
አዲስ አበባ፡- በአገር አቀፍ የክህሎት ውድድሩ ያሸነፉ ቴክኖሎጂዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት እንዲገቡ ይደረጋል ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ ገለጹ፡፡ ለእይታ ብቻ ቀርቦ በመደርደሪያ ላይ ብቻ ታይቶ የሚጣል ቴክኖሎጂ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራባቸው ካሉት ዘርፎች አንዱ የቴክኒክ ሙያ ዘርፉ ክህሎትና ገበያ መር እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በዘርፉ የሚሰጡ ስልጠናዎች ተግባር ተኮር፣ አገር በቀል የሆኑ እውቀቶችንና ክህሎቶችን አስተሳስሮ የያዘ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ከዚህ በፊት ለክህሎት የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአዲሱ የትምህርና ስልጠና ፖሊሲ ትኩረት ከተሰጠው ጉዳይ የትምህርና ስልጠና ስርዓቱ ችግሩን ሊቀርፍ በሚችል መንገድ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በመላ አገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የየአካባቢያቸውን ጸጋዎች መሰረት አድርገው መልሰው እንዲደራጁና ስምሪት እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ተሻለ ገለጻ፤ እያንዳንዱ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአካባቢው ያለው አገር በቀል የሆነ እውቀትና ክህሎት በመጠቀም በአካባቢው የሚሰሩ ልማቶችን መሰረት አድርገው ወደ ስራ እየገቡ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በአገር አቀፉ የክህሎት ውድድር ላይ የቀረቡት አብዛኛዎቹ አገር በቀል የሆኑ እውቀቶችን ለማዘመንና ውጤት ለማምጣት ያለመ ነው፡፡
በተለምዶ ሲሰሩ የነበሩ ዘርፎችን ለምሳሌ የግንባታ፣ የቆዳ፣ የሽመና ስራዎችን በማዘመን አለም ከደረሰበት ደረጃ ለማድረስ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለገበያ ማቅረብ መቻል አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ አገር በቀል እውቀቶቻችን በነበሩበት የሚቆዩ ሳይሆኑ መሰረታቸውን ሳይለቁ ካላቸው ላይ እሴት ጨምሮ የማሻሻል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አገር አቀፍ የክህሎት ውድድር የአንድ ጊዜ ሁነት ብቻ ሆኖ የሚቀር አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሂደቱን ያለፉ ሰልጣኖች፣ አሰልጣኞችና የቀረቡ ቴክኖሎጂዎች ይመረጣሉ፡፡ በብሔራዊ ደረጃ በሚቋቋም የባለሙያዎች ቡድን ቴከኖሎጂዎቹ መስተካከልና መጨመር ያለባቸው ካሉ ተፈትሸው እንዲስተካከሉ በማድረግ ወደ ምርት ማምረት የሚገቡበት ፍኖተ ካርታ ይቀመጣል፡፡ በዚህም የቴክኖሎጂ አቅራቢዎቹ ከግሉ ዘርፍና ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ጋር በመሆን የሚያመርቱበት ዕድል ይፈጠራል ብለዋል፡፡
ዶክተር ተሻለ፤ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የቴክኖሎጂ መፈልፍያ መሆን አለባቸው ተብሎ የተቀመጠውን የትኩረት አቅጣጫ ዕውን ለማድረግ ያሏቸውን ሰፋፊ ቦታና ማሽነሪዎች በመጠቀም የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲያመርቱ ይደረጋል፡፡ ቴክኖሎጂው ተሰርቶ ለእይታ ብቻ ቀርቦ መደርደሪያ ላይ ብቻ ታይቶ የሚጣል ቴክኖሎጂ መኖር የለበትም፡፡
በአገር አቀፍ የክህሎት ውድድር አሸናፊ ሆነው የሚመለሱ ቴክኖሎጂዎች ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የሙያና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም ቴክኖሎጂና ስራ ፈጣሪ ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን ያለፉት ሁለት አገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ክፍተቶችን በመለየት ወደ ውጤት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ተሻለ ገልጸዋል፡፡
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም