የወርልድ ቴኳንዶ የዓለም ቻምፒዮና ከዛሬ ግንቦት 21 እስከ ግንቦት 26/2015ዓም በአዘርባጃኗ ባኩ ከተማ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል:: ከ144 ሀገራትና የስደተኛ መጠለያዎች የተወጣጡ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ውድድራቸውን ያደርጋሉ:: ኢትዮጵያም ከተሳታፊዎቹ አንዷ ስትሆን በሁለት ወንድ አትሌቶች በመወከል ተሳትፎዋን ታደርጋለች::
ውድድሩን ለሚያሸንፉና ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ለሚችሉ አትሌቶች ለኦሊምፒክ ማጣሪያ ብቁ የሚያደርጋቸውን ደረጃ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል:: ቻምፒዮናው ለ26ኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን፤ በአዘርባጃን ሲካሄድ ደግሞ የመጀመሪያው ነው:: ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያት ያልተሳተፈችባቸው ጊዜያት ቢኖሩም በዘንድሮው ውድድር ለ9ኛ ጊዜ ትሳተፋለች:: በአሰልጣኝ አዲሱ ኡርጌሳ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥቂት ዝግጅት በማድረግ ወደ ውድድሩ ስፍራ ሽኝት ተደርጎለታል:: ውድድሩ በ16 የክብደት ምድቦች ተከፍሎ ይካሄዳል::
ኢትዮጵያ በሰለሞን ቱፋ 54 ኪሎ ግራም እና ሰለሞን በጋሻው 68 ኪሎ ግራም የምትካፈል ይሆናል:: በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዝ በኦሊምፒክ ተሳትፎ ልምድን ያካበተው ሰለሞን ቱፋ እና በተለያዩ የአፍሪካና ሌሎች የውድድር መድረኮች የተሳተፈው ሰለሞን በጋሻው ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው ወደ ስፍራው አምርተዋል::
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ በቀረው እና በኋላ በእንግሊዝ በተካሄደው የዓለም ቻምፒና ደግሞ ቪዛ በመከልከሏ ለሁለት ቻምፒናዎች ተሳትፎን ማድረግ አልቻለችም:: በዘንድሮ ውድድርም የማትሳተፍ ከሆነ ከዓለም አቀፉ የቴኳንዶ ፌዴሬሽን የሚደረግላትን ጥቅሞች ለማግኘት ተሳትፎ በማስፈለጉ ብሔራዊ ቡድኑ በጥቂት አትሌቶች ሊወከል ችሏል::
ቡድኑ ለስልጠና ካምፕ ያልገባ ሲሆን በሁለቱ ልምድ ያላቸው ስፖርተኞች ለመሳተፍ ተወስኖ፤ ባላቸው ብቃት ተመርጠው ለአንድ ወር ገደማ ዝግጅት በማድረግ ወደ ወድድሩ ቦታ መሄዳቸውን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አስታውቋል:: ሰለሞን ቱፋ ለ15 ቀናት ወደ አሜሪካ አቅንቶ ለውድድሩ ዝግጀት ማድረግ ችሏል:: ሰለሞን በጋሻው ደግሞ በብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አማካኝነት ለአንድ ወር ያክል የዝግጀት ስልጠናን አከናውኗል::
በቴኳንዶ ስፖርት በኦሊምፒክና አለም ቻምፒዮና መድረኮች ኢትዮጵያን በመወከል ውጤታማና ልምድን ያከበተው ሰለሞን ቱፋ በኦሊምፒክ መድረክና በማጣሪያ ውድድሮች ላይ በገጠመው ጉዳት ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ርቆ ቆይቷል:: በተደረገለት ህክምና ከጉዳቱ በማገገም ወደ ልምምድ በመመለስ ብቁ በመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑን ሊወክል ችሏል:: ከጉዳቱ በማገገሙ ወደ አሜሪካ በመጓዝ የስልጠና እና ወድድር እድልን በማግኘት ለአንድ ወር ያህል ዝግጅቱን በሚገባ አከናውኗል:: አትሌቱ ካለው ልምድ፣ ከጉዳት ነጻ በመሆኑና ካደረገው ዝግጅት አኳያ ውጤት እንደሚያመጣም ይጠበቃል::
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ብሔራዊ ቡድኑ ካምፕ ገብቶ ሰፊ ዝግጅት ያላደረገበትንና በሁለት አትሌቶች ብቻ የመወከሉን ምክንያት ያብራራሉ:: በዚህም ያሉት ስፖርተኞች በቂ ልምድ የሌላቸውና ካምፕ ገብተው በደንብ ባለመዘጋጀታቸው ነው:: በመሆኑም በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ልምድ ያላቸውን ተወዳዳሪዎች መወከሉ የተሻለ ይሆናል ከሚለው እንደሆነ አስረድተዋል::
እንደ አቶ ፍቅሩ ለብሔራዊ ቡድኑ በብዙ ተወዳዳሪ አለመወከልና ካምፕ ገብቶ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ አለመቻል እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው የአለም ቻምፒና የሚደረግበት ጊዜና ቦታ መለዋወጥ ነው:: እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የት እንደሚደረግ እና መቼ እንደሚደረግ አለመታወቁ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ሰፊ ዝግጅት እንዳይደረግ እንቅፋት ፈጥሯል:: ፌዴሬሽኑ በዘንድሮ ውድድር አምስት እና ስድስት አትሌቶችን ለማሳተፍ ፍላጎት ቢኖረውም በዝግጅት ማነስ ምክንያት ልምድ ያላቸውንና ለውድድሩ መድረስ የሚችሉትን አትሌቶች ብቻ ለማሳተፍ ተገዷል:: ከስፖርቱ ባህሪ አኳያ ወጣትና ልምድ ያሌላቸውን አትሌቶች በሁለት ወር ዝግጅት ለአለም ቻምፒና ማድረስ ከባድ በመሆኑም ቁጥሩ ሊያንስ ችሏል::
ለዓለም ቻምፒዮና ይሄን ያህል ተወዳዳሪ ይሳተፍ እንጂ በቀጣይ ለአፍሪካ ጨዋታዎችና ለኦሊምፒክ የሚሆን ብሔራዊ ቡድን ከዚህ ውድድር መጠናቀቅ በኋላ ተመርጦ ዝግጅት ያደርጋል:: ለዚህም ለብሔራዊ ቡድን 32 የቴኳንዶ አትሌቶች ተመርጠው ጥሪ እንደተደረገላቸውም ተጠቁሟል:: አትሌቶቹ የሚሳተፉት ለአፍሪካ ጌም፣ ኦል አፍሪካ ጌም ፣ ለኦሊምፒክ ማጣሪያና ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች ይሆናል:: ለዚህም እንደ አሁኑ አይነት የተሳታፊ ቁጥር ማነስ እንዳይከሰት ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ ውጤት ለማምጣት ይሰራልም ተብሏል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም