‹‹የፊደል አባት›› በሚል ቅጽል መጠሪያ ይታወቃሉ:: የፊደል አባት የተባሉበት ምክንያት የአማርኛ የፊደል ሆሄያትን በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በእግራቸው እየዞሩ ለማህበረሰቡ ስላስተማሩ ነው:: በገጠሩ ያለው ማህረሰብ ‹‹የፊደል አባት›› ሲላቸው በምሁራን በኩል ደግሞ ‹‹የፊደል ገበታ አባት›› ይባላሉ:: ምክንያቱም ፊደላቱን የፈጠሯቸው ሳይሆኑ ያስተዋወቋቸው ናቸው::
በያኔው ዘመን ፊደላትን ማስተዋወቅና እየዞሩ ማስተማር ፊደላቱን ከመፍጠር አይተናነስም:: ለዚያ ፊደል ለማያውቅ ማህበረሰብ እኚህ ምሁር የፊደላቱ ፈጣሪው ናቸው፡ እኚህ ምሁር አርበኝነትን ጨምሮ ሌሎች አገራዊ አስተዋፅኦዎችም አሏቸው:: በዚህ ሳምንት ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩበት ነውና ዛሬ እኚህን ምሁር እናስታውሳለን:: ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ::
ታኅሣሥ 24 ቀን 1895 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ፣ ቡልጋ ውስጥ አክርሚት በተባለ ስፍራ በመምህር ገብረሥላሴ ቢልልኝ እና ወይዘሮ ሥዕለአብ ወልደሚካኤል ቤት ይችን ዓለም የተቀላቀለው ልጅ ‹‹ተስፋ›› የሚል ስም ተሰጠው:: አራት ዓመት ሲሞላውም ከአባቱ እግር ስር ተቀምጦ ፊደል መቁጠር ጀመረ:: የሕፃኑ ተስፋ ወላጆች አራሽ ገበሬዎችና ከብት አርቢዎች ስለነበሩ፣ ተስፋ እያደገ ሲሄድ ከትምህርቱ ይልቅ ወደ ከብት ጥበቃው እንዲያተኩር ተደረገ:: ተስፋ ከትምህርት ይልቅ ከብት ጥበቃ ላይ እንዲያተኩር መደረጉ ያልተዋጠላቸው የተስፋ አያት መሪጌታ ቢልልኝ፤ ተስፋን እንዲያስተምሩላቸው መምህር ገብረአብ ለተባሉ የቤተ ክህነት ሊቅ ወስደው ሰጧቸው::
መምህር ገብረአብም ሕፃኑን በደስታ ተቀብለው ንባብን፣ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ መልክዓ ማርያምን፣ መልክዓ ኢየሱስንና ሰዓታት ዘሌሊትን አስተምረው በዲቁና አስመረቁት:: ተስፋ ዲቁናውን ከተቀበለ በኋላም በአክርሚት ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልግሏል::
የተስፋ አባት መምህር ገብረሥላሴ ከቅስና ሙያቸውና ከግብርና ስራቸው በተጨማሪ በትርፍ ጊዜያቸው ከእፅዋት ቀለም እያነጠሩ ለፀሎትና ለአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጡ መጻሕፍትን በብራና ይፅፉና ያዘጋጁ ነበር:: ሕጻኑ ተስፋ ይህን እያየ ነው ያደገ::
ሕጻኑ ተስፋ ህልሙ የሚሳካው አዲስ አበባ በመሄድ መሆኑን ያሰበ ይመስላል:: ከወላጆቹ ጠፍቶ ወደ አዲስ አበባ ሄደ:: አዲስ አበባ ብዙ ውጣ ውረድ ካሳለፈ በኋላ የኢትዮጵያውያን ባለውለታ የሚያደርገውን ተግባር አከናወነ:: የፊደል ገበታን አዘጋጀ::
ተስፋ የፍየል ቆዳ በእንጨት ላይ በመወጠር እየፋቀ፣ ቀለሙን ከልዩ ልዩ እፅዋት እያነጠረና ፊደላትን በመቃ ብዕር እየፃፈ በማራባት ወገኑን የሚጠቅም ስራ ያከናውን ጀመር::
በዚያ ጊዜ ግዕዝም ሆነ አማርኛ ማንበብና መፃፍ፣ በቤተክህነትና በቤተ መንግስት የተገደበ እንጂ ሰፊው ሕዝብ ዘንድ አልተዳረሰም ነበር::
በ1921 ዓ.ም ማተሚያ ቤት በማቋቋም ‹‹እውቀት ይስፋ፤ ድንቁርና ይጥፋ፤ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ›› የሚለውን ኃይለ ቃል አርዕስት በመስጠት ፊደልን፣ ፊደለ ሐዋርያንና አቡጊዳን በሦስት ረድፎች እያዘጋጀ በማሳተም በመላ ኢትዮጵያ ማሰራጨት ጀመረ:: በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ከፊደላት ጋር ተዋወቁ::
የእውቀት ብርሃንን በመላ አገሪቱ የማዳረስ ዓላማ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ሊሰናከል በተቃረበበት ጊዜ፤ ተስፋ ራሱ ባዘጋጀው የፊደል ገበታ ተጠቅሞ አርበኝነቱን ጀመረ:: ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የመውረሯ ጉዳይ እርግጠኛ እየሆነ በመጣበት ወቅት እንዲህ በማለት ጽፎ ለሕዝቡ አሰራጨ::
‹‹ ከባሕር እየወጣ መጣልን አሳው፣
በሰይፍ እየመተርን ባረር እቆላን ፈጥነን እንብላው፣
ጥንት አባቶቻችን ምግባቸው ይህ ነው፣
ምነው ያሁን ልጆች ዝምታው ምንድን ነው፣
የባሕሩ አሳ ወጥቶ ከጎሬው፣
አጥማጁ አንቆ እንጂ ስጋውን ይብላው::››
ተስፋ ይህን መሰል ወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎችን እያዘጋጁ በማተምና በማባዛት በመላ ኢትዮጵያ በማሰራጨት ሕዝቡ አገሩን ከወራሪው ኃይል ለመከላከል እንዲነሳ አድርገዋል:: ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መውረር በጀመረበት ወቅት አንዳንድ የኢትዮጵያን ባለስልጣናትን በገንዘብ እየደለለች የስለላና የማስከዳት ስራ ስትጀምር ተስፋ የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ፎቶ የጽሑፉ አርማ በማድረግ የዓድዋ ጀግኖች የፈፀሙትን አኩሪ ተግባር መድገም እንጂ ለገንዘብና ለስልጣን ብሎ አገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት እጅግ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ለመግለፅ
‹‹ የተረገመ ነው አገሩን የከዳ፣
ክብሩን ነፃነቱን ሀበሻን የጎዳ::
ከኢትዮጵያ (ከሀበሻ) ጠላት ጉቦ የበላችሁ፣
የት ነው የምትበሉት አገር ሳይኖራችሁ::
ያልታመኑ ሌቦች ከሹመት ተሸረው፣
አገሪቱን ይምሩ ታማኞች ተመርጠው››
በማለት ስለሁኔታው ሃሳባቸውን በግጥም አቅርበው ነበር::
ተስፋ እነዚህንና መሰል ጽሑፎችን እያተመ በብዛት ሲያሰራጭ አገር በመክዳት የተጠረጠሩት ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆኑ ወረራውን የሚቃወሙትና የከዳተኞቹን ድርጊት የሚያወግዙት ሹማምንት ጭምር ያጉረመርሙ ጀመር:: በጊዜው ይታተሙ የነበሩ ጽሑፎች ሁሉ በጽሕፈት ሚኒስቴር ሳይመረመሩና ፈቃድ ሳይሰጣቸው ማሰራጨት የተከለከለ ስለነበር ተስፋ ተይዞ እንዲቀርብና በየክፍላተ አገሩ አሳትሞ ያሰራጫቸው ጽሑፎችም እንዲሰበሰቡ ታዘዘ:: ተስፋም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ፊት ቀርቦ ‹‹በመላ ኢትዮጵያ ያሰራጨኸውን ስብከት የት ነው ያሳተምከው?›› ተብሎ ተጠየቀ:: እርሱም ‹‹በሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ ግቢ ውስጥ ባለው ማተሚያ ቤት ነው›› ብሎ መለሰ:: በዚህም ምክንያት ሊቀ ጳጳሱ ‹‹ስለምን በብፁዕነትዎ ግቢ ውስጥ ወንጀል ተሰራ?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ … ‹አገራችሁን አትካዱ፤ ከጠላት ጉቦ አትቀበሉ› ብሎ መስበኩ ወንጀልነቱ ምንድን ነው? …›› ብለው መልስ ሰጡ:: ጉዳዩ እንዲጣራ ተወስኖ ተስፋ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ:: ወዲያውኑም የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ እየገፋ በመምጣቱ ያለመንግሥት ፈቃድ እንዲህ ዓይነት ጽሑፎችን እንዳያትምና እንዳያሰራጭ ዋስ ጠርቶ ከእስር ተፈታ::
ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅትም ተስፋ ሕዝቡ ለነፃነቱ እንዲታገል የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን እያሳተሙ ከማሰራጨት አልቦዘነም ነበር:: ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ባለው መሳሪያ ጠላትን እንዲከላከልና እጁን አጣጥፎ እንዳይቀመጥ የሚያሳስብና ‹‹የኢትዮጵያ ፋና›› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ እያሳተመ ያሰራጭ ነበር::
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ተስፋ ታሰረ:: በመኖሪያ ቤቱ የነበሩትን ጽሑፎች ቀደም ብሎ በመደበቁ በፋሺስቶች ዘንድ እንደ ወንጀለኛ የሚያስቆጥረው ነገር ስላልተገኘበት ከእስር ተፈታ:: ከእስር ከተፈታ በኋላም ጽሑፎችን በማተምና በማሰራጨት አርበኞችን የማነቃቃት ስራውን ቀጠለበት::
በኋላ ተስፋ በድጋሚ በፋሺስት ወታደሮች ታሰረ:: ማተሚያ ቤቱም ተወረሰበት:: በእስር ቤቱ ውስጥም እስረኞች በረሀብና በውሃ ጥም መጎዳታቸውን ተመለከተ:: የእስር ቤቱን ኃላፊ አስጠርቶ ‹‹ … አርባ ማርትሬዛ ብር ስላለኝ ይፈቀድልኝና ዳቦ ገዝቼ ላብላቸው …›› ብሎ ጠየቀ:: የእስር ቤቱ ኃላፊም በተስፋ አነጋገር ስሜቱ በመነካቱ ብዙ ዳቦ፣ ሻይና ውሃ መጥቶ ለእስረኞች እንዲታደላቸው በማድረጉ እስረኛውን ሁሉ በረሀብና በውሃ ጥም ከማለቅ ታደገው::
ከወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ኃይል መባረር በኋላ ተስፋ ሰላማዊ ኑሮ ለመምራት ጥረት ማድረግ ጀመሩ:: ማተሚያ ቤቱንም በአዲስ መልኩ በማጠናከር ‹‹ሀ ሁ … እውቀት ይስፋ … ድንቁርና ይጥፋ … ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ … ›› ብለው ጽሑፎችን ማሳተምና ማሰራጨት ቀጠሉ::
የፊደል ገበታን ቀርጸው መሃይምነትን ለማጥፋት ካበረከቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ በአርበኝነት ትግላቸው ላደረጉት ተጋድሎ የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል::
97ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ ‹‹ … ሆዴ እህል በልቶ ቢጠግብም እጄን ስራ ይርበዋል …›› በማለት ለስራ ያላቸውን ጉጉትና አክብሮት ገልፀው ነበር::
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ከእፅዋት የቀለም ዱቄት ቀምመውና በጥብጠው፣ ከመቃ እንጨት ብዕር ቀርጸው በወረቀት ላይ ፊደል በመፃፍ በካርቶን ላይ እየለጠፉ በማቅረብ ሚሊዮኖችን ከመሃይምነት ያወጡና የእውቀትን ብርሃን የፈነጠቁ ሆኑ::
ቀኛዝማች ተስፋ የስራን አስፈላጊነትና የትምህርትን ጥቅም ሲያስረዱ ‹‹ማንኛውም ሰው እናት አገሩ ባስገኘችለት፤ ሊቃውንት አባቶች አዘጋጅተው ባቆዩለት ፊደል ተምሮ ማንበብና መፃፍ ተቀዳሚ ተግባሩ ይሆናል:: መምህራንም የፊደላትን ስነ ባሕርይ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል:: ይህም በየጊዜው የሚነሳው ብሔራዊ ትውልድ ራሱን ክዶ ሌላውን ሆኖ እንዳይገኝ ወይም ‹መነሻውን አያውቅ መድረሻውን ይናፍቅ› ከመሰኘት ነፃ ያደርገዋል›› ብለው ነበር::
ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ በስራቸው ላይ ከጎናቸው ሆነው ሲያበረታቷቸውና ሲደግፏቸው ከኖሩት ወይዘሮ አለሚቱ ንጉሤ ጋር ጋብቻ መስርተው 13 ልጆችን አፍርተዋል:: በሕይወት እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ 42 የልጅ ልጆችንም አይተዋል:: ‹‹ሀ ሁ … እውቀት ይስፋ … ድንቁርና ይጥፋ … ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ … ›› ብለው በማወጅ ድንቁርናን ለማጥፋት በመላ ኢትዮጵያ የፊደል ሰራዊትን ሲያዘምቱ የኖሩት አርበኛው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ፣ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በደብረ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም