የአገራችን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ከኋላቀር አስተራረስና አመራረት ተላቅቆ የሚዘመንበትን ጊዜ በጉጉት ስንጠብቅ ኖረናል። የአገሮችን ግብርና ዘርፍ ሲያዘምኑ በተለያዩ መረጃዎች የተመለከትናቸውን ቴክኖሎጂዎች በተለይ ለግብርናው ዘርፍ ቅርበቱ ያላቸው አካላት ምነው ለእኛ ባደረጋቸው ብለው ሲመኙ ቆይተዋል።
ሩቅ አድርገን ያሰብናቸው ቴክኖሎጂዎች ጊዜው ደርሶ እነሆ በአሁኑ ወቅት በእኛው መዳፍ ውስጥ መግባት ጀምረዋል። በርካታ ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ዓይነቶችን በአርሶ አደሮች ማሳ መመልከት ውስጥ ገብተናል። በሳይንስ ሙዚየም ለሳምንታት ለሕዝብ ክፍት ተደርጎ የታየው እና እየታየ ያለው የግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ድግስ ለዚህ ሌላው ሕያው ምስክር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በአውደ ርእዩ የቀረቡት ቴክኖሎጂዎች በግብርናው ዘርፍ ሥራ ላይ የዋሉና ግብርናው በቴክኖሎጂ መለወጥ መጀመሩን የሚያሳዩ ናቸው፤ ለእዚህ ለውጥ መሣሪያ ሆነው ያገለገሉትን ቴክኖሎጂዎች የግብርናው ዘርፍ ተዋንያን ተመልክተው እንዲያሰፏቸው፣ ይበልጥ አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲያደርሷቸው የሚያደርጉም ናቸው።
«ከቤተ ሙከራ ወደ አዝመራ» በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው ይህ የግብርና የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ፣ ግብርናውን ሊያዘመኑ የሚችሉ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከየዓይነቱ ቀርበውበታል። በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ቴክኖሎጂዎች የአገራችንን ግብርና የሚያዘመኑ ከመሆናቸውም ባሻገር ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ እያደረገች ያለችውን ጥረትና ቴክኖሎጂው በአገሪቱ የደረሰበትን ደረጃ ያመለክታሉ።
በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ግብርናውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውን ገልጸዋል። የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ግብርናውን በቴክኖሎጂ ማዘመን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አውደ ርዕዩ ግብርና ከተለያዩ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳየና የግብርና ሳይንሳዊ አጠቃቀምና አተገባበር ላይ ትምህርት የሚገኝበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ማነቆ የሆኑትን የአፈር ለምነትና ሌሎች ችግሮችን ሳይንሳዊ መንገድ በመከተል መፍታት ይገባል ብለዋል።
በአውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ፣ የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ሊቆጠቡ የሚችሉ በርካታ ቴክኖሎጂዎች፣ የፈጠራ እና የምርምር ውጤቶች ቀርበዋል። ከእነዚህ ውስጥ «ዓባይን በጭልፋ— » ይሉት ዓይነት ነገር ቢሆንም፣ ‹‹ስማርት ፋርሚንግ›› እና ‹‹ቫሎን ኢሪጌሽን›› የተሰኙ የመስኖ ሥራ ለማከናወን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች እና የተቀናጀ ግብርናን ለመሥራት የሚያስችል የፈጠራ ቴክኖሎጂ በአውደ ርእዩ ከቀረቡት ቴክኖሎጂዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ቴክኖሎጂውን በአውደ ርእዩ ይዘው የቀረቡት የቢጄአይ ኢትዮ ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ኤንድ አይ ሶሊሽን ድርጅቱ አቶ ተክላይ ገብረዮሐንስ ‹‹ስማርት ፋርሚንግ›› የተሰኘው አዲስ ቴክኖሎጂ ግብርናን በማዘመን የእርሻ ሥራን በመስኖ ለማከናወን ከሚያስችሉ ቴክኖሎጂ ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ። ቴክኖሎጂው የመስኖ እርሻን ያለምንም ድካም ውሃ ለማጠጣት ያገለግላል። ሌላኛው ይዘውት የቀረቡት ‹‹ቫሎን ኢሪጌሽን›› የተሰኘው ቴክኖሎጂም እንዲሁ የመስኖ እርሻን ውሃ ለማጠጣት የሚያስችል ነው።
‹‹ስማርት ፋርሚንግ›› የተሰኘው ቴክኖሎጂ እርሻ ቦታው ላይ መገኘት ሳይጠበቅ የመስኖ እርሻ ውሃ ማጠጣት የሚያስችል ነው። ባለንበት ቦታ ሆነን ስለእርሻ ስፍራው ሙሉ መረጃ የምናገኝበት ነው ያሉት አቶ ተክላይ፤ በእርሻው ቦታ ላይ የሚገጠሙ ሴንሰሮችን በመጠቀም ሙሉ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) በመሰብሰብና ወደ ሀርድ ዌር በመላክ መረጃዎች ወደ ዌብ ሳይት እንዲገቡ የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ዌብ ሳይቱም የእርሻ ቦታውን ሙሉ መረጃዎች እንደሚጠቁም ይገልጻሉ።
‹‹የእርሻ ቦታውን የአየር ሁኔታ፣ ለምነት፣ የአፈሩን አሲዳማነትና የመሳሰሉትን በመለካት ወደ ዌብ ሳይት መረጃን የሚልክ ሶፍት ዌር ያለው ሲሆን፣ የመስኖ ሥራ ለመሥራት ማሳው ድረስ መሄድን አያስፈልግም ይላሉ። በሶፍት ዌሩ በመጠቀም አስፈላጊውን የእርጥበት መጠን ማግኘት የምንችለበት ነው። ጊዜን፣ ጉልበትንና ብክነትን የሚያስቀር በቀላሉ መተግበር የሚቻል ቴክኖሎጂ እንደሆነ ነው አቶ ተክላይ የሚናገሩት።
‹‹ስማርት ፋርሚንግ›› የተሰኘው ቴክኖሎጂ በኢንዱስትሪ ደረጃ ባሉ የእርሻ ቦታዎች ላይ የሚገጠም ሲሆን፣ እስከ10 ዲያሜትር የመለካት አቅም ያላቸው ትላልቅ ሴንሰሮች ይኖሩታል። እነዚህን ሴንሰሮች አመቺ ቦታዎች ላይ ተግባራዊ የሚቀመጡ ሲሆን፣ ሴንሰሮቹ ሁሉንም ነገር ለክተው ያለውን መረጃ(ዳታ) ተንትነው በሚያስፈልግበት ጊዜ እንደሚያቀርቡ ያስረዳሉ።
‹‹እኛ አገር ባለ የአስተራራስ ዘዴ አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን እርጥበት ለማወቅ መሬቱን መቆፈር ወይም ማየት አለበት›› የሚሉት አቶ ተክላይ፤ ይህ ቴክኖሎጂ ግን እርሻ ቦታ ላይ ያለውን የእርጥበት መጠን በትክክል የሚያስቀምጥ ከመሆኑም በላይ በውሃ መብዛት ምክንያት በሰብል ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በመከላከል ለሰብሉ በጣም አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ይላሉ። አቶ ተክላይ ምሳሌም ጠቅሰው ሲያስረዱ የአበባና የሩዝ ማሳዎችን ብንመለከት እኩል የእርጥበት መጠን እንደማይፈልጉ ተናግረው፣ እነዚህን ሰብሎች ለማልማት በባለሙያ የተጠና የእርጥበት መጠን እንዳለም ይጠቁማሉ። ቴክኖሎጂው በዚህ ለክቶ ስለሚያውቀው ቅድመ መረጃዎች እንደሚሰጥ ይገልጻሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህንን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የእርሻ መሬቱን ሲስተሙ ሊቆጣጠረው በሚችል መልኩ ማመቻቸት ያስፈልጋል። አጠቃቀሙም የመስኖ ማጠጫውን ፓምፑ ውሃ ያለበት ቦታ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ውሃውን ይረጫል። የተገጠመለት ሴንሰርም እርሻ ቦታው እርጥበት ከሌለውና ያለው የእርጥበት መጠን ከተሞላው እርጥበት ልኬት በታች ከሆነ ወዲያውኑ በራሱ ውሃ የማጠጣት ሥራውን ይጀምራል። በእርሻው ቦታ ላይ ሴንሰሩና የውሃ መስመሩ ከተገጠመ በኋላ የሚሰጠውን አገልግሎት እርሻውን የሚቆጣጠረው አካል ባለበት ሆኖ በሶፍት ዌር አማካይነት መቆጣጠር የሚያስችል ነው።
ቴክኖሎጂውን ስንጠቀም የውሃ መስመሮችን የፓምፕ አቅም ከፍ በማድረግና ሴንሰር በማብዛት እስከተፈለገው ሄክታር መሬት ድረስ ያለን የእርሻ ቦታ ውሃ ማጠጣት ያስችለናል ሲሉም አቶ ተክላይ ይገልጻሉ፤ የ‹‹ስማርት ፋርሚንግ›› የመስኖ እርሻን በዘመናዊ ዘዴ ውሃ ማጠጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የድርጅቱ የእርሻ ቦታ ባለበት ተጂ በሚባል አካባቢ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑንም ይገልጻሉ። ቴክኖሎጂው በተለይ የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ በሚገባ ውጤታማ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ማሳው የሚያስፈልገውን ያህል ውሃ እንዲጠጣ ከተደረገ በኋላ ዝናብ ቢጥልስ ውሃ ከተፈለገው መጠን በላይ ሊሆን አይችልምን ስንል ለአቶ ተክላይ ላቀርብነው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ማሳው በተፈጥሮ የሚጥለው ዝናብ ካገኘ በኋላ ውሃ መጠጣት እንደሌለበት ጠቅሰው፣ ቴክኖሎጂው በራሱ ሴንስ ያደርጋል ብለዋል። የተፈጥሮ ዝናብ የሚበዛበት ከሆነ ግን በቀጣይ ደግሞ ውሃውን መምጠጥ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲኖር ቴክኖሎጂውን በማሻሻል እንደሚሠራ ጠቁመው፤ በተለይ የበጋ ወቅት የመስኖ ልማት ሥራውን እንደሚያግዝ አመላክተዋል።
ቴክኖሎጂው ለአጠቃቀም በጣም ቀላል ምቹ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሚፈለገውን ዓይነት ምርት ለማግኘት ተመራጭ መሆኑንም አቶ ተክላይ አስታውቀዋል፤ በተለይ ባለሀብቶች ትላልቅ የእርሻ ቦታዎቻቸውን በቅርበት ለመቆጣጠር እንደሚያመቻቸው ጠቁመዋል። ሌላኛው ‹‹ቫሎን ኢሪጌሽን›› የተሰኘ ቴክኖሎጂ መሆኑን አቶ ተክላይ ጠቅሰው፣ ይህም ለመስኖ ሥራ እንደሚያገለግል ይገልጻሉ። ቴክኖሎጂው ከ‹‹ስማርት ፋርሚንግ ›› የተሻለ እንደሆነም ነው አቶ ተክላይ የሚገልጹት።
እሳቸው አንደሚሉት፤ ‹‹ቫሎን ኢሪጌሽን›› እንደ ‹‹ስማርት ፋርሚንግ ›› ቦታው ላይ ቦይና ሌሎች ሴንሰሮች አያስፈልጉትም። ቫሎኑን አየር ላይ በሂልየም ጋዝ በመሙላት የውሃ መስመር እንዲሸከም ይደረጋል። ከዚያ በኋላ በማንጠልጠል አየር ላይ እየተጎተተ የእርሻ ማሳን ውሃ እንዲያጠጣ ይደረጋል። በቫሎን የመስኖ ውሃ ለማጠጣት የመሬት አቀማመጥ ማመቻቸትን የሚጠይቅ አለመሆኑ ጠቁመው፤ የመሬት አቀማመጡ የፈለገው ዓይነት አይደለም። የቫሎን ቴክኖሎጂ ልክ እንደ ድሮን አየር ላይ የሚንቀሳቀስ ስለሆነ ከስር በሁለት በባጅጅ እየተጎተተ በአየር ላይ ሆኖ የእርሻ ማሳውን ውሃ ለማጠጣት ያስችላል።
ቴክኖሎጂውን ለመሥራት መነሳሳት የፈጠረው የአገቱን የእርሻ ሥራ በማዘመን ምርትና ማርታማነትን ለመጨመር ማሰብ መሆኑን ነው አቶ ተክላይ የገለጹት። ቀደም ሲል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች፣ የእህል ማበጠሪያ ማሽኖችና የመሳሰሉት ሲያመርቱ ተጠቃሚዎች ማሽኖች ገዝተው ለመጠቀም የግብዓት እጥረት ይገጥማቸው እንደነበር አስታወሰው፤ ይህንን መነሻ በማድረግ የእርሻ ሥራችንን ብናዘምነው እንዲህ ዓይነት እጥረት አይፈጠርም በሚል ቴክኖሎጂውን ለመሥራት መነሳሳታቸውን ይገልጻሉ።
ሌላኛው የተቀናጀ ግብርና ሥራን የሚያሳይ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ይዘው የቀረቡት የግብርና ሚኒስቴር የዓሣ ሀብት ልማት ዲስክ የዓሣ ባለሙያ አቶ አደፍርስ ካሳዬ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ቴክኖሎጂ ከዝዋይ ዓሣ ምርምር ማዕከል ጋር በትብብር የተሠራ ሲሆን፣ ዶሮዎች ወይም ሌሎች እንስሳት፣ ዓሣ እና አትክልት(ሰብል) ልማትን በአንድ ላይ አቀናጅቶ ማካሄድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ በሞዴልነት የቀረበው የፈጠራ ሥራ በቅድሚያ ዶሮዎች ወይም ሌሎች እንስሳትን ለማርባት የሚያስችል ቆጥ መሳይ ክፍል ይሠራል፤ ቆጡ ስር ዓሣ የሚረባበት ውሃ እንዲኖር ይደረጋል፤ ዓሣ ወደሚኖርበት ውሃ ሲለቀቅ ደግሞ በቀጥታ ለጓሮ አትክልቶች (ሰብሎች) እንደ መስኖ ሆኖ እንዲያገለግል ይደረጋል። ዶሮዎች ካሉበት ክፍል ወደ ውሃ ውስጥ የወደቀውን የዶሮዎች ኩስ አንዳንድ ዓሣዎች በቀጥታ ይመገቡታል፤ ሌላው ደግሞ ለመሬቱ ማዳበሪያ ሆኖ ስለሚያገለግል እዚያ ውስጥ ጥቃቅን እንስሳትና አትክልቶች እንዲበቅሉ የሚረዳ ነው። አትክልት እና ጥቃቅን እንስሳትን የሚመገቡ እንዲሁም ሁለቱንም የሚመገቡ ዓሣዎች መኖራቸውን ነው አቶ አደፍርስ ያብራሩት።
ከዚህም በተጨማሪ ወደ ውጭ የሚፈሰው ውሃ ወደ ማሳ ተለቆ አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎችና ሌሎች አዕዝርት ማልማት ያስችላል። ከዶሮ ኩሱና ከዓሣዎች በተለያየ መልኩ የሚወገዱ ነገሮችም እንዲሁ ለአትክልቶቹ እንደማዳበሪያ ሆነው ያገለግላል ሲሉ ያብራራሉ።
ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ በእኛ አገር ከተጀመረ ቅርብ ጊዜ እንደሆነው ጠቅሰው፣ አንዳንድ አርሶ አደሮች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፤ ቴክኖሎጂው ለንግድ ሥራም ሆነ ለቤት ውስጥ የምግብ ፍጆታ ልንጠቀምበት እንችላለን ሲሉ አቶ አደፍርስ ይገልጻሉ። ቴክኖሎጂውን እንደአስፈላጊነቱ መሥራት እንደሚቻል ጠቅሰው፣ በመቶ ስኩየር ካሬሜትር ቦታ ላይ ከ30 እስከ 50 ዶሮዎች ድረስ ማስገባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፤ ዶሮዎቹን እንቁላል ለማግኘት ወይም ለምግብነት ለመጠቀም እና ዓሣውን ለመሸጥ ወይም ለራስ የምግብ ፍጆታ ማዋል ይቻላል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የተቀናጀ ግብርናን ማካሄድ የሚያስችለው ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ውሃው ሲወጣም ሆነ ሲገባ በምንም ዓይነት መልኩ አካባቢ አይበክልም። ዓሣዎች ያሉበት ውሃ እየተለቀቀ እንደገና ሌላ ውሃ ገብቶበት የሚታደስ ሲሆን፣ የሚለቀቀው ውሃ ደግሞ ወደ አትክልቶቹ እና ሰብሎቹ እንዲጠጡት እየተደረገ ማዳበሪያ ሆኖም የሚያገለግል ነው። ለዚህ ሥራ የሚሆነው ቦታ የሚመረጥ ሲሆን፣ ቦታው ተዳፋት የሆነ ወንዝ ያለበት ወይም ከከርሰ ምድር በፓምፕ የሚወጣ ውሃ ያለበት ቢሆን ይመረጣል። ዓሣዎችም እንዳይጎዱ ውሃው በተከታታይነት መቀየር ይኖርበታል፤ ውሃውን ለመቀየር የሰው ጉልበት እንዳይጠይቅ በመሬት ሰበት እንዲፈስ ይደረጋል።
በአካባቢ ላይ ብክለት ሊያደርሱ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን አሉታዊ ተጽእኖ መቀነስ እንደሚገባ ተናግረው፣ የተቀናጀ የግብርና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን በማሳደግ ብክነትን መቀነስና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል አስታውቀዋል። አርሶ አደሩም ይህን ቴክኖሎጂ በተወሰነ መልኩ እየተጠቀመበት መሆኑንም ይገልጻሉ። አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ግብርናውን እንዲያዘምን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
መንግሥት ግብርናውን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቶት እየሠራ ነው የሚሉት አቶ አደፍርስ፣ በግብርና ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ስልጠናዎችና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሰጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በክልል ደረጃም የዓሣ ሀብት ባለሙያዎች ለኅብረተሰቡ ሙያዊ ድጋፎች እያደረጉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2015