ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሚወደው እግር ኳስ፤ አብዝቶ ከሚወዳቸው ደጋፊዎቹ ጋር ውብ እንዲሁም አሳዛኝ ጊዜያትን አሳልፏል:: ለበርካታ ጊዜ የሚጫወትባቸውን ክለቦች በአምበልነት መርቷል፣ በታማኝነት አገልግሏል፣ ለብዙዎችም አርአያ ሆኗል። ደጉ ደበበ። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በርካታ አመታት በመጫወት ቀዳሚው ተጫዋች ነው:: በአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በወላይታ ድቻ ክለቦች የተጫወተ ውጤታማ ተከላካይ ነው። ጥቂት ለማይባሉ አመታትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን በኋላ ደጀንነት አገልግሏል።
በክለብ ቆይታው በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ተወዳዳሪ የለውም:: ብዙዎች በሚመኙት ብሔራዊ ቡድን ተካቶ ብቃቱን ከማሳየት አልፎ በተደጋጋሚ በመሰለፍ ቀዳሚ ኮከብ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ:: በሊጉ በመጫወት ላይ ያሉ አሁን ላይ ምርጥ የሚባሉት ተከላካዮች አርአያቸው ይህ ታታሪ ተጫዋች ደጉ ደበበ ነው:: ከእርሱ ጋር የተጫወቱ ብዙዎች እግር ኳስ አቁመዋል፣ ያሉበት እንኳን የማይታወቅም በርካቶች ናቸው:: እርሱ ግን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በእግር ኳስ ውብ ቆይታ አድርጎ በሊጉ ረጅም እድሜ በመጫወት ታሪክ መከተቡን ቀጥሏል።
ደጉ ደበበ በአሳና ፍራፍሬ ምርቷ በምትታወቀው አርባ ምንጭ ከተማ በ1974 ዓ.ም ነው የተወለደው:: እድገቱም ሲቀላ ተብሎ በሚጠራው የከተማዋ ክፍል ነው:: የእግር ኳስ ሕይወቱን በ1991 ዓ.ም በአካባቢው በሚገኝ የእግር ኳስ ፕሮጀክት በመታቀፍ ጀመረ:: በ1993 ዓ.ም አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ እግር ኳስ ክለብ ሲመሰረት ከቀዳሚዎቹ ተጫዋቾች አንዱ ሆነ::
በ1995 ዓ.ም አርባ ምንጭ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተለየ ታሪክ ማጻፍ የቻለ ክለብ ነበር:: በወቅቱ እስከ መጨረሻው ጨዋታ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንገት ለአንገት ቢችልም ዋንጫውን ማሳካት ሳይችል ቀረ:: ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ይገናኝ ስለነበር በወቅቱ ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት አሊያም በቡና አሸናፊነት ቢጠናቀቅ የቻምፒዮንነት ክብር የአርባ ምንጭ ይሆን ነበር:: ነገር ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ በአወዛጋቢ ሁኔታ ቡናን በማሸነፍ ዋንጫውን በመውሰዱ የአርባ ምንጭ ህልምና ቀጣይ ጉዞም ጨለማ ሆነ:: በቀጣዩ ዓመት በሊጉ እየተንገዳገደ ቢቆይም በመጨረሻ ለመፍረስ ተገደደ:: የቡድኑ አባል የነበረው ደጉ ደበበም ለክለቡ ውጤታማነት ተጠቃሽ ከነበሩ ተጫዋቾች የሚመደብ ነበር::
በቀጣዩ ዓመትም በርካታ ክብሮችን ወደ ተቀዳጀበትና ኮከብነቱን ያሳየበትን ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቀለ:: በክለቡ የመጀመሪያ ተመራጭ የመሃል ተከላካይ በመሆን እያገለገለ በሊጉ ውጤታማ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል:: በዚህም ከ1999 በቀር ከ1997-2002 ዓ.ም በተከታታይ የሊጉን ዋንጫ ከፈረሰኞቹ ጋር አንስቷል:: ደጉ ከኳስ ጋር ያለው ምቾት፣ እርጋታው፣ ቡድንን ከኋላ ሆኖ በመምራት ያለው ችሎታ አስገራሚ ነው:: በዚህም ክለቡን ለበርካታ ጊዜያት በአምበልነት እየመራ በሊጉ ጠንካራ ተከላካይነቱን ሲያስመሰክር፤ አጥቂዎችም ሆኑ የመስመር ተጫዋቾች እሱን አልፈው ከበረኛ መገናኘት የማይታሰብ መሆኑን በበርካታ አጋጣሚዎች አሳይቷል:: በ1997 ዓ.ም የውድድር ዓመት ምርጥ ተጫዋች በመባል የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል:: ደጉ የቅዱስ ጊርጊስ እግር ኳስ ክለብን ከተቀላቀለበት ጊዜ
አንስቶ በወጥነት፣ ስህተቶችን በመቀነስ ክለቡን ለድል አድራጊነት አብቅቶ ለብዙዎች ምሳሌ መሆን የቻለ የእግር ኳስ ፈርጥ ነው:: በወቅቱ የክለቡ አምበል ከነበረው ሳምሶን ሙሉጌታ ጋር የፈጠሩት ጥምረትም አስደናቂ የሚባል እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ። በዚህም በ2002 ዓ.ም ክለቡ ከ18ቱም የሊጉ ክለቦች ዝቅተኛውን ግብ ማስተናገዱ የተጣማሪውና የደጉ ብቃት ምን ያህል አስደናቂ እንደነበር ያመላከተ ነበር::
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ለረዥም ጊዜ ተጫውቷል:: ደጉ ደበበ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ውድድሮች ሁሉ ተመራጭ በመሆን አገልግሏል:: በ1997 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በ1998 ዓ.ም ደግሞ ሩዋንዳ ላይ የሴካፋ ቻምፒዮን የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የኋላ ደጀን በመሆን ጣፋጮቹን ድሎችም አጣጥሟል::
ታታሪው የእግር ኳስ ተከላካይ ደጉ ደበበ ከብሔራዊ ቡድን ራሱን ካገለለ ዓመታቶች እየተቆጠሩ ነው። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 51 ጊዜ ተሰልፎ በመጫወት ከፍተኛውን ቦታ ከያዙ ተጨዋቾች አንዱ የሆነው ደጉ ‹‹በቃኝ›› በማለት ከዋልያዎች መለየቱ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ልብ የሰበረ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። በራሱ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ያገለለው ደጉ ‹‹ከዚህ በኋላ ለስንት ዓመት ለመጫወት ሀሳብ አለህ›› ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ‹‹በዚህ ዓመት እግር ኳስ መጫወት አቆማለሁ ብዬ አልወሰንኩም። ይህንንም ማሰብ ትንሽ የሚከብድ ይመስለኛል። እግር ኳስ የአደባባይ ስራ በመሆኑ አቅሜን አይቼ ነው የምወስነው። ስለዚህ እግር ኳስ መጫወት ለጥቅም ብቻ ሳይሆን እየወደድኩት የምሰራው ሙያ ስለሆነ ገደብ ማስቀመጥ ከባድ ነው›› የሚል ምላሹን ሰጥቶ ነበር።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስም ያለው አንጋፋው የተከላካይ መስመር ተጫዋች ደጉ ደበበ በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ለክለቡ ወላይታ ድቻ ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል። የቀድሞው የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ምንም እንኳን አንጋፋ ከሚባሉ እና በአሁኑ ሰዓት በሊጉ ላይ እየተጫወቱ ካሉ ተጫዋቾች መካከል በግንባር ቀደምትነት ቢጠቀስም እድሜ ሳይበግረው በጥሩ ብቃት እየተጫወተ ይገኛል። አሁንም ቢሆን ምርጡ ተጫዋች ስራውን ቀጥሎ በመጨረሻ ጊዜያት ላይ ቢገኝም በሊጉ ከታዩ ምርጥ እና ድንቅ ተጫዋቾች አንዱ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2015