በአሜሪካ ውስጥ በየ43ሰኮንዱ አንድ ሰው የልብ ድካም ያጋጥመዋል። ልብ ድካም ከሚያጋጥማቸው ሰዎች 15 በመቶ የሞት እድላቸው ከፍተኛ ነው።
የልብ ድካም፡ ምንድን ነው?
ለምን ይከሰታል?
አንድ ሰው የልብ ድካም የሚያጋጥመው የደም ዝውውር በሚያግድ ነገር ኦክስጅን የያዘ ደም ወደ ልብ መድረስ ሲያቅተው ነው። ይህ ማለት ወደ ልብ የሚደረግ የደም ዝውውር ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ ማለት አይደለም። ልባችን የሚደርሰው የደም መጠንም ትንሽ እንኳ ቢቀንስ የደማችን የልባችን ጡንቻ ደም መርጨት ይቸገራል።
የልብ ድካም ዋና መንስኤ የልብ ወይም የደም ቧንቧ በሽታ ሲሆን፣ ይህ ብዙ ግዜ የሚፈጠረው የደም ቧንቧችን ውስጥ በሚፈጠር ክምችት የደም ቧንቧችን ሲዘጋ ነው። ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን የደም ቧንቧችን ግድግዳ ላይ ፕላክ እንዲከማች ያደርጋል።
እንደ ካልሲየም፣ ፊብሪን እና የሴሎች ቆሻሻ የመሳሰሉ ነገሮች በደም ቧንቧ ሲያልፉ ክምችቱ ላይ አብረው ይጨመራሉ።
የልብ ድካም ምልክቶችን መከታተል ህይወትዎን ሊያድን ይችላል
እንደ ሲዲሲ የልብ ድካም ከሚያጋጥማቸው ሰዎች ግማሾቹ ሆስፒታል ሊደርሱ ሲሉ ወይም ህክምና ክትትል ከማግኘታቸው በፊት ነው የሚሞቱት።
የልብ ድካም ስሜቶችን ህመሙ ከማጋጠሙ ከቀናት በፊት አስቀድሞ ማወቅ ይችላል። ይህንን ስሜት ችላ ሳንል ተገቢውን ህክምና በማድረግ ህይወታችንን ከአደጋ መጠበቅ እንችላለን። ብዙ ሰዎች ከልብ ድካም አስቀድመው የሚመጡ ስሜቶችን ተከታትለው ቢመረመሩ ከበሽታው ሊድኑ ይችሉ ነበር።
የልብ ድካም ከመፈጠሩ በፊት የሚከተሉት ስሜቶች ሊሰሙን ይችላሉ፦
1/የደረት ህመም ወይም ምቾት ማጣት
ከልብ ድካም በፊት የሚያጋጥም የደረት ህመም ከፍተኛ ህመም አይደለም። በደረታችን፣ እጃችን፣ ትከሻችን እና አገጫችን ላይ የሚሰማ ቀለል ያለ ህመም ነው።
ብዙ ታማሚዎች ደረት ላይ ምቾት ያለመሰማት ብለው ይገልጹታል። ደረታችን ላይ የሚሰማ ጫና ወይም ጥብቅ ያለ ስሜት ሊሰሙን የሚችሉ ስሜ ቶች ናቸው።
•ስቴብል የደረት ህመም፡ ይህ የህመም አይነት የጠበበ የደም ቧንቧ ላይ ጫና የሚፈጥር ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ባደረግን ቁጥር የሚሰማን የደረት ህመም አይነት ነው። እረፍት ስንወስድ ህመሙ ይጠፋል።
•አንስቴብል የደረት ህመም፡ ይህ የህመም አይነት በማንኛውም ግዜ ሊፈጠር ይችላል። አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የለብንም፤ መነሻውን መተንበይ አይቻልም። ህመሙ የሚቆይበት ግዜ ከስቴብል ህመም አይነት ይበልጣል
የደረት ህመም ከግዜ ግዜ ቀስ እያለ ስልሆነ እየጨመረ የሚመጣው ብዙ ሰዎች የልብ ህመም ሊሆን ይችላል ብለው አያስቡም። ይልቅ የህመሙን መነሻ የእድሜ መጨመር፣ ወይም አካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ውጤት አድርገው ይፈርጁታል።
2/ የልብ ምት መቆራረጥ
አልፎ አልፎ ልባችን ምት ሊዘል ይችላል ወይንም ከቁጥጥር ውጪ መርገብገብ ይጀምራል። እነዚህ ስሜቶች ፓልፒቴሽን ተብለው ይታወቃሉ። ምቾት ማጣት፣ የፍርሃት እና የመደንገጥ ስሜት አብረውት ይከተላሉ።
አንዳንድ ግዜ የፓልፒቴሽን መንስኤ የሚያሰጋ ላይሆን ይችላል። ጭንቀት፣ መደንገጥ፣ መድሃኒት፣ እና ከፍተኛ መጠጥ እና ቡና መጠጣት ስሜቱ እንዲከሰት ሊያደርጉ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ትተን ስናርፍ የልባችን ትርታ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ይመለሳል።
ነገር ግን ፓልፒቴሽን የልብ ህመም መገለጫ ሊሆንም ይችላል። ፓልፒቴሽን ጋር አብሮ የማዞር ስሜት ከተሰማን ጤናችን አደገኛ ሁኔታ ላይ ሊሆን ስለሚችል ተገቢውን ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል። የልብ ትርታ መቆራረጥ ወይም ፓልፒቴሽን ለረጅም ግዜ የሚሰማዎት ነገር ከሆነ እና ከግዜ ወደ ግዜ ስሜቱ እየበረታ ከመጣ ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ይኖርብዎታል።
3/የትንፋሽ እጥረት
ማንኛውንም አይነት አካላዊ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ ከፍተኛ የትንፋሽ እጥረት ካጋጠምዎ የልብ ህመም መገለጫ ሊሆን ስለሚችል ተገቢውን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ደረጃ መውጣትም ሆነ ቀላል እንቅስቃሴ ትንፋሽዎን ሊያሳጥርዎት ይችላል።
የልብ በሽተኞች ላይ በተደረገ ጥናት፣ የትንፋሽ እጥረት የሚያጋጥማቸው ህመምተኞች የሞት እድላቸው በንጽጽር የሰፋ መሆኑን አረጋግጧል።
4/ከፍተኛ ላብ
የደም ቧንቧ ወደ ልብ ደም ማስተላለፍ ሲቸግረው ማንኛውም አይነት የአካል እንቅስቃሴ ልብን ጫና ውስጥ ይከታል። እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሰውነትዎ ሙቀቱን ለመቆጣጠር ሙቀት እና ላብ ያመነጫል። የላብን መጨመር ብዙ ሰዎች እንደ ጥንቃቄ ምልክት አይወስዱትም።
በትንሽ እንቅስቃሴም የላብ መጠንዎ መጨመሩን ካስተዋሉ ልብዎ በተገቢው መጠን እየረጨ እንዳልሆነ እና ስራውን ለመስራት ከፍተኛ ሃይል እነደሚያስፈልገው እየነገረዎት ይሆናል።
5/ማቅለሽለሽ
የደም ቧንቧዎ መዘጋት ሲጀምር ልብዎ ደም ለመርጨት ይከብደዋል። ይህም ሁኔታ ደም ወደ ጨጓራ በተገቢው ደረጃ እንዳይሄድ ያደርጋል። ይህ ሲከሰት የማቀለሽለሽ ስሜት ይፈጥራል።
የማስታወክ እና የሆድ ህመም ከላብ እና ማዞር ጋር የሚያጋጥመዎ ከሆነ የተዘጋ ደም ቧንቧ ምልክት ሊሆን ስለሚችል ዶክተር ጋር መሄድ አለብዎ።
5/መድከም እና ማዞር
ማንኛውም አይነት የልብ መዳከም ሰውነትዎን ያዳክማል። ልብ ስራውን ለመስራት ከፍተኛ ሃይል ሲያስፈልገው የመድከም ስሜት ይሰማዎታል። ትንሽ ወይንም ምንም እንቅስቃሴ አድርገው የድካም ስሜት ከተሰማዎ የልብ ሃኪም ማማከር አለብዎ።
6/የጆሮ መጨማደድ
ጆሮዎ ላይ የሚፈጠር መጨማደድ የደም ቧንቧ መጨማደድ ምልክት ሊሆን ይችላል። በ2006 የታተመ ጥናት እንደሚናገረው የልብ በሽታ ካጋጠማቸው 520 ሰዎች ውስጥ 55ፐርሰንቱ የጆሮ መጨማደድ እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ። የጆሮ ላይ መጨማደድ ካጋጠመዎ የደም ቧንቧ መዘጋት ጠቋሚ ሊሆን ስለሚችል ተገቢዎን ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011