የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን በቀጣዩ ዓመት በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ፈረስ ስፖርት ቻምፒዮና ብሔራዊ ቡድኑን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መርጧል:: ብሔራዊ ቡድኑ ሦስት የዝግጅት ምዕራፎች እንደሚኖሩትም ተገልጿል::
ቻምፒዮናው የሚዘጋጀው በአፍሪካ ፈረስ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን (ACES) አማካኝት ሲሆን በሦስት የዕድሜ እርከኖች ተከፍሎ የሚካሄድ ይሆናል:: የዕድሜ እርከኖቹ፤ በሕፃናት ምድብ ከ12 እስከ 14 ዓመት፣ በወጣቶች ምድብ ከ15 እስከ 18 ዓመት እና በአዋቂዎች ምድብ ደግሞ ከ18 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ስፖርተኞችን ያካተተ ነው:: ውድድሩም በመጪው ዓመት መጀመሪያ (2016ዓ.ም) ጥቅምት ወር የሚካሄድ ነው::
ለዚህ ውድድርም የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን አገራቸውን የሚወክሉ የብሔራዊ ቡድን አባላት ምርጫን እያካሄደ ይገኛል:: አሶሴሽኑ የብሔራዊ ቡድኑን የምርጫ እንዲሁም የዝግጅት ሂደት ከመጋቢት ወር 2015ዓ.ም አንስቶ በተለያዩ ምዕራፎች ከፍሎ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል:: ስፖርተኞቹ የተመረጡትም በተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮች ነው::
በመጀመሪያው የዝግጅት ምዕራፍ በየዕድሜ ክልሉ የሚወዳደሩ ስፖርተኞች ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፤ ስፖርተኞቹ ከ 8ቱ የአሶሴሽኑ አባል ክለቦች ሊመረጡ ችለዋል:: በዚህ ምዕራፍ በሕፃናት ምድብ 11 ስፖርተኞች፣ በወጣቶች ምድብ ደግሞ 9 ስፖርተኞች መመረጥ ችለዋል:: ሁለተኛው የዝግጅት ምዕራፍ የማጣሪያ ውድድር ማካሄድ ሲሆን ውድድሩን ለማድረግ የሚያስችል ደንብ ተዘጋጅቶ ከክለቦች ጋር መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ በአሶሴሽኑ የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ለክለቦች በማሰራጨት ሊያከናውን ችሏል::
በደንቡ መሠረትም ሦስት የማጣሪያ ውድድሮች ሲከናወኑ፤ የመጀመሪያው የማጣሪያ ውድድር ሚያዝያ 22/ 2015ዓ.ም ሁለተኛው ደግሞ ግንቦት 5/2015 ዓ.ም በቤካ ፈርዳ ፈረስ ስፖርት ክለብ ተካሂዷል::
ሦስተኛውና የመጨረሻው የማጣሪያ ውድድርም ግንቦት 19/2015 ዓ.ም በቤካ ፈርዳ ስፖርት ክለብ ተከናውኖ ብሔራዊ ቡድኑን በየዕድሜ እርከኑ የሚወክሉ ስፖርተኞች ተመርጠዋል:: በዚህም መሠረት ሦስቱ የማጣሪያ ውድድሮች ከተጠናቀቁ በኋላ ከየምድቡ በመጨረሻው የማጣሪያ ውድድር በአጠቃላይ ውጤት ከ1ኛ እስከ 4ኛ የወጡ እና አንድ ተጠባባቂ ተወዳዳሪ ተመርጧል:: ሴት ስፖርተኞችን ለማበረታታት ሲባልም ከየ ምድቡ አንድ አንድ ሴት ስፖርተኛ የመመረጥ ዕድል ሊሰጣቸው ችሏል::
ብሔራዊ ቡድኑን በመወከል በአዋቂዎች ምድብ
አምጀድ ሳሚ በ30 ነጥብ አንደኛ፣ ዳንኤል ሰለሞን በ24 ነጥብ ሁለተኛ፣ አብይ በሪሁን ደግሞ በ23 ነጥብ 3ኛ እና ተገኑ አራርሶ በ22 ነጥብ 4ኛ በመሆን ተመርጠዋል:: በተጠባባቂነት ደግሞ ዮሐንስ ታደሰ በ16 ነጥብ ቡድኑ ውስጥ ሊካተት ችሏል::
በወጣቶች ምድብ መሐመድ ሳሚ፣ አብረሃም ካሱ፣ ዮናስ ጌቱ እና አማረ ኡስማን ከ1ኛ እስከ 4ኛ በመውጣት ሲመረጡ ማይክ ዮናስ በተጠባባቂነት ተይዟል:: በሕፃናት ምድብ ሁሉም ከቤካ ፈርዳ ስፖርት ክለብ ሲመረጡ፣ ወንድማማቾቹ ፈጠነ ተሾመና ቀነኒሳ ተሾመ፣ አዲሱ ንጉሡ፣ ጂቱ ግርማ እና ፈጠነ ንጉሡ በቀጥታ ሲመረጡ ሺመያ ዴሳም በተጠባባቂነት ተይዟል::
ከተመረጡት ስፖርተኞች መካከል በአዋቂዎች ምድብ ውድድሩን ያደረገው ዳንኤል ሰለሞን ከወትሮ በተለየ መልኩ
መልካም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል:: ከ30 ዓመት በፊት ሲደረግ የነበረውን ውድድር ዕድል በመፍጠር ላይ በመሆኑ አሶሴሽኑ ሊመሰገን ይገባል:: የመዝለያው መሰናክል ከፍታ በዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ በደንብ ለመዘጋጀት እንደሚጠቅማቸውም አስረድቷል::
አቶ ጸጋሁን ተሰማ የቤካ ፈርዳ ስፖርት ክለብ ባለቤት በመጨረሻው የማጣሪያ ውድድር በየደረጃው ብዙ ተወዳዳሪዎችን ይዞ መቅረቡን ገልጾ፤ በተለይ በሕፃናት ምድብ ስድስት ልጆች መወከላቸውን ጠቁሟል:: ባለፈው ዓመት ከክለቡ በተመረጡ 6 ታዳጊዎች ኢትዮጵያን ወክሎ በአልጄሪያ በተደረገው ውድድር አንድ ወርቅ መመዝገቡን አስታውሰው ዘንድሮም ጥሩ አቋም በማሳየታቸው ውጤት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል:: ስፖርቱ ከሌሎች ስፖርቶች በሚለየው ፈረስ ስፖርት ሁለት ስልጠና ይጠበቃል:: ፈረሱና ስፖርተኛው ከፍተኛ ስልጠናን የሚፈልጉ ሲሆን፤ ሁለቱ ተቀናጅተው ውጤት ማምጣት ይችላሉ ሲሉ አብራርቷል:: የስፖርቱ ደረጃ መሻሻሉን የጠቀሱት አቶ ጸጋሁን፤ ውጤት እንዲመጣ ከፍተኛ ጥረት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል::
ብሔራዊ ቡድኑ በሦስቱም ምድብ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ በውድድሩ የሚካፈል ይሆናል:: የተመረጡትን ስፖርተኞች ይዞ በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ዝግጅት እንደሚያደርግም ተጠቁሟል:: የመጀመሪያው የስልጠና ምዕራፍ ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣ ሁለተኛው የዝግጅት ምዕራፍ ደግሞ ከመስከረም 1ቀን እስከ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም የሚደረግ ይሆናል::
ብሔራዊ ቡድኑ የሚሰለጥነው በአንድ ዋና አሰልጣኝና በሁለት ረዳት አሰልጣኞች በመታገዝ ሲሆን፤ ስፖርተኞቹን ያስመረጡ ክለቦች አሰልጣኞችም በተባባሪ አሰልጣኝነት ይሳተፋሉ:: ለዝግጅቱ የሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀት ተዘጋጅቶም ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንደተላከም ተነግሯል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2015