የዘንድሮ ዝናብ በጋው ከክረምቱ የገጠመ መስሏል:: ዝናቡ ጸሐይዋን እያሸነፈ፣ ጊዜውን እየረታ ትግል የገጠመው ገና በጠዋቱ ነው:: ዛሬ አያ ዝናቦ ላባብልህ፣ ላሳልፍህ ቢሉት መስሚያ ጆሮ የለውም:: ይኸው ወራትን በእምቢተኝነት ዘልቆ እንዳሻው ሲያደርግ ከርሟል::
ወዳጆቼ ! እንደው አይጣል እንጂ ሌላማ ምን ይሏል? መቼም ከተፈጥሮ መጣላት መጋፋቱ አይሞከርም:: እንዲያማ ቢሆን ያለጊዜው ደርሶ በጎርፍ ወጀቡ፣ በንፋስ ዳመናው ሲያስፈራራ ‹‹እስቲ ተው እረፍ ›› በተባለ ነበር::
በዘንድሮው ዝናብ ላይ የሚሰጠው ትርጉም የተለያየ ነው:: አንዳንዱ ድንገቴውን ዝንብ እንደበረከት፣ እንደስጦታ ቆጥሮ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል:: አንዳንዱ ደግሞ ይህ አይነቱን በረከት በጤና አይቆጥረውም:: እረፍት አልባው ዝናብ ገጠሩን ዘንግቶ በከተማ ብቻ እንዳይወሰን ሲገምት በስጋት ነው::
የሌላው ሀሳብ ደግሞ በምርምርና ጥናት የተደገፈ ይመስላል:: የዝናቡን ቀድሞ መከሰት በበጎ አይመለከትም:: የበጋው እንግዳ ክረምቱ ሲደርስ ሀይሉን ጨርሶ፣ ባዳ ሆኖ ጊዜውን እንዳይረሳው ከወዲሁ ይተነብያል::
ያም ሆነ ይህ የዘንድሮ ዝናብና ጨዋታው በገዛ ሜዳው አልሆነም:: በጋውን ተጋፍቶ፣ ጸሐይዋን አሸማቆ እንዳሻው ሲሆን መክረሙን አይተናል:: እንደውም ብዙዎቻችን ጸሐይ ሙቀቱን ረስተን የክረምት ሰዎች ሆነናል:: ማለዳውን በወፍራም ልብስ፣ ተጀቡነን በጭቃ ጫማዎች እየተጠቀምን ነው::
የዘንድሮ ዝናብ ደግሞ ብቻውን እየመጣ አይደለም:: ሲለው በረዶ አዝሎ አልያም በወጀብና ጎርፍ ታጅቦ ነው:: ደርሶ በተመለሰ ቁጥር የሚጠፋው፣ የሚያፈርሰው ይበዛል:: ባስ ባለው ቀን ቤት ንዶ፣ አጥር አፍርሶ ሕይወት ይነጥቃል:: ዘንድሮ ድንገቴው እንግዳ በወግ አልሆነም:: ያለቀጠሮ እየመጣ፣ ያለሀሳብ ያሻውን ፈጽሞ ይመለሳል::
አሁን ላይ በየቀኑ ለጆሮ የሚደርሱ ዜናዎች የምስራች የላቸውም:: ድንገቴው ዝናብ ቤት አፈረሰ፣ ንብረት አወደመ፣ ሕይወት ነጠቀ ይሏቸው ወሬዎች ተለምደዋል:: ዛሬ ይህን ሰምተን፣ ስለነገው ማሰብ መጨነቅ ልምዳችን ሆኗል::
እነሆ ከወራቶች መሀል ዘጠነኛ በሆነው የግንቦት ወር ላይ እንገኛለን:: እንደዋዛ የጀመርነው ጊዜ ሳናስበው መጋመስ ይዟል:: ይህ ወር በባህርይው ወበቃማ፣ ሙቀታማ የሚባል ነው:: ይህን ተከትሎ በእንግድነት የሚቆዩት ዝንቦች ጊዜውን አሳበው ሲያበሳጩን ይከርማሉ:: አቅል ከምታስጥለው የግንቦት ጸሐይ ጋር በእኩል መራመድ ደግሞ ከሽንፈት ይጥላል:: እኛ እስከዛሬ ግንቦትን ስናውቀው ከነዚህ ባህርያቱ ጋር ነበር::
ዘንድሮ አያ ግንቦት በምናውቀው አይነት ባህርይው አልተከሰተም:: ወሩ አንድ ብሎ ሲጀምር እንደልምዱ በሙቀትና በወበቁ አልሆነም:: ይህ ልምዱ አስቀድሞ በዶፍ ዝናብ ተውጧል ፣ በጭቃ ጎርፉ ተይዟል:: እንዲህ መሆኑ ደግሞ ለግንቦት ገጽታ መለወጥ ድርሻውን ከፍ አደርጎታል::
በዚህ ወር ማለዳውን ደምቃ እስከ ምሽት ትዘልቅ የነበረችው ጸሐይ ሰሞኑን ስትሽኮረመም ከርማለች:: አንዳንዴ ልበርታ ባለች ቀን ለወጉ ፈገግ ማለቷ አይቀርም:: እንዲያም ቢሆን ቆይታዋ እምብዛም ነው:: ገና ማንሰራራት ከመጀመሯ በላይዋ የሚንጓጓው አስደንጋጭ ነጎድጓድ መድረሻ ያሳጣታል:: ይህኔ ፈገግታዋ ይዳምናል፣ የጋለ ሙቀቷ ይቀዘቅዛል:: ጣይቱ በራሷ ጊዜ ያለቀጠሮ ደርሶ በሚያውካት ዝናብ ትከፋለች:: ከልብ ታዝናለች::
እንዲህ በሆነ ጊዜ እመት ጣይቱ ቆይታዋ አይዘልቅም:: እንደፊቱ ውላ፣ አመሻሽታ የመመለስ ውጥኗ በአጭር ይቋጫል:: እንደቀድሞው ስቃ አሳስቃ የመሄድ አቅም ያጥራታል:: እንዳመጣጧ ሁሉ የውሎዋ ነገር አይሰምርም ::
በቀን፣ በሰዓቷ ስንት ልታደርግ ያሰበችው ፍልቅልቅ ደስታዋ በአያ ጉልቤ ሲነጠቅ ውሳኔዋ ይፈጥናል:: ይሄኔ ከሰማይ በታች ያለ ዓለሟን ጭልም ፣ ድርግም አርጋው ለመጥፋት አትዘገይም:: የእሷን ህጋዊ ቦታ ፈጥኖ የሚረከበው ጉልበተኛ ወዲያው ያሻውን ሊያደርግ ፈጣን ነው::
የበጋው እንግዳ በነጎድጓዱ እያሸበረ፣ በዶፍ በረዶው ተገልጦ በዝናብ ጎርፉ፣ በጭቃ ማጡ የልቡን ያደርሳል:: እንደ ልማድ ወጉ ደረቁን የሰነበተው መሬት በሀያሉ ድንገቴ ተሸንፎ እጅ ይሰጣል::
ይሄኔ ተዘግተው የሰነበቱ የከተማ ቱቦዎች ሲውጡት የከረሙት ቆሻሻ አያድናቸውም:: አጅሬው ሲመጣ በእጅጉ አቅም ያጥራቸዋል:: ድንገቴው ደርሶ በአፍ በአፍንጫቸው ሲጥለቀለቅ የዋጡትን መትፋት ይሳናቸዋል:: ጭንቅ ጥብ ይሆናል አንገት ጎሮሯቸው፣ ሆድ ጉድጓዳቸው አብዝቶ ይታነቃል::
የበጋው እንግዳ በቻለው ሁሉ ሞልቶ ሲፈስ ጎዳና መንገዱ፣ ሜዳ ስርቻው በማዕበሉ ይጥለቀለቃል :: ይሄኔ እግረ መንገዱን በእንግድነት ጎራ የሚልባቸው አንዳንድ ስፍራዎች ሳይቀሩ ጡንቻውን ሊቀምሱ ግድ ነው::
እሱ ያገኘውን ሲጠርግ፣ የወሰደውን ሲያጠፋ ምህረት ይሉት የለውም:: ትናንት ክፉ ድርጊቱን ሰምተው ዛሬን የደነገጡ አንዳንዶች ነገ ከእነሱ ደርሶ የሚያመጣውን ቅጣት አያውቁም::
እነሆ ! ባልተሰጠው ጊዜ ባልተጠበቀ ወቅት ደርሶ ያሻውን ሲያደርግ የከረመው የበጋው እንግዳ ወራት እየተሻገረ፣ ቀናት እየቆጠረ ከግንቦት ላይ ደርሷል:: እንግዳው በግንቦትም አገባቡ ከወትሮው ሳይለይ ቆይቷል::
ግንቦት መንጋት ሲጀምር አንስቶ የለማዳው እንግዳ ልማድ አልጎደለም:: እንደወትሮው ሳያሰልስ ጠዋት ማታ መመላለስ ይዟል:: ቀድሞ ግንቦትን በሙቀቱ የሚውቁት አንዳንዶች ተስፋ ቆርጠዋል:: የበጋ ልብሳቸውን ትተው በክረምቱ ታይተዋል:: የሜትሮሎጂው ወቅታዊ ዘገባ አሁንም ዝናቡ በጀመረው ኃይል እንደሚቀጥል ማስገንዘቡን አልረሳም::
አሁንም ግንቦትና ዝናብ በግንባር ተገናኝተዋል:: የወቅቱ ሙቀትና ወበቅ እየተረሳ ነው:: እነ እመት ዝንቢት ልምዳቸው ቢቀር አኩርፈዋል:: እነሱ ዘንድሮን የሆነላቸው አይመስልም:: ተደራጅተው ብቅ ከማለታቸው ጥግ የሚያሲይዛቸው ሀያል መድረሻ አሳጥቷቸዋል:: ዛሬም ዝናቡ እየጣለ፣ ወንዞች እየሞሉ ነው:: ጣይቱም በማፈር መሽኮርመሟ ቀጥላለች::
ከሰሞኑ ደግሞ ግንቦት ማንነቱን ማስታወስ የጀመረ መስሏል:: ከማለዳው ጠቁሮ የሚታየው ዳመና እስከ ረፋዱ አይዘልቅም:: እንደ ጊዜው ልማድ አናት የሚበሳው፣ አቅል የሚያሳጣው ሙቀት ከጸሐይ ተባብሮ የወጉን ማድረስ ይዟል::
አንዳንዴ ቀትር ላይ የሚብሰው ሙቀት እንዳመረረ ይውላል:: ይህን ያስተዋሉ አንዳንዶች ወፍራም ልብሳቸውን ይጥላሉ:: ማግስቱን የከረሙበትን የክረምት ጫማ አሽቀንጥረው የበጋ ሰው ይሆናሉ::
ወረተኛው ግንቦት ግን እንደትናንቱ አይውልም:: ዳመናን በሰማዩ ይጥላል፣ ቀኑን አስኮርፎ ያጨልማል:: ‹‹መጣሁ›› በሚለው ዝናብ በነጎድጓድ ታጅቦ ማስፈራራት፣ ማጉረሙረሙን ቀጥሏል::
ግንቦት ወደማታ ባህርይው እንዲህ ታይቷል:: ከሙቀት ወበቁ አጋርቶ፣ ከዝናብ ዳመናው ተስማምቷል:: ከጸሐይዋ ታርቆ ከወግ ልምዱ ውሏል:: ግንቦት ወደማታ ባህርይውን አልረሳም፣ ማንነቱን አልዘነጋም::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015