ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር የስፖርት ችግሮችን ለመፍታት
ብርሃን ፈይሳ
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤን ለ8ኛ ጊዜ አካሂዷል:: አካዳሚው የስፖርት ሳይንስ የጥናትና ምርምር ጽሁፎች የሚታተሙበት ድረገጽም አስመርቋል::
በኢትዮጵያ ስፖርት ተተኪ እና ውጤታማ የሆኑ ወጣት ስፖርተኞችን በማፍራት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ ከተልእኮዎቹ መካከል የስፖርት ጥናትና ምርምሮችን ማከናወን አንዱ ነው:: በምርምር የተገኙ ውጤቶችንና ተሞክሮዎችን ከማሰራጨት ባለፈም፤ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ሳይንስ ምሁራን የተሰሩ ጥናቶችን በዓመታዊው ጉባኤ ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል:: ዘንድሮም ይህ ጉባኤ ለ8ኛ ጊዜ ‹‹ሳይንሳዊ የስፖርት ጥናትና ምርምር ለአገር ብልጽግና›› በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት ሁለት ቀናት ተካሂዷል:: ችግር ፈቺ እና የመፍትሄ ሃሳብ ማመላከት የሚችሉ ጥናቶች ለህትመት የሚበቁ ሲሆን፤ ገለጻ ከተደረገባቸው በኋላ በጉባኤው በተገኙት የስፖርት ሳይንስ ምሁራንም ውይይት ተደርጎባቸዋል::
አካዳሚው በስፖርትና ምርምር ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ለማበርከት ባቀደው መሰረትም የስፖርት ሳይንስ ጆርናል አዘጋጅቶ ወደ ስራ አስገብቷል:: የኢትዮጵያ ስፖርት ሳይንስ ጆርናል (EJSS) የሚል መጠሪያ ያለው ድረገፅ፤ አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምሮችን በማሳተም የመጀመሪያው መሆኑም በጉባኤው ተጠቁሟል:: የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የአካዳሚው ዳይሬክተር አምበሳው እንየው እንዲሁም ምሁራኑ በተገኙበትም ድረገጹ ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል:: አገልግሎቱ የሚሰጠው በእንግሊዝኛ፣ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ሲሆን፤ በቀጣይ ሌሎች ቋንቋዎችንም ወደ ስራ ማስገባት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመስራት ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግም ታቅዷል::
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ፤ የስፖርት ፖሊሲው በግልጽ ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ዘመናዊ የስፖርት ሳይንስና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የላቁ ስፖርተኞችን ማፍራት መሆኑን አብራርተዋል:: የጥናትና ምርምር አስፈላጊነት አንድ ተቋም ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛልም ብለዋል:: በጥናት ላይ ያልተመሰረተ አካሄድ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል ያሉት ሚኒስትሩ ዘርፉ በጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት በማድረግ መሰል ተቋማትን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል:: አካዳሚውም የተሰጠውን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሙያዎች ጋር በመሆን የሚሰራውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አክለዋል::
የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ በዚህ ወቅት ስፖርት እየተመራ ያለው በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር መሆኑን ገልፀዋል:: በመሆኑም ከልማዳዊ አሰራር ወጥቶ ትልቅ የመወዳደሪያ እንዲሁም የገጽታ መገንቢያ መሳሪያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል:: ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በስፖርቱ ዘርፍ በሚፈለገው መልኩ በጥናት የተደገፈ መንገድ አልተከተለችም:: ስለዚህም አካዳሚው ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔ በማዘጋጀት ወሳኝ ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል:: ወደ ስራ የገባው ድረገጽም የኢትዮጵያን እምቅ የስፖርት አቅም ለማስተዋወቅ የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል:: ይህ እንዲሆንም የሚመለከታቸው አካላት ጠንክረው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል::
የአካዳሚው ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው በበኩላቸው፤ አካዳሚው ተልእኮውን ለማሳካት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: ይህም በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የስፖርት ምርምር ቤተሙከራ በማዘጋጀት ለሰልጣኞቹ የብቃት ልኬት ከማድረግ ባለፈ ለተለያዩ ብሄራዊ ቡድኖችም አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል:: የተለያዩ የስፖርት ማህበራት፣ ክለቦች፣ የማሰልጠኛ ተቋማት፣… በሚፈልጉት መልኩም የስልጠና፣ የማማከር፣ … አገልግሎቾችንም ያገኛሉ:: ከዚህ ባለፈ አካዳሚው ባለፉት ዓመታት አሳትሞ ያወጣቸውን የጥናት እና ምርምር ውጤቶች በስፖርቱ ዘርፍ መደርደሪያ ላይ ከመታየት ይልቅ ለውጥ እንዲመጣ፣ ተቋማት በግብዓትነት እንዲጠቀሙ እንዲሁም ለተግባራዊነቱ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጥ እንደሚገባውም ጠቁመዋል::
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ታዳጊዎችን ከማፍራት ባለፈ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን እንዲሁም የሙያ ብቃት ስልጠናዎችን መስጠት ከኃላፊነቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ:: ጥናትና ምርምርን በሚመለከትም የአገሪቷን የስፖርት ችግሮች የሚፈቱ ምርምሮችን እንዲሁም ልኬቶችን በራሱ ቤተሙከራ ያከናውናል:: በእነዚህ ዓመታትም 42 የሚሆኑ ጥናቶችን በአገሪቱ የሚገኙ የዘርፉን ሙያተኞች በመጋበዝ ጥናቶችን አድርጓል:: የተለያዩ ከፍተኛ ተቋማትም በተለያዩ ጊዜ የሰሯቸውን 150 ጥናቶች ጨምሮ በጥቅሉ 192 ጥናቶችም አካዳሚው ባከናወናቸው ጉባኤዎች ላይ ቀርበዋል:: የዘንድሮውን ጨምሮም መድረክ ያገኙት ጥናቶች ታትመው ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2015