የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት አምስት ዓመታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል። በዚህም ኢትዮጵያ ለአገሪቱም ሆነ በአካባቢው አገራት የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር፣ ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላም እና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በምትከተለው የትብብር እና የሠላም ዲፕሎማሲ መርህ መሠረት፤ በዓለም ዙሪያ ካሉት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ ላይ ነች። ኢትዮጵያ ከአህጉሪቱ አልፎ በተለይም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር የጀመረችው መልካምና ጠንካራ ግንኙነት ከአገሪቱ ዘላቂ ጥቅም አኳያ እየተቃኘ ቀጥሏል። እንዲሁም ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በተደጋጋሚ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉብኝቶች የታጀበ እና መልካም የሚባል ሆኖ ቀጥሏል።
በአገሪቱ በሰሜኑ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ለበርካታ ወራት እጅግ ተዳክሞ የነበረው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአሁኑ ወቅት ማንሰራራት እያሳየ ይገኛል። መንግሥት ከሕወሓት ጋር የሰላም ድርድር ካካሄደ እና ጦርነቱ በሰላም ከተቋጨ ወዲህ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቆ የነበረው የኢትዮጵያ እና የውጭው ዓለም ግንኙነት ወደ መደበኛ ግንኙነት ተመልሷል፤ በአሉታዊ ጎን የቆሙትን የማለዘብና ወዳጅን የማብዛት ሥራ በመሥራት የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የማሳደግ እንቅስቃሴው ውጤት ማሳየቱም ይገለፃል።
የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኙ አቶ አትክልት አጥናፉ እንደሚናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ግንኙነት አገራት ከአገራት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ቋሚ ጥቅማቸውን በዘላቂነት ማስጠበቅ ላይ የተመሠረተ ነው። ይሁን እንጂ ከቋሚ ወዳጅ ይልቅ ትኩረት የሚሰጠው ቋሚ ጥቅም የሚባለው መርህ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ከዚያ ወጣ ባለ መንገድ አገራት የራሳቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይኖራቸዋል፤ ከሕገ መንግሥቱ የተቀዳና እርሱን መሠረት በማድረግ የውጭ ፖሊሲያቸውን ለማሳካት የአጭር እና የረዥም ስትራቴጂ ይኖራቸዋል።
ስትራቴጂው ከመልካምድር አቀማመጥ ቅርበት፣ የንግድ፣ የፖለቲካ፣ የዜጋ ለዜጋ ግንኙነቶች ላይ መሠረት ያደረገ ሊሆን ይችላል። እነዚህ እንዳሉ ሆነው በአንድ ጉዳይ ላይ አገሪቷ የውስጥ አቋሟ ወይም የውስጥ ፍላጎቷ ወይም አገራዊ፣ ፖለቲካዊና በራሷ አስተዳደር ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ጫናዎችን ተቋቁማ መሰለፍ ስትችል፤ የአገሪቷን የውስጥ ጥንካሬ የተቋማት ጥንካሬ እንዲሁም ደግሞ የመተግበር አቅም ሲኖራት፤ ከዚያም ባሻገር በዲፕሎማሲ የመደራደር አቅሟን ጭምር የሚያሳይ ተቋማዊ አቅም ሲኖራት አንዲት አገር ጠንካራ ዲፕሎማሲ ገንብታለች ለማለት ያስደፍረናል ይላሉ።
ወጥ የሆነ መለኪያ ባይኖርም አገራት በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ ያንን ተቋቁመው የማለፍ አቅማቸው እንደ አንድ ጉዳይ ይታያል። በሁለተኛነት ያነሱት፤ የኢኮኖሚ ጥንካሬን ነው። አገራት በጦርነት፣ በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ ርሃብና ተያያዥ ፈተናዎች ሲያገጥማቸው ዜጎች ችግር ውስጥ ሳይገቡ ወይም ደግሞ ለሌላ እርዳታ ሳይገለጡ በእራሳቸው አቅም መሸከም ሲችሉ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬ እንደሚታይ ይናገራሉ።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ መምህሩ ሙሉዓለም ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ በዋናነት አንዱ ከሌላ አገር ጋር፣ አገራት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ዓለም አቀፍ ግንኙነት የጋራ ጥቅም መሠረት በማድረግ ይመሰርታሉ። ይህ የጋራ የኢኮኖሚ ጥቅም ሊሆን ይችላል። ግንኙነቱ ፖለቲካዊም ማህበራዊም አሊያም በሌሎች ዘርፎች ላይ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የምንለው ይሄንን ዓይነት ግንኙነት ነው።
አንዲት አገር ከተቀረው ዓለም ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላት የሚባለው መቼ ነው? የሚለውን ስናይ የዓለም አቀፍ ግንኙነትን ሁለት ነገሮች ይወስኑታል፤ አንደኛው ውስጣዊ ሲሆን፣ ሁለተኛው ውጫዊ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ። ውስጣዊ ሲባል ኢትዮጵያ ያለችበት ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ሊሆን ይችላል። አካባቢያዊ ሁኔታውም ወሳኝ ነው ተብሎ ይታሰባል። ውጫዊው ስንል ደግሞ በዋናነት አሰላለፉ ምን ይመስላል የሚለው ዋናው እና መሠረታዊ ተብሎ ይወሰዳል። ዓለምን እየመራ ያለው አገር የትኛው ነው? አንድ አገር የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆነው ከማን ጋር ቢሰለፍ ነው? የሚለውን ተሳቢ ማድረግ እንደሚያፈልግ ይናገራሉ።
አቶ አትክልት እንደሚሉት፤ የአንድ አገር የውጭ ጥንካሬ የሚመጣው በውስጥ ከፍተኛ አቅም ሲፈጠር ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደሚታወቀው የሚመነጨው ከውስጥ ወደ ውጭ ነው። ይህ ማለት ውስጣዊ የማድረግ አቅም በዓለም አቀፍ መድረክ ለሚኖር ግንኙነት እንደ አንድ መነሻና ስትራቴጂ ተደርጎ የሚያዝ ነው። ስለዚህ በኢኮኖሚ፣ በጦር አቅም እንዲሁም ደግሞ ዓለም አቀፍ የፕሮፖጋንዳ ጫና ተቋቁሞ ማለፍ እንደ አንድ ተቋማዊ አቅሞች ማሳያ ወይም የአንድ አገር ዓለም አቀፍ ግንኙነቷ ጥንካሬ አለው ለማለት እንደ ማሳያ የሚወሰድ ነው።
ከኢትዮጵያ አንፃር ላለፉት ሁለት አመታት ጦርነት ውስጥ እንደነበርን ይታወቃል፤ የእርስ በእርስ ግጭቶች ለውጫዊ ኃይሎች ፍላጎት መነሻ ይሆናሉ። ለብሔራዊ ደህንነት ጭምር አቅምን የሚፈታተኑ የአገሪቷን ኢኮኖሚ፣ ገፅታ፣ የመፈፀም አቅም ያዳክመሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣው ቀውስ ቀላል አይደለም። ጦርነት በባህሪው ይዞት የመጣው መዘዝ አለ። የጦርነት ውጤት የሚባሉ ከኢኮኖሚ እስከ የሰው ልጅ ሕይወት የሚያደርሰው ጉዳት ትልቅ ነው።
የእርስ በእርስ ጦርነት ሲሆን ደግሞ በሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት በሁለቱም ወገን ኢኮኖሚ የሚያደርሰው ቀውስ የከፋ ነው። ይህ ደግሞ የአገሪቱን አቅም ያዳክማል፤ የሰው ኃይል ይጠፋል፤ በዚህ ሂደት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሉ በሚል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ትችች ያስከትላሉ፤ ሲያከትሉም ነበር።
እንደ አቶ አትክልት አባባል፤ አንዳንድ አገራት ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በአገራት ላይ ጣልቃ ለመግባት እንደ መነሻ ይጠቀማሉ። በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው እንኳን ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ እነርሱን ለመከላከል በሚል በአገራት የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን ለማስገባት የሚፈልጉ አገራት እንደ ስትራቴጂ ጭምር ይጠቀማሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ቀድሞ የነበራት መልካም ስም እና አገራዊ ቁመና በተቃራኒው የተወሩበት ወቅት ነበሩ፤ እነዚህን መነሻ በማድረግ የራሳቸውን ተጓዳኝ ፍላጎት ለማሳካት ጥረት የሚያደርጉ አገራት ነበሩ ይላሉ።
እንደሚታወቀው ደግሞ ኢትዮጵያ ካለችበት ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቃሜታ አንፃርና ቀጣናው ላይ ከነበራት ሚና በመነሳት አትዮጵያ ላይ የሚፈጠረው አለመረጋጋት ቀጣናው ላይ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር አድርገው ስለሚያስቡ እነዚህን መነሻ በማድረግ በአንድም በሌላም ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ነበር። እርሱ ሰይሳካ ሲቀር ደግሞ የአገሪቷን ገፅታ የማጠልሸት ድርጊቶች ብርቱ እንደነበሩም ተናግረዋል።
አቶ አትክልት ፣ ከጦርነት መልስ የነበረውና አገሪቷ እንደገና የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት ባደረገችው ጥረት ትልቅ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል። በተለይ የመልሶ ግንባታ ሥራና ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተኬደበት ርቀት ይበል የሚያሰኙ ነበሩ። ይህ ሁሉ አካሄድ በዓለም አቀፍ መድረክ እውቅና ተሰጥቶት ስለነበር፤ የነበሩ ማዕቀቦች በሂደት መቅረት ችለዋል። ከትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደየዓለም የንግድ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረት ከእነዚህ ተቋማት የምናገኛቸው የብድር፣ የድጋፍ ለታዳጊ አገራት ይደረግ የነበሩ ድጎማዎች ተስተጎጉለው ቢቆዩም አሁን ወደነበረበት ስለመመለሱ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ጥረት ጨምሮ በተደጋጋሚ በተደረጉ ጥረቶች ውጤቶች እየታዩ ነው። እነዚህ እንደ እድገት ይታያሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ሙሉዓለም በበኩላቸው ሲናገሩ፤ ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ለሰላም ስምምነቱ ድጋፍ በማድረጉ ግንኙነቱን ወደነበረበት ለመመለስ ተችሏል ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራር ወደተለያዩ ሀገራት በመጓዝ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ሰፋፊ ውይይቶች ተደርገዋል። የዓለም አቀፍ ተቋማትን በርም በተደጋጋሚ አንኳኩተናል፤ እነርሱም በጎ ምላሽ ሰጥተውናል። ዲፕሎማሲው ተሻሽሏል መባሉ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ ግን ከዚህ በላይ መሻሻል አለበት።
አቶ ሙሉዓለም እንደሚሉት፤ እንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ቋሚ ወዳጅ ሆነ ቋሚ ጠላት ስለሌለ ሁኔታው ሊቀያየር ይችላል። ስለዚህ ጊዜው እንደሚፈቅደውና እንደ ሁኔታው ከተለያዩ አገራት ጋር ግንኙነት መፍጠሩ መልካም ነው። ኢትዮጵያን በተመለከተ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ አንዳንድ አገራት ጋር ከሁሉም ጋር ባይሆንም የነበራት ግንኙነት ሻክሮ ነበር። ኢትዮጵያ ለአሜሪካና ለምዕራቡ ዓለም ስትራቴጂካዊ አገር እንደመሆኗ ከእነዚህ አገራት ጋር የነበራት ግንኙነት መልካም አልነበረም። ለዚህ ማሳያው ለኢትዮጵያ በሚሊዮን ዶላር ይሰጡ የነበረውን ድጋፍ እና ዕርዳታ እስከ ማቋረጥ ደረሰው ነበር፤ ይህ ደግሞ ያደረሰው ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም።
በየጊዜው የሚለያይ ቢሆንም አሁን ባለው ደረጃ ዓለም ከ‹‹unipolar›› ማለትም አንድ አገር ዓለምን ከምትመራበት ወደ ብዙ አገር ‹‹multipolar›› የመሆን ሁኔታ እየተፈጠረ ስለሆነ አንድ አገር ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን ወደ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ እየመጡ ካሉ የተለያዩ አገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር የግድ የሚልበት ወቅት ስለመሆኑ አቶ ሙሉዓለም ያስረዳሉ። ከኢትዮጵያ አንፃር ደግሞ ከጎረቤት አገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመስረት አለበት ተብሎ ይታሰባል። ምክንያቱም በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች መሠረት ተደርጎ የሚመሠረተው ግንኙነት ጠንካራ መሆን ፋይዳው ትልቅ እንደሆነም ያመለክታሉ።
በአጠቃላይ ከተቀረው ዓለም ጋር ጠንካራ ግንኙነት በተመሠረተ ቁጥር የአገር ተጠቃሚነት እየሰፋ ብሔራዊ ጥቅም እየተከበረ የሚሄድበት ዕድል ሰፊ ነው የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፣ በአሁኑ ጊዜ ለብቻ ሆኖ ሁሉንም ነገር የሚጋፈጡበት እንዳልሆነ ይገልጻሉ። በተቻለ መጠን ግንኙነት መፍጠርና ከሌሎች አገራት ጋር በትብብር መሥራት በተለይ ወሳኝ ከሆኑ አገራት ጋር አሰላለፉን እየተመለከቱ ዲፕሎማሲያዊ ህብረት መመስረት የግድ ነው ይላሉ። ምክንያቱም ግንኙነቱ በተጠናከረ ቁጥር ኢንቨስትመንት የመሳብ ዕድል እየሰፋ ይመጣል። ይህ ደግሞ ይዞት የሚመጣው በርካታ በረከት አለ፤ ከንግድና ቱሪዝም አንፃር ከተመለከትነውም ኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣው በጎ ተፅዕኖ እጅግ የላቀ ነው ብለዋል።
ይህ የዲፕሎማሲ መሻሻል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በምን መልኩ ይሠራ? ከማን ምን ይጠበቃል? የሚለውን አቶ ሙሉዓለም ሲናገሩ፤ አሁን መንገዱ እየተቀየረ መጥቷል ብለዋል። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚጠናከረው መንግሥት ከመንግሥት ጋር በአንድ መንገድ በሚያደርገው ግንኙነት ብቻ አይደለም። ይህ አንዱ መንገድ ነው። መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ከተቀረው ዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ሂደት ውስጥ የጎላ ድርሻ ሊወጣ ይገባል። ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችም ኢትዮጵያ ያላት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም፣ አቅም ለተቀረው ዓለም በደንብ ማስተዋወቅ ከቻሉ ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች ትሄዳለች በማለትም አስረድተዋል።
ከዚያ በፊት መቅደም ያለበት ግን መንግሥት በየአገሩ የሚልካቸው አሊያም የላካቸው ዲፕሎማቶች ተልዕኳቸውን በአግባቡ ስለመወጣታቸውና እየተወጡ ስለመሆናቸው መጤን አለበት ይላሉ። በየአገሩ የተቀመጡ አምባሳደሮቻችን እንዲሁም ዲፕሎማቶቻችን ባሉበት አገር ያለውን ሀብት እንዲንቀሳቀስ ከማድረግ አኳያ ምን እየተሠራ ነው ብለን ብንጠይቅ ያን ያህል አመርቂ ነው ማለት አይቻለንም ሲሉ ይናገራሉ።
ትልልቅ የቢዝነስ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ መንግሥት መሄድ ያለበትን ርቀት ሁሉ መሄድ አለበት። በየአገሩ ያሉ አምባሳደሮቻችን እነዚህን ተቋማት አሳምነው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያውን እንዲያፈሱ ለማድረግ መሄድ የሚገባቸውን ያህል ርቀት መሄድ አለባቸው።
ሌላው ትልቅ ነገር ብለው አቶ ሙሉዓለም ያነሱት፤ አንድ እና ሁለት አጋር አገር ከሚል አባባል ወጥተን ፍላጎት ካለን ከየትኛውም አገር ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለብን ነው። ይህ በእርግጥ የሚከናወነው ባለን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን መሠረት ነው። እንዲያም ሆኖ ከአሜሪካና ከምዕራቡ ዓለም በተቃራኒ ከቆሙ ከቻይና ወይም ከሩሲያ ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር አለብን። ለዚህም መንግሥት እየሠራ ያለውን ሥራ በትኩረት አጠናክሮ መሥራት አለበት ብለዋል።
ምሁራኑ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ውስጥ የነበረው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ የተፈታበት ሂደት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ኢንቨስትመንት መልካም አጋጣሚ ሆኖ መጥቷል። ስለዚህ ፋይዳው እንደአገር ዘርፈ ብዙ ነው። ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ፈተናዎች ሲገጥሙን ለመቋቋም የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት አለብን። በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በቀጣናው የበረታ ሚና እንዲኖረን አቅም ይሆናሉ። ስለዚህ አገሪቱ ቀጣይነት ላለው ጥንካሬዋ አገራዊ የውስጥ አቅም ግንባታ ላይ መሥራት የግድ ይለታል። ፈተናዎች ከመምጣታቸው በፊት አሁን መሥራት አገሪቱ ፈተና ሲገጥማት ተቋቁማ ማለፍ እንድትችል አቅም ስለሚሆኑ በትኩረት መሥራት ተገቢ ነው።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2015