ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ይህ ደግሞ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የሚታወቅ ነው፡፡ ታዲያ ይህ በጦርነት የተጎዳው ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ምን ሊደረግ ይገባል፤ የመፍትሄ አማራጮችስ ምንድን ናቸው በሚለው ላይ የዘርፉ ምሁራን ሃሳባቸው ይሰጣሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ሊደር ሺፕ የዶክተሬት ትምህርታቸውን በመከታተል የሚገኙትና በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ ታምራት መንገሻ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በጦርነት የተጎዳውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባታል፡፡ በተለይም ደግሞ ከጦርነት ማግስት ያለውን ኢኮኖሚ በአግባቡ ለመምራት ሰፊ ጥረት፣ እውቀትና ትዕግስት ይፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
እንደ አቶ ታምራት ከሆነ፤ በኢኮኖሚው እና በፋይናንስ ረገድ ተገቢ የሚባሉ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ በኢኮኖሚው ረገድ ነገሮችን ለማስኬድ ሁለት ዓይነት ፖሊሲዎች ያሉ ሲሆን፤ እንደ አስፈላጊነቱ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ይህ ማነቃቃያ በብዛት በመስጠት ኢኮኖሚው የበለጠ እንዲፍታታ ወይንም እንዲነቃቃ የሚከወን (Expansionist) ፖሊሲ ሲሆን፤ መንግሥት ወደኢኮኖሚው የሚገቡትን በማበረታታት እና ራሱ የሚሰጠውን በማስፋት የሚከወን ነው ይላሉ፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኢኮኖሚ በጣም ወደ ላይ እያሻቀበ ሲሄድ መንግሥት (contraction) የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊከተል ይገባል፡፡ በዚህ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ እንዳያሻቅብ እና የኑሮ ውድነቱ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሄድ መሰብሰብ (Contraction) የሚሰኘውን ፖሊሲ ሊከተል ይችላል፡፡ በዚህ ውስጥ የተበታተኑትን ነገሮች የመሰብሰብ ሂደት ሲሆን ኢኮኖሚውን ከቀውስ ለመታደግም የራሱ የሆነ ሚና ይኖረዋል፡፡
ስለዚህም እነዚሁ ሁለት የኢኮኖሚ አስተሳሰቦች መሰብሰብ (Contraction) ሆነ ኢኮኖሚው የበለጠ እንዲነቃቃ የሚከወን (Expansionist) ፖሊሲ ከጦርነት ማግስት በኋላ ቢተገበሩ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ እንደሚችሉ ምሁሩ ይናገራሉ። አንዳንዴ ነገሮችን ለማረጋጋት ሲባል፤ መንግሥት ትልልቅ የሚባሉ ነገሮችን ያዝ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የኑሮ ውድነቱም ከፍ እያለ በመሆኑ ፖሊሲ አውጪዎች ሊያስቡበት ይገባል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ግሽበትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን በመለየት እየቀነሰ መሄድ እና መሠረታዊ ነገሮች በብዛት እንዲቀርቡ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ የሰዎችን መሰረታዊ ፍላጎት የሚያሟላ ነገር ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል የሚል ምክር ይለግሳሉ፡፡
አቶ ታምራት አክለውም በጦርነቱ የወደሙ መሰረት ልማቶችን መልሶ መገንባት እና በግንባታውም ባለሀብቶችን ጨምሮ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን ማነቃቃት ይገባል ይላሉ፡፡ እነዚህ ከተከናወኑ በኋላ ወደ ሌሎች የዕድገት አጀንዳዎች መሸጋገር ይቻላል፡ ዕድገት በራሱ አይቆመም፤ ዕድገት ከቆመ በራሱ ገዳይ ነው፡፡ ይሁንና ግን መጠኑ መታወቅ አለበት፡፡ በመሆኑም የት ደርሰናል የሚለውን መመጠን ተገቢ ይሆናል፡፡
በፋይናንስ ረገድ ደግሞ የሂሳብ አያያዝና አቀራረብ ጥሩ እንዲሆንም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም በመልሶ ግንባታ ወቅት የፋይናንስ ምንጮችም በግልጽ መታወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በጦርነት ውስጥ የቆየች አገር ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ለመዝረፍም የሚያሰፈስፉ መኖራቸው አይቀሬ በመሆኑ፤ ተገቢውን ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የታለሙ ፕሮክቶችም ለታለመላቸው ዓላማ ስለመዋላቸው ጥብቅ ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ገንዘቡ ወጪ ከተደረገ በኋላም ላልተፈለገ ዓላማ የመዋል ዕድሉ ሰፊ ነው ፡፡
ይሁንና ሀብት ዝም ብሎ መለቀቅ የለበትም የሚሉት አቶ ታምራት የገንዘብ ምንጩም በበጀት ከሚፀድቅ በተጨማሪ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችን በጥልቀት መመርመርና መጠቀም እንደሚኖርበት ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም ባለው ውስን ሀብት ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ ምንድን ነው የሚለውን መለየትና ቅደም ተከተልን የተከተለ ሥራ ማከናወን ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፓርላማው ጀምሮ በተዋረድ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ግድ እንደሚል በመግለጽ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት መምህር ዶክተር ፍቃዱ የኋላሸት በበኩላቸው፤ ከጦርነት ማግስት ያለውን የኢኮኖሚ ስብራት መጠገን ብዙ እሳቤዎችን የሚፈልግና በራሱ አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተለይም ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች በደረሱበትና በበረቱበት ሁኔታ ነገሮችን ማስተካከል አለፍ ሲልም የተሻለ ነገር መፍጠር በራሱ ፈታኝ ይሆናል፡፡ ይህም በመሆኑ ከጦርነት በኋላ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ለማምጣት ሲባል በርካታ አማራጮች ላይ ማማተር እና ዕድሎችን ሁሉ መጠቀም ብሎም መጥፎ አጋጣሚዎችን ወደ መልካም ዕድል የመቀየር ጥበብን ይጠይቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ መሰረታዊ ፍላጎቶች በእጅጉ ዋጋቸው እየናረ መገኘቱና ይባስ ብሎም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጦርነት በመጎዳቱ ነገሮችን የበለጠ የሚያከብደው በመሆኑ ሊሰጠው የሚገባው ትኩረት ከመቼውም የተለየ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር መሆኗም ነገሮችን ከሚታሰበው በላይ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት የራሺያ እና ዩክሬን ጦርነት በምርቶች ላይ ያስከተለው የዋጋ ንረት በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የአገሪቱ የገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛንም የተናበበ ባለመሆኑ ይህን ለማስተካከልም ረጅም ርቀት መጓዝ እንደሚገባ በመጠቆም፤ በተለይም አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባት ያሳስባሉ፡፡ የአገሪቱ መንግሥት በጀት፣ የመንግሥት ጠቅላላ ወጪ እና ገቢው በዚያው ልክ ተጣጥሞ እየሄደ ባለመሆኑ አገሪቱን በዕዳ ጫና ውስጥ ሊጥላት የሚችልበት እድል ሰፊ በመሆኑ በአንክሮ ማየትና መፍትሄ መሻት ይገባል፡፡
እንደ ዶክተር ፍቃዱ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ከጦርነት በኋላ ኢኮኖሚው ለመጠገን ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለባት ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የምትከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እስከምን ድረስ ያስኬዳል የሚለውን በሰፊው ልታጤን ይገባል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ በአገር ውስጥ የተጀመሩ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ‹‹ሆም ግሮውን ኢኮኖሚክ ሪፎርም›› በተግባር ምን ያክል ውጤታማ ነው የሚለውን በጥልቀት መገምገም ይጠበቅባታል፡፡
አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችና ውጤቶችን በሚገባ መጠቀምና ማተለቅ የሚገባ ይሆናል፤ ጉድለቶችንም ደግሞ በአግባቡ እየሞሉና እያስተካከሉ መሄድ አስፈላጊ ነው። ከዚህ በዘለለ ግን በዚህ ውስጥ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት አስቻይ ያልሆኑ አሰራሮችን፣ መመሪያዎች እና ውጤት አልባ የሪፎርሞች አካሄዶችን ከሪፎርሙ አካል መቀነስ አለባቸው የሚል አቋም አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከኢንዱትሪው አኳያ ሲታይም አገልግሎት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፤ በኢኮኖሚው ውስጥ የኢንዱስትሪው ድርሻ ከአገልግሎትና ሌሎች ዘርፎችም የላቀ እንዲሆን አሰራሮች ሊተገበሩ ይገባል የሚል እምነት አላቸው፡፡
እንደ ዶክተር ፈቃዱ ከሆነ፤ መንግሥት የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብም ማዳመጥና መተግበርም እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ሚና ሊኖራቸው የሚችሉ እንደ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሼሽን የሚያቀርባቸውን ትንታኔዎችና ጥናቶችን፣ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ የሚያቀርባቸውን ጥናቶችና ትንታኔዎች፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት እንዲሁም ገንዘብ ሚኒስቴር እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታው አካላት የሚያቀርቡትን ምክረ ሃሳብ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም መጠቀም እንደሚገባ ነው የሚገልጹት፡፡
ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ኢኮኖሚው ለመታደግ እና ጉድለቶችን ለመሙላት በአነስተኛ ወለድ ብድር ከሚሰጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ማስኬድ ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ብድር ለማግኘትና የኢኮኖሚውን ክፍተቶች ለመሙላት አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ድጋፍ አድራጊ አገራት ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ መንግሥት የተለየ አካሄድ አሊያም ደግሞ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ሊጠቀም እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አሶሼሽን ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አረጋ ሹመቴ እንደሚሉት፤ በአገሪቱ በተለያዩ የሚስተዋለውን የምጣኔ ሀብት መንገራገጭ ለማስተካከል መንግሥት የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮችን መከተል አለበት፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ብቻ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ በተለይም ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ እና ወደ ምርታማነት እንዲገቡ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
በሌላ ጎኑ ደግሞ ሊጀመሩ የታሰቡ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማዘግየት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች መለየት ተገቢ ነው፡፡ ለአብነትም በአሁኑ ወቅት የዓለም ምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ የገባበት ወቅት በመሆኑ ኢትዮጵያም የዚሁ ምስቅልቅል ኢኮኖሚ ሰለባ ናት፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ምን ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ከተፈጠሩስ እንዴት ኢኮኖሚው መታደግ ይቻላል በሚለው ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው፡፡
የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ማጠናቀቅ ፋይዳው ብዙ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አረጋ፤ የውጭ ምንዛሪን ከማዳኑም በተጨማሪ የህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታም ይጨምራል። ይህ ደግሞ ችግሮችን የጋራ በማድረግ መፍትሄ ለማፈላለግም እድል ይሰጣል ባይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የምጣኔ ሀብት ስብራቶችን ለመጠገን መንግሥት በአገር ውስጥ ያሉትን አማራጮች ሁሉ መጠቀም እንዳለበት ያሳስባሉ።
እንደ ምሁራኑ ከሆነ፤ አገሪቱን ኢኮኖሚ ለመታደግ መንግሥት አያሌ መንገዶችን ላይ ማማተር አለበት። ከዚህም አለፍ ሲል አስቻይ የፖሊሲ አማራጮችን ማየትና መተግበር ይጠበቅታል። በተለይም በመንግሥት ዘንድ የሚታዩ ብክነቶች ማስወገድ፤ የሀብት አጠቃቀም ማሻሻልና በዋጋ ንረቱ ላይ ሚና ያላቸውን በሙሉ ማየትና መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡
ኢኮኖሚውን ለመታደግ በበጀት ከሚፀድቅ ገንዘብ በተጨማሪ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችን በጥልቀት መመርመርና መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ባለው ውስን ሀብት ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ ምንድን ነው የሚለውን መለየትና ቅደም ተከተልን የተከተለ ሥራ ማከናወን ግድ ይላል፡፡
በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ደግሞ የምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት ማሳደግም ሌላኛው መፍትሄ ነው። ተተግባሪ የፖሊሲ አማራጮችን ስራ ላይ የማዋል ኃፊነት የመንግሥት ቢሆንም ጉዳዩ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑም የሙያ ማህበራትም ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ከጦርነት ማግስት የምጣኔ ሀብት ጉድለቶችን እና ህፀፆችን ለማረም ሰፋፊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሊያስፈልጉ እንደሚችሉም ምሁራኑ ይመክራሉ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015