ኢትዮጵያ ዲጅታል ቴክኖሎጂን እውን ለማድረግ እያደረገች ያለውን ጥረት አጠናክራ ቀጥላለች። በመሆኑም አሁን ላይ በእያንዳንዱ ዘርፉ ዲጅታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረትና እየታዩ ያሉ ለውጦች አበረታች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ አገራዊ በሆነው ነባራዊ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ተሰርተው ተግባር ላይ እየዋሉ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለዲጅታላይዜሽን እውን መሆን ተስፋን የሚፈነጥቁ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በአገሪቱ ተጠናክሮ የቀጠለው ዲጅታላይዜሽን ለትምህርት ጥራትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል፡፡ መንግሥት ከትምህርት ተደራሽነት ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ቀዳሚ ጉዳይ የሆነውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እየሠራ ይገኛል፡፡ ቴክኖሎጂ የትምህርት አሰጣጥን የማዘመን የትምህርት ዘርፉን ተደራሽነት የማስፋት እንዲሁም የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል የማድረግ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ ይታመናል፡፡
የትምህርት ዘርፉን በማዘመን ዲጅታላይዜሽንን ማሳለጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፤ በቅርቡም ኢትዮ ቴሌኮም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ የመማር ማስተማር ሂደቱ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ አድርጓል፡፡ ይፋ ያደረገው መተግበሪያም ‹‹ስማርት የመማሪያ ክፍል›› (Smart Class Room)የተሰኘው ዘመናዊ የመማሪያ ክፍል የያዘ ቴክኖሎጂ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ ሥራ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡
‹‹ስማርት የመማሪያ ክፍል›› (Smart Class Room) የተሰኘው አዲሱ ቴክኖሎጂ የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሂደት ከተለመደው አካሄድ በተሻለ ሁኔታ በቀላሉ ለማከናወን ያስችላል፡፡ ተማሪዎች ከልማዳዊ መማር ማስተማር ሂደት በማውጣት በተግባራዊ ተሞክሮ የበለጸገና የተሻለ የትምህርት ተሞክሮ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ‹‹ስማርት የመማሪያ ክፍሉ›› የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ መምህራን በቀላሉ ማስተማር እንዲችሉ፣ የተማሪዎችን ሁኔታ ለመከታተል፣ ፈተናዎችን ለማረምና ውጤቶችን ለማሳወቅ እንዲሁም የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶችን፣ በቴክኖሎጂ ቤተ-ሙከራ እንዲደገፉ ለማድረግ፣ የማስተማሪያ ወጪዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል።
የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና ተደራሽነት ለማስፋት የመማር ማስተማር ሂደት በቴክኖሎጂ ማገዝ እንደሚገባ የሚናገሩት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም በመደበኛነት ከሚሰጣቸው የቴሌኮም አገልግሎቶች ውጭ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግና ዲጅታል መንገድን ለማሳለጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እያከናወነ ነው
‹‹ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎችን በቴክኖሎጂ ማገዝ መደገፍ ይገባል›› ያሉት ዋና ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፤ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ማዕከላት ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱ ጤናማና ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል ነው ይላሉ። እንደ ሀገር የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት፣ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እና የዜጎችን ውጤታማነት ለመለካት የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ያሉ ግብዓቶች መፈተሽን የሚጠይቅ መሆኑን አንሰተው፤ ገበያው የሚፈልገው ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በዓለም ላይ ያሉ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ችግሮችን በጣም በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
‹‹የተሻለ ብቃት ያለው ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ተቋማትን በማገዝና ችግሮችን በጋራ መቅረፍ ያስፈልጋል›› ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የትምህርት ተቋማትን በቴክኖሎጂ ማገዝ ሲቻል እንደ ሀገር ውጤታማ በመሆኑ የትምህርት ጥራትን በማምጣት የተሻለ ትውልድ ማፍራት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ኢትዮ ቴሌኮም እንደ አገር ችግር ፈቺ የሆኑ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለመምጣት በገነባው ሰፊ መሠረተ ልማት በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት፣ ተወዳዳሪ ለመሆን እና እያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት ለማሻሻል እየሰራ ነው፡፡ የትምህርት ተደራሽነት እንዲስፋፋ በመደገፍ የትምህርት ተቋማትን በማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም አሁን ላይ የተጀመረው የስማርት መማሪያ ክፍል የዲጂታል የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
የስማርት መማሪያ ክፍል የተሰኘው አዲሱ ቴክኖሎጂ የዩኒቨርሲቲዎች አቅም ለማጎልበት የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ‹‹ስማርት የመማሪያ ክፍል›› ሲባል የመማር ማስተማር ሂደት ማገዝ የሚችል አካታችነትን በማረጋገጥ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አብራርተው፤ የትምህርት መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂውን በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂው አዲስ እንደመሆኑ መጠን ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው በፍጥነት ቴክኖሎጂውን በመፈተሽ ተግባራዊነቱን እያረጋገጠ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ‹‹በጋራ የገነባነውን መሠረተ ልማት በሚገባ መጠቀም ፤ የትምህርት ጥራትን፤ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በጋራ ሆነን በመስራት ያለንን አጠናክሮ እንቀጥላለን›› ሲሉ ተናግረዋል።
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ጥሩ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ማስቀጠሉ ላይ ከባድ መሆኑን ነው ሥራ አስፈጻሚዋ የሚገልጹት፡፡ አሁን የተጀመረው ትውልድ ማፍራት የሚቻልባቸውን የትምህርት ተቋማት በመደገፍ የሚወሰዱትን የመፍትሔ እርምጃዎች ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ያለን ውስን ሀብት በመጠቀም ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን መፍጠር ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹አሁን ላይ ተቋማት የሚፈልጉት እውቀትና ብቁ ተብለው ከየትምህርት ተቋማቱ የሚወጡት ተማሪዎች ጋር ያለው ልዩነት የሚፈጠርበት አንደኛውና ዋንኛው ምክንያት ተቋማቱ ወቅቱ የሚፈልገውን አይነት የማስተማር ዘዴን አለመጠቀማቸውን የሚያሳይ ነው›› ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ዲጅታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ግን በየጊዜው ያሉ ለውጦችን በማየት ለማሻሻል፣ ወቅታዊና ዘመናዊ ለማድረግ ብዙ ኢንቨስትመንት ስለማይጠይቅ የምንፈልገው አይነት የማስተማር ዘዴ ለመጠቀም ያስችላል ይላሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ጥራት ከማረጋገጥ አንጻር እያንዳንዱ ትምህርት የሚፈልገውን ጥራት አምጥቷል ወይስ አላመጣም የሚለውንም ሂደት በየጊዜው ለመከታታልና ለመገምገም የሚረዳ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አጠቃላይ የትምህርቱን ጥራት ለማረጋገጥ የመምህሩን፣ የተማሪውን፣ አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱን በጊዜው ገምግሞ ማስተካከያ እርምጃ ለመወሰድ እንደሚረዳም ጠቅሰው፣ የትምህርት ሥርዓት ጥራቱንም፣ ሽፋንና ተደራሽነቱም እንዲሁም አካታችነቱንም ለማረጋገጥ ሰፊ እድል ይፈጥራል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ትምህርትን ለመቀየር ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋወቀና የተላመድ የትምህርት ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚሉት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ‹‹ስማርት የመማሪያ ክፍል›› የተሰኘው አዲሱ ቴክኖሎጂ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ መጀመሩን ጠቁመው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ይናገራሉ። እንደዚህ አይነት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በፍጥነት ማስፋፋት እንዲቻል ብዙ መስራትን የሚጠይቅ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
አዲሱ ቴክኖሎጂ ተማሪዎችን በዕውቀት ለማብቃትና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚረዳ መሆኑን በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲዎች በደንብ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ይገባል፡፡ የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በቴክኖሎጂ መታገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ብቁ ትውልድ በማፍራት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመውጣት የሚያግዛቸው መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላይ ያሉ ተማሪዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዙ ተማሪዎች ስለመሆናቸው ከዩኒቨርሲቲዎች የሚገኘው መረጃ የሚያመላክት እንደሆነና የተሻሉ ተማሪዎች እየወጡ ስለመሆናቸው ተናግረዋል። አያይዘውም ስማርት የመማሪያ ክፍሉ የትምህርት ጥራት በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው የትምህርት ጥራት የሚጀመረው የመማሪያ አካባቢን ዘመናዊ ከማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹ዘመናዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለመፍጠር ሆነ ባልተለመደው ሁኔታ ለማስቀጠል የሚቻለው ዘመናዊ የመማሪያ ክፍል መፍጠር ሲቻል ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ ደግሞ በቴክኖሎጂ ሲታገዝ ውጤታማና ምርታማ ትውልድ ማፍራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ስማርት የመማሪያ ክፍል ቴክኖሎጂ ሀብት በመቆጠብ በአንድ ጊዜ በርካታ ቦታዎች ላይ ትምህርት ለማቅረብና የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የሚረዳ ነው፡፡ መምህራን በቀላሉ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶች በቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራ እንዲደገፉና የትምህርት አሰጣጡን ከሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም እንዲችሉ የሚያግዝ ነው። የቴክኖሎጂው መማሪያ ክፍል የተማሪዎችን ሁኔታንና የቨርቹዋል ትምህርትን ለመከታተል፣ ፈተናዎችን በቀላል መንገድ ለማረም እንዲሁም ውጤቶችን ወዲያውኑ ለማሳወቅ የሚረዳ በመሆኑ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያቀላጥፍ ነው፡፡
‹‹በኛ ሀገር አንድ ተማሪ የመማር ማስተማሩ ሂደት ካመለጠው ደግሞ የሚያገኝበት ምንም አይነት አማራጭ የለውም›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ስማርት መማሪያ ክፍል የተሰኘው ዘመናዊ የመማሪያ ክፍል ግን ትምህርቱን በመቅዳት (ሪከርድ) በማድረግ በተለያየ ምክንያት ትምህርት ክፍለ ጊዜ ያመለጠው ተማሪ የተቀዳው ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። በተመሳሳይም ተማሪው የትምህርቱን ለመማር አስቸጋሪ ሁኔታው ውስጥ ሆኖ ባይመቸውም ኢንተርኔት መጠቀም የሚችልበት ቦታ ላይ ሆኖ ትምህርቱን መከታተል የሚችልበት ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተለመደ መልኩ እየተሰጠ እንደሆነና አንድ ስማርት የመማሪያ ክፍል ብቻ እንዳለ ጠቅሰው፤ ያለውም ዘመናዊ የመማሪያ ክፍል የሚባለው ማሟላት የሚገባውን ስታንዳርዱ የማያሟላ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡ አዲሱ ‹‹ስማርት የመማሪያ ክፍል›› ግን በአይነቱ ለየት ያለና ደረጃውን የጠበቀ፣ የኢትዮጵያ ትምህርት ጥራትን ለመጨመር፣ የመማሪያ ክፍል ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ እርምጃ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፤ እንደዚህ አይነቱ ስማርት የመማሪያ ክፍል ለማስገንባት ያለው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም አቅሙን በማሳደግ መሥራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ መውጫ
የአገሪቷ የትምህርት ሥነ ምህዳር ሲታይ ትምህርት ሥርዓቱ እየዘመነ ባለበት በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሂደት መጠቀም የግድ ይላል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በየትኛውም ጊዜ የትኛውም ቦታ ላይ ትምህርትን ማግኘት የሚችልበት ሁኔታን የሚፈጥር እንዲሆንም ያስፈልጋል፡፡
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ በያመቱ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ የተማሪዎች ብዛትና በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙት የመምህራን ቁጥር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ ይህም የመምህራን እጥረት መኖሩን ያመላክታል፡፡ እንዲህ አይነቱ ችግሮች ለመቅረፍ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በቴክኖሎጂ ማዘመን የሚጠይቅ ስለሆነ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተሰራው ‹‹ስማርት የመማሪያ ክፍል›› አይነት ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎችን በማስፋት በየዩኒቨርሲቲዎቹ እንዲዳረስ ብዙ መሥራት የሚጠይቅ ነው፡፡
ዘመናዊ መማሪያ ክፍል ሲኖር ትምህርትን በቀላሉና በተግባር የተደገፈ ከማድረግ ባሻገርም አንድ መምህር አንድ ቦታ ሆኖ ብዙ ቦታዎች ማስተማር የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር ያስችላል። እንዲሁም የትምህርት መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂውን በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የሚያስችል ነው፡፡
በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፉን ለዲጅታል ቴክኖሎጂ ዝግጁ እንዲሆን በማድረግ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ የሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍለቂያ የሆኑ የትምህርት ተቋማትን በማዘመን የትምህርት አሰጣጡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግና መደገፍ የትምህርት ጥራት ላቅ ያለ ደረጃ ላይ ማድረስ ለነገ የማይባል ሥራ ነው፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2015