የዓመቱ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ሁለተኛ መዳረሻ ከተማ በሞሮኮዋ ራባት ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል። በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ስኬታማ ሆነዋል። ከ14ቱ የዳይመንድ ሊግ መዳረሻ ከተሞች መካከል አንዷ እና በአፍሪካም ውድድሩን በብቸኝነት በምታስተናግደው ራባት በርካታ የዓለም ቻምፒዮኖች በተለያዩ ርቀቶች ተሳትፈዋል።
ከእነዚህ ርቀቶች መካከል አንዱ በሆነው 1ሺ500 ሜትር የሴቶች ውድድርም አስቀድሞ እንደተጠበቀው ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ተከታትለው በመግባት የበላይነቱን መያዝ ችለዋል። በመካከለኛ ርቀት የወቅቱ ምርጥ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ደግሞ የዚህ ውድድር አሸናፊ ሆናለች። ያለፈው ዓመት የቤልግሬድ የዓለም ቤት ውስጥ ቻምፒዮናዋ አትሌት ጉዳፍ በውድድሩ ላይ ከተሳተፉት አትሌቶች መካከል የተሻለ ቅድመ ግምት ያገኘች ሲሆን፤ በቅርቡ በኦሪጎን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በዚህ ርቀት የብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗም ይታወቃል።
የ5ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮናዋ ጉዳፍ በራባት በተካሄደው ውድድር ከመነሻው አንስቶ ለአሸናፊነት እንደምትሮጥ የመጀመሪያውን ዙር የአሸፈነችበት 1:01.3 የሆነ ሰዓት ያመላክት ነበር። አትሌቷ በዚህ ርቀት ልምድ ያላትና በበርካታ ውድድሮች ስኬታማነቷን ያረጋገጠች ሲሆን፤ እአአ 2021 ላይም በፈረንሳይ ሌቪን በተደረገ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና 3:53.09 በሆነ ሰዓት በመግባት በርቀቱ የዓለም የቤት ውስጥ ክብረወሰንን መስበሯ የሚታወስ ነው። በዚህም አትሌቷ እንደተጠበቀው ከውድድሩ መነሻ አንስቶ በፍጥነት በመሮጥ 3:54.03 በሆነ ሰዓት አሸናፊ ሆና መፈጸም ችላለች።
ከዓለም ክብረወሰኑ በአንድ ሰከንድ በመዘግየት ያስመዘገበችው ይህ ሰዓትም በርቀቱ የአፍሪካውያን ምርጡ ሰዓት በሚል ተይዞላታል። ጉዳፍ የአገሯን ልጆች አስከትላ ውድድሩን በበላይነት መጨረሷን ተከትሎም በሰጠችው አስተያየት ‹‹ይህ በዚህ ዓመት የተሳተፍኩበት የመጀመሪያው ከቤት ውጪ ውድድር ነው። በማሸነፌ እጅግ ብደሰትም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቤ ደግሞ ይበልጥ ተደስቻለሁ። ከጉዳት ውጪ በጥሩ አቋም ላይ እገኛለሁ፤ ስለዚህም ሁሉም እንዳሰብኩት ነው›› ብላለች።
ወጣቷ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ ከጉዳፍ ሦስት ሰከንዶችን ዘግይታ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች። በዩጂን ዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒኮ በዚህ ርቀት ለአገሯ ዲፕሎማ ያስገኘችው አትሌት ፍሬወይኒ ከምርጥ ተተኪ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። በዚህ ውድድር ላይም አቅሟን በሚያስመስከር 3:57.65 የሆነ ሰዓት ልታስመዘግብ ችላለች። የገባችበት ሰዓትም ሁለተኛው የግሏ ምርጥ ሰዓት ነው።
ሌላኛዋ የ17 ዓመት ታዳጊ አትሌት ብርቄ ሃየሎም ደግሞ የአገሯን ልጆች ተከትላ በመግባት ሦስተኛውን ደረጃ ይዛለች። እጅግ ተፎካካሪ የሆነችው ይህች ወጣት አትሌት ሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም በአንድ ማይክሮ ሰከንድ ብቻ ተበልጣለች። ባለፈው ዓመት በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች ቻምፒዮና ላይ ርቀቱን 4:04.27 በሆነ ሰዓት በመግባት ተተኪነቷን ማስመስከሯም የሚታወስ ነው። የመጀመሪያዋ በሆነው በዚህ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ደግሞ 3:57.66 በሆነ ሰዓት በመግባት ተስፋዋን አሳይታለች። በ800 ሜትር ተሳትፎዋ የምትታወቀው አትሌት ወርቅነሽ መለሰ በበኩሏ 4:01.81 በሆነ ሰዓት በመግባት አራተኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች።
በራባት ዳይመንድሊግ ውድድር ከተካሄደባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ በሆነው የወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ወንዶችም አትሌት ጌትነት ዋለ ውጤታማ ሊሆን ችሏል። በዚህ ርቀት የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኘው ሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ ሲሆን፤ እንደተጠበቀውም ተሳክቶለታል። በአገሩና በደጋፊዎቹ ፊት የሮጠው ይህ አትሌት ለረጅም ዓመታት 3ሺ ሜትር መሰናክልን በመሮጥ ከፍተኛ ልምድ አካብቷል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በዩጂኑ የዓለም ቻምፒዮና አሸናፊ የነበረው ይህ አትሌት 7:56.68 በመግባት የርቀቱ የበላይ መሆን ችሏል።
ኢትዮጵያዊው አትሌት ጌትነት ዋለ ደግሞ 8:05.15 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል። ለረጅም ዓመታት በዚህ ርቀት በመሮጥ የሚታወቀው ጌትነት ዋለ እአአ በ2019 የዳይመንድ ሊግ ቻምፒዮን መሆን ችሏል። አትሌቱ በዓለም ቻምፒዮናዎች እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒክ አገሩን በመወከልም ዲፕሎማ ማግኘቱ ይታወቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2015