የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሄራዊ ቡድኑ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚለብሳቸውን የሙሉ ትጥቅ አቅርቦት አጋርነት ስምምነት ከሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ጎፈሬ ጋር ተፈራርሟል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ የትጥቅ አቅርቦት ለአራት ወራት እንደሚቆይም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሄራዊ ቡድኑ በጊዜያዊነት የሚጠቀምበትን ትጥቅ አቅርቦት የአጋርነት ስምምነት ከትናንት በስቲያ ከሀገር በቀሉ ጎፈሬ የትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር መፈራረም ችሏል፡፡ የአጋርነት ስምምነቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ተፈራርመዋል። ቡድኑ በቀጣይ በሚኖሩት ዓለም አቀፍ ውድድሮችም በዚሁ ትጥቅ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
ለኢትዮጰያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን የሚቅርበው የስፖርት ትጥቅ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ሲሆን፤ ዋናውን የሴቶችና የወንዶች ብሄራዊ ቡድን ጨምሮ በሁሉም የእድሜ ክልል ለሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች የሚቀርብ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ዋናውን የብሄራዊ ቡድን ማለያ፣ የልምምድ እና የደጋፊ ትጥቆችን ጨምሮ በአጠቃላይ 17 የስፖርት ትጥቆችን ለብሄራዊ ቡድኑ ያቀርባል፡፡ የስፖርት ትጥቅ አቅርቦቱ ለቀጣይ አራት ወራቶች ብቻ እንደሚቆይ በስምምነት ስነስርዓቱ ተጠቁሟል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ፌዴሬሽኑ የራሱን ትጥቅ በሀገር ውስጥ ለማምረት በመወሰኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊና ከግብጽ እንዲሁም በመጪው ሀምሌ ወር/2015ዓም ወደ አሜሪካ በመጓዝ ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሙሉ የስፖርት ትጥቆቹ ከጎፈሬ የትጥቅ አቅራቢ ድርጅት የሚያገኝ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከሁለት ወራት በኋላ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም በጎፈሬ የስፖርት ትጥቆች እንደሚቀርቡለትም ተጠቁሟል፡፡
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም ለብሄራዊ ቡድኑ የስፖርት ትጥቆችን በተወሰነ መልኩ ሲያቀርብ ከነበረው የእንግሊዙ አምብሮ ጋር በዋጋ ንረት እና በዶላር እጥረት ምክንያት የትጥቅ አቅርቦት ውሉን እንዳቋረጠ ገልጿል። በዚህም የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ሀገር በቀል የስፖርት ትጥቅ የሚያመርቱ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ የሚያስገድድ በመሆኑ የሀገር ውስጥ አማራጭ ለማየት ወስኗል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጎፈሬ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ድርጅቱ የስፖርት ትጥቆቹን ለገበያ ከሚያቀርብበት 50 በመቶ በመቀነስ እንደሆነም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የእድሜ እርከን ለሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች የስፖርት ትጥቅ ሲያቀርብ የነበረው አምቡሮ የትጥቅ አምራች ድርጅት መሆኑን ያስታውሳሉ። ድርጅቱ መቀመጫውን እንግሊዝ ሀገር አድረጎ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ቅርንጫፉ በኩል ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የስፖርት ትጥቆችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
አቅርቦቱ በዋነኝነት ለዋናው ወንዶች ቡድን ቢሆንም በተለያዩ የእድሜ ክልል ለሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖችም ትጥቆችን በማቅረብ በአጋርነት መቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት እና አቅርቦቱ በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ ስምምነቱ ሊቋረጥ ችሏል። የመንግስት አቅጣጫዎች እና የኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲኖሩ ስለሚያበረታታ ከሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ድርጀት ጋር ለመስራት እንደተወሰነም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ባህሩ ገለጻ የሀገር ውስጥ የትጥቅ አምራቾች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ከጎፈሬ ጋር ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር በኢትዮጵያ በተዘጋጀበት ወቅት ለብሄራዊ ቡድኑ ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አቅርቧል። በተጨማሪም እጥረት ሲገጥም እንዲሁም አምብሮ ያማያሟላቸውንና ትኩረት የማይሰጣቸውን ከማለያ ውስጥ የሚለበሱ ትጥቆችን ከጎፈሬ ጋር በመስራት ሲቀርቡ እንደነበርም ያክላሉ፡፡
ፌዴሬሽኑ ከጎፈሬ ጋር አብሮ የመስራቱ ልምዱ የቆየና ደረጃውም ከፍ እያለ በመምጣቱ አብሮ ለመስራት መወሰኑን ጠቁሟል፡፡ ድርጅቱ ምርቶቹን በሀገር ውስጥና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ በመቻሉ እንደ አማራጭ ሊወሰድ ችሏል። ፌዴሬሽኑ ከተለያዩ የውጭ እና ሀገር በቀል የስፖርት ትጥቅ አምራቾች ጋር በመስራት ለብሄራዊ ቡድኖች ትጥቆቹን እያቀረበ ቢገኝም በቀጣይ በትጥቅ አቅርቦት ላይ የራሱ ፕሮጀክ እንዳለውም ጠቁሟል፡፡ በዚህ መሰረት እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የራሱ የሆነ ብራንድ ሊኖረው ይገባል በሚል እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በዚህም ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያየት ስራዎች የተጀመሩ ሲሆን፤ በቀጣይም የራሱን ማሊያዎችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2015