግጥም ብጠቅስ “ራሴን ያመኛል ሐርሻሽ ይለኛል” ይላል። ታዲያ ወንድ ልጅ ከመቼ ወዲ ነው ሐርና ሻሽ መምረጥ የጀመረው?
አበራ ለማ
(አዲስ ዘመን ታኅሳስ 13 ቀን 1968ዓ/ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015