የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች የሚካሄዱ ማጣሪያዎች ይፋ መደረግ ጀምረዋል። ከቀናት በፊት የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ የኦሊምፒክ ማጣሪያ መርሃግብርና የምድብ ድልድል በተለያዩ ዞኖች ይፋ ተደርጓል። ኢትዮጵያም በቅድመ ማጣሪያ ውድድር የምትገጥመውን አገር አውቃለች።
በእግር ኳስ በአፍሪካ ዞን አራት ዙሮች ያሉት የማጣሪያ ጨዋታዎች ዕጣ የማውጣት ሥነ-ስርዓት ካይሮ ላይ ሲካሄድ የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከቻድ አቻው ጋር የመጀመሪያ የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታውን ከሐምሌ 3-11 ባሉት ቀናት እንደሚያከናውን ተረጋግጧል። የኢትዮጵያና የቻድ የደርሶ መልስ አሸናፊ ደግሞ ከናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ እንደሚጫወት በቀጥታ ስርጭት በተላለፈው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ላይ ታውቋል። በአጠቃላይ አራት ዙሮች ባሉት ማጣሪያ ውድድር የአንደኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎች ከሚሳተፉ አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። በቀጣይ ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ላይ የሚሳተፉት እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገራት በተሻለ የእግር ኳስ ደረጃቸው የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታ አያደርጉም።
በአፍሪካ በመጀመሪያው ማጣሪያ ጨዋታ ከሚሳተፉ አገራት መካከል የምእራብ አፍሪካዎቹን የኳስ ተቀናቃኝ (ደርቢ) አገራት ጋና እና ጊኒን ያገናኘው መርሃግብር ትኩረት ያገኘ ሆኗል። በሌላ በኩል በምስራቅ አፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ የተሻለ ደረጃና ስም ያላቸው ዩጋንዳና ርዋንዳን ያፋጠጠው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ቡርኪናፋሶና ማሊ የተገናኙበት ጨዋታም በተመሳሳይ ትልቅ ትኩረት ያገኘ መርሃግብር ሆኗል። በኦሊምፒኩ ማጣሪያ በአፍሪካ በአጠቃላይ ሃያ አምስት አገራት ተሳታፊ ሲሆኑ አስራ ስምንቱ ከመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ጀምሮ ተፎካካሪ ናቸው። ቀሪዎቹ ሰባት አገራት ደግሞ ባላቸው የተሻለ የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ ማጣሪያውን የሚቀላቀሉ ይሆናል። ከነዚህ መካከል የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የወቅቱ ቻምፒዮን ደቡብ አፍሪካ አንዷ ነች።
በመጀመሪያው የማጣሪያ ውድድር ከሚሳተፉ አስራ ስምንት አገራት በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸናፊ የሚሆኑት ዘጠኝ አገራት ከሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ጀምሮ ፉክክሩን ከሚቀላቀሉ ሰባት አገራት ጋር ይፋለማሉ። በዚህ ዙር በአጠቃላይ አስራ ስድስት አገራት ከተፎካከሩ በኋላ ስምንቱ ብቻ ወደ ሶስተኛው ዙር የሚያልፉ ይሆናል። ከዚህም በኋላ አራት አገራት በመጨረሻው ዙር ተለይተው በፓሪሱ የ2024 ኦሊምፒክ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል። አገራት በኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን የሚያጫውቷቸው ተጫዋቾች እድሜያቸው ከ23 አመት በታች የሆኑ ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ(ሴካፋ) የሴቶች ከ18 ዓመት በታች ውድድር ዝግጅት ለማድረግ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ከትናንት በስቲያ ለተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል። ከዚህም ውድድር ለኦሊምፒኩ ማጣሪያ ብዙ ተጫዋቾች እንደሚመረጡ ይጠበቃል።
ከሰኔ 17 እስከ ሐምሌ 1/2015 በኬንያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የምትሳተፍ ሲሆን ለውድድሩ ዝግጅት እንዲረዳ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ለ34 ተጫዋቾች ነው ጥሪ ያደረጉት። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከዛሬ ሰኞ ግንቦት 28 ከ5፡00 ሰአት ጀምሮ በፌዴሬሽን ፅሕፈት ቤት ተገኝተው ሪፖርት በማድረግ ዝግጅት እንዲጀምሩም ጥሪ ተላልፏል። አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጥሪ ካደረጉላቸው ተጫዋቾች መካከል አስራ አንዱ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፍሬ ናቸው። ይህም በአካዳሚው በመሰልጠን ላይ ከሚገኙ እና የአካዳሚውን ስልጠና አጠናቀው የተለያዩ ክለቦችን የተቀላቀሉ መሆናቸው ታውቋል።
በአካዳሚው በስልጠና ላይ ከሚገኙትና ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል በዘንድሮው የኢትዮጵያ የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ 19 ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆና ያጠናቀቀችው ማህሌት ምትኩ በአጥቂ መስመር የተመረጠች ሲሆን ግብ ጠባቂዎቹ አበባ አጃቦ እና ሮማን አምባ ይገኙበታል። የአካዳሚውን ስልጠና አጠናቀው በተለያዩ ክለቦች በመጫወት ላይ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ትርሲት ወንደሰን(ከቦሌ ክፍለ ከተማ)፣ቃልኪዳን ቅንበሸዋ (ከቦሌ ክፍለ ከተማ)፣ሊንጎ አማን (ከቦሌ ክፍለ ከተማ)፣ህይወት አመንቴ (ከይርጋጨፌ ቡና) እና ቤተልሄም ግዛቸው (ከአርባምንጭ ከተማ) ይገኙበታል። በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በረከት ዘመድኩን (ከቅድስ ጊዮርጊስ)፣ ደራ ጎሳ (ከአዳማ ከተማ) እና ሂሩት ተስፋዬ (ከቦሌ ክፍለ ከተማ) በድምሩ 11 ተጫዋቾች በእጩነት ተመርጠዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም