የፋሽን ኢንዱስትሪው ለየት ያለ የፈጠራና የክህሎት ተሰጥኦ እንደሚፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች ያላቸውን ተሰጥኦ በመጠቀም ፈጠራ የታከለበት ሥራዎችን በመስራት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የተለያየ የባህል አልባሳት ባለቤት የሆኑ አገራት የፋሽን ኢንዱስትሪው ጎልቶ እንዲወጣ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። አልባሳቱ ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ከዘመናዊ ጋር በማቀላቀል ለየት ያለ ነገር መፍጠር ጥበብን ይጠይቃል። ጥበብ የታከለበት ሥራ ደግሞ ገዥውን ይማርካል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ፋሽን የሚለው ቃል በአብዛኞች ዘንድ እንደሚታሰበው ዘመናዊ የሚባሉትን አልባሳትን ዲዛይን አድርጎ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍ ያለ ችሎታን ተጠቅሞ ባህላዊውን ከዘመናዊ አልባስ ጋር በመስራት ለገበያ በማቅረብ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ መሆንም የሚቻልበትም ነው። ሙያው ፍላጎትን፣ ተሰጥኦን፣ የፈጠራ ጥበብና ክህሎት የሚጠይቅ ከመሆኑ ባሻገር አገርን በዓለም አቀፍ መድረክ ያስተዋውቃል። በመሆኑም ኃላፊነት የሚጠይቅ የሙያ ዘርፍ ነው። የሚሰሩት ሥራዎች ጥራታቸውን የጠበቁ፣ አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው እንዲሆኑ ማድረግ የፋሽን ኢንዱስሪውን አንድ እርምጃ ወደፊት ከፍ የሚያደርግ እንደሆነ ነው የሚገልጹት።
የዲዛይን ሙያ ውስጣዊ ፍላጎትንና ክህሎትን የሚጠይቅ እንደሆነ የምትናገረው ዲዛይነር ትዕግስት አማረ እንደምትለው፤ የፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲያደግ ባለሙያው በውስጡ ያለውን የፈጠራ ክህሎት በማወጣት ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት ማድረግ አለበት። ዲዛይነር ትዕግሥት እንደገለጸችልን በባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት ደረጃቸውን የጠበቁ የህጻናት፣ የወጣቶች እና የሴቶች ልብሶች በማዘጋጀት ለገበያ ታቀርባለች። እድሜያቸው ከ3ዓመት እስከ 6 ዓመት ክልል ውስጥ ላሉት ህጻናት የምትሰራቸው የፋሽን አልባሳትም ከወቅቱ ጋር እንዲሄዱ ጥረት ታደርጋለች።
ባህላዊውንም ሆነ ዘመናዊውን የፋሽን አልባሳት የተለያዩ ፈጠራዎች በመጠቀም ዲዛይን እንደምታደርጋቸው የምትናገረው ትዕግስት፤ በተለይ ለህጻናት ብላ የምትሥራቸውን ሥራዎች ብዙ ወላጆች እንደሚወዱትና ከመግዛትም ባለፈ እንደሚያበረታቷት ትናገራለች። ‹‹ለወጣቶችም ሆነ ለሴቶቹ የማዘጋጃቸውን ልብሶች ሃሳባቸውን ሳይቀር በመውሰድ እነሱ በፈለጉት መልኩ ዲዛይን በማድረግ የራሴን የፈጠራ ክህሎት ተጠቅሜ እንዲወዱት አድርጌ ዲዛይን አድርጋለሁ›› ትላለች።
በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ብላ ለወጣቶች ይሆናሉ ብላ የምታዘጋጃቸውን የተለያዩ ዲዛይኖችን እንዲያዩት በማድረግ የመረጡትን አይነት እንደምትሰራላቸው ገልጻለች። የፋሽን ሥራዎቿን ወቅቱና ጊዜው ባገናዘበ መልኩ እንደምትሰራ የምትናገረው ትዕግስት፤ ወቅቱ የበዓል ከሆነ ለበዓል የሚያስፈልጉ የባህል አልባሳትን ዘመናዊና ባህላዊ በሆነ መልኩ የምታዘጋጅ ሲሆን፣ ወቅቱ የባህላዊ ልብስ የማይሸጥበት ከሆነ ሌላ ለወቅቱ ተመራጭና ተሰማሚ የሆነ ወቅቱን የሚመጥን የአፍሪካ ልብሶች ስብጥር እንደምትሰራ ትናገራለች።
የባህል ልብሶችን ለመስራት የሚያስፈልገው ግብዓት ችግር እንደሌለ ገልጻ፤ ቅይጥ (ኮሌክሽ) በማድረግ የምትሰራቸውን የአፍሪካ ልብሶች ለመስራት ስትፈልግ ጥሬ እቃዎችን ግብዓት ከዱባይ የሚመጡ በመሆኑ ግብዓቶቹን በፈለገችው መጠን እንደማታገኝ ትናገራለች። እነዚህ ልብሶች ዋጋቸው እጅግ ተመጣጣኝ ነው፤ ከውጭ እንደመምጣታቸው መጠን ውድ የሚባሉ አይደሉም የምትለው ትዕግስት፤ ትንሽ በዋጋቸው የሚጨምረው ለሕጻናት የተሰሩ ስብጥር ልብሶች ናቸው ትላለች። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ቅይጥ ልብሶች ይልቅ የበለጠ በዋጋ ውድ የሆኑት ባህላዊ አልባሳት መሆናቸውን ታስረዳለች።
ዲዛይን የምታደርጋቸውን አልባሳቶች ለኢግዚቢሽን ለማቅረብ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን የምትናገረው ትዕግስት፤ በምትኖርበት ላልይበላ አካባቢ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ሥራዎቿን እንደምታቀርብ ትገልጻለች። ቀደም ሲል አብዛኛውን ዲዛይን የምትደርጋቸው ምርቶች የሚገዟት የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውን ጠቅሳ ፤ አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ላልይበላ ላይ የቱሪስት ፍሰቱም ሆነ ገበያው እየተቀዛቀዘ ስለመጣ አብዛኛውን ምርቶቿን የሚሸምቱት የአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ትገልጻለች።
አሁን ላይ የአፍሪካ ልብሶችን ለህጻናት፣ ለወጣቶችና ሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም በሚሆን መልኩ እንደምታዘጋጅ ጠቁማ፤ የፋሽን ሥራዋን አስፋፍታ በመቀጠል ለብዙዎች የሥራ እድል ለመፍጠር በፋሽን ኢንዱስትሪው ጎልቶ ለመውጣት ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ተናግራለች። የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ሥራዎቿ ወቅቱን ተከትለው የሚሰሩ ስለሆነ እንደወቅቱ ሁኔታ ቢለያይም ምርቶችን በብዛት ለማምረት ስትፈልግ በርካታ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ቀጥራ እንደምታሰራ ትገልጻለች። እስካሁን በቋሚነት ለአንድ ሰው የሥራ እድል የፈጠረች መሆኑን ጠቅሳ፤ በተለያዩ ጊዜያት ግን ለበርካታ ሰዎች በጊዜያዊነት የሥራ እድል እየፈጠረች መሆኑን ትናገራለች። ‹‹በተለይ ምርቶችን በብዛት ዲዛይን በማድረግ ባዛር ላይ ለማቅረብ ከፈለግኩ በርካታ ጊዜያዊ ሠራተኞች ስለምፈልግ ብዙ ሰዎች እቀጥራለሁ›› ትላለች
እንደ ትዕግስት ገለጻ፤ የሀገራችን የፋሽን ኢንዱስትሪው ብዙ ተግዳሮቾች አሉበት። በተለይ ሴቶች ለሥራው ተፈላጊዎች ቢሆኑም ሥራው ፈጠራ የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ልብሶችን ዲዛይን ለማድረግ ፣ ለመስፋትና ለመተኮስ እያንዳንዱ ሂደት ለማከናወን ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው። ባለሙያው ሥራው የሚፈጅውን ጊዜና ጉልበት ታሳቢ በማድረግ ሁሉንም አጣጥሞ ለመስራት የሚያደርገው ጥረት ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባል ትላለች።
‹‹በሥራው ላይ እንደመቆየቴ መጠን ቀደምሲል የነበረው የህብረተሰቡ አስተሳሰብና አሁን ላይ ያለው በጣም ይለያይል፤ በፊት ላይ ህብረተሰቡ ከውጭ የሚመጡትን ልብሶች ነበር የሚመርጠው፤ እኛ ጋ የምንሰራው ዲዛይን አይፈልገውም ነበር›› የምትለው ትዕግስት፤ አሁን ላይ የህብረተሰቡ አመለካከት ተቀይሯል ብዙ ለውጦች መምጣታቸውን ትናገራለች። ህብረተሰቡ በአገር ውስጥ ዲዛይን የተደረጉ ልብሶችን ከመልበስም ፣ በልብሶቹ ከማጌጥም ባሻገር ዲዛይነሩን ጭምር እያበረታታ ድጋፍ እየሰጠን እንደሆነ ትጠቁማለች።
‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ ለሙያው ፍቅርና ፍላጎት ስለነበረኝ ቴክኒክና ሙያ ተቋም በመግባት የዲዛይኒንግ ትምህርት ተምሬ፤ ትምህርቴ እደጨረስኩ ነው ሥራ የጀመርኩት›› የምትለው ትዕግስት፤ የዲዛይንኒግ ሙያ በእጅጉ ሥራ ፈጣሪ የሚያደርግ ሙያ ስለሆነ ፍላጎቱና ተሰጥኦ ያለውን ሰው ቢሳተፍበት ውጤታማ ሊሆን ይችላል ትላለች። ወደፊትም የፋሽን ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለሀገራችን በኢኮኖሚ ከፍተኛ ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ባለሙያው ሆነ የሚመለከተው አካል ተቀናጅተው በመስራት አለባቸው ስትል ተናግራለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም