ይህ የአንጋፋው ክለብ የእግር ኳስ ስፖርት ታሪክ ነው፡፡ አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ጊዜ ያስቆጠረው ይህ ክለብ የስኬት ታሪኩ ግን በጉብል እድሜ የሚቆጠር ነው፡ ፡ በማንቸስተር ከተማ እና በተወዳጁ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የነገሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ደጋፊ ካላቸው 10 ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ማንቸስተር ሲቲ፤ ዛሬ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመትም በድል ደምድሟል፡፡
እአአ በ1880 በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን የተመሰረተው ይህ ክለብ መጠሪያው ጎርተን ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ አርድዊክ የሚል ስያሜ ያገኘ ሲሆን፤ እአአ ከ1887 አንስቶ አሁን የሚታወቅበትን ማንቸስተር ሲቲ የሚል መታወቂያ አገኘ፡፡ ይህ ክለብ አሁን የደረሰበት የስኬት ደረጃ ለመድረስ በርካታ መሰናክሎችን ማለፍ የግድ ብሎታል፡፡ ከእግር ኳስ የብቃት ደረጃ እስከ ፋይናንስ በእጅጉ የተፈተኑባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ እስከ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ምስረታ ድረስም በጥቂት ስኬቶችና በጥረት የታጀበ ታሪክ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም የክለቡን የውጤታማነት ታሪክ በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቀላል፡፡
ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ማንቸስተር ሲቲ በ114 ዓመት ታሪኩ እምብዛም የሚነገር ታሪክ የለውም፡፡ እአአ ከ1894-2008 ባሉት ዓመታት ያሳካው 2 የፕሪምየር ሊግ፣ 2 የሊግ ካፕ፣ 4 የኤፍኤ ካፕ፣ 3 የኮሚኒቲ ሺልድ እንዲሁም 1 የዩሮፓ ሊግ በጥቅሉ 12 ዋንጫዎችን ብቻ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታትም አስገራሚ የእግር ኳስ ከፍታ እና ዝቅታዎችንም አስተናግዷል፡፡
ወርቃማው የውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ ታሪክ የሚጀምረው እአአ 2008 አንስቶ ሲሆን፤ የአቡዳቢው ባለሀብት መንሱር ቢን ዛይድ ክለቡን መግዛታቸውን ተከትሎ የክለቡ አይነጥላ ሊገፈፍ ችሏል፡፡ በእርግጥ ክለቡ ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት መሸጋገሩን ተከትሎ የራሱን ብቻም ሳይሆን ብቻም ሳይሆን የሊጉንም መልክ መቀየር ችሏል፡፡ ይህ ባለሀብት በክለቡ ባደረጉት የገንዘብ ፈሰስ ምክንያት ስመጥር ተጫዋቾችን ወደ ማንቸስተር ሲቲ ከመቀላቀል በሊጉ የተጫዋቾች የዝው ውር ክብረወሰንን እስከ መስበርም ደርሷል፡፡ በመጀ መሪያዎቹ 5 ዓመታት ብቻ እስከ 500 ሚሊዮን ማው ጣት ከሀብታም ክለቦች ተርታ መሰለፍ ችሏል፡፡
በአሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ እየተመሩም በሊጉ አምስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ህልማቸውን ቢያጨናግፈውም የዩሮፓ ሊግ ተሳትፎን ግን ማሳካት ችለው ነበር፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዓመትም በሊጉ ሶስተኛ ደረጃን በመቆናጠጥ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸውን ከዓመታት በኋላ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ቀጣዩ የሲቲዎች አለቃ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ደግሞ ክለቡን ከተረከቡ በኋላ ሁለት የሊግ ካፖችን ማሳካት ችለዋል፡፡ በሊጉ ሁለት የውድድር ዓመታትንም ያሳለፉት የዋንጫ ተቀናቃኝ በመሆን ነበር፡፡
ክለቡን እስካሁንም ድረስ በከፍታ ማማ ላይ ያስቀመጡት የቀድሞ የባርሴሎና አሰልጣኝ እአአ በ2016 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ተቀላቀሉ፡፡ እኚህ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰውም ክለቡ ከዚያ ቀደም ካሳለፋቸው ረጅም ዓመታት ይልቅ ጥቂቱን በድል ያንቆጠቆጡት ፔፕ ጋርዲዮላ ናቸው፡፡ አሰልጣኙ ከጅምሩ የሊግ ካፕን እንዲሁም ፕሪምየር ሊጉን በማንሳት ምርጥ አሰልጣኝነቱን አስመሰከረ፡፡ ክለቡ ከታላላቆቹ ተርታ መሰለፉን ተከትሎም ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ጭምር የክለቡን መለያ ለመልበስ የሚመኙት ምርጡ የእንግሊዝ ክለብ ሆነ፡፡ ከከተማ ተቀናቃኙ ሃያል ክለብ ማንቸስተር ሲቲ የጻፋቸውን የስኬት ታኮች ተረክቦም በራሱ ገጽ ለማስፈር በቃ፡፡
እአአ ከ2008-2023 ባሉት ዓመታትም 7 የፕሪምየር ሊግ፣ 6 የሊግ ካፕ፣ 2 የኤፍኤ ካፕ እና 3 የኮሚዩኒቲ ሺልድ በድምሩ 18 ዋንጫዎችን ከካዝናው ደርድሯል፡ ፡ በአዲስ የእግር ኳስ ማንነት ከፍ ብሎ በመብረር ላይ የሚገኘው የማንቸስተር ከተማው ድምቀት ዛሬ በሚጠናቀቀው የሊግ ዓመትም ስኬቱን እአአ ከ2019 በቀር በተከታታይ ለአምስተኛ ዓመት ዋንጫውን የራሱ ማድረግ ችሏል፡፡ የዋንጫው ተቀናቃኝ የነበረው ክለብ አርሰናል በኖቲንግሃም ፎረስት መረታቱን ተከትሎም ውሃ ሰማያዊዎቹ አንድ ጨዋታ እየቀራቸው ቼልሲን ባሸነፉበት ጨዋታ ኢትሃድ ላ ዋንጫውን ተረክበዋል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊግ እና ኤፍኤ ካፕም ለፍጻሜ በመድረስ በዓመቱ ተጨማሪ ዋንጫዎችን ለመውሰድም የተሰናዱ ሲሆን፤ ስኬታማ ከሆነም አዲስ ታሪክ የሚጽፍ ይሆናል፡፡
በጥቂት ዓመታት በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቁንጮ መሆን የቻለው ሲቲ ያሳለፋቸው የውጣ ውረድ ዓመታት ከምንም ተነስቶ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ለበርካቶች ትምህርት የሚሆን ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም