የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የአገሪቱን የስፖርት ችግር ለመፍታት በቂ አቅም እንዳለው ተጠቆመ።የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ እንዲሁም ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከትናንት በስቲያ በአካዳሚው የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ታዳጊዎችን ከመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመመልመል አሰልጥነው ለክለቦችና ለብሔራዊ ቡድኖች ከሚያበቁ ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ነው።ተተኪ ስፖርተኞችን በአራት ዓመት ቆይታ ብቁ የሚያደርገው አካዳሚው በዓለም አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ያስጠሩ በርካታ ስፖርተኞችን አፍርቷል።ይህም አካዳሚው የአገሪቱን የስፖርት ችግር ለመፍታት በቂ አቅም እንዳለው ተገልጿል።መንግሥት ለስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት እንደሰጠ ማሳያ የሆነው ይህ አካዳሚ፤ በቀጣይም መሰል ተቋማት እንዲበራከቱ ሊሠራ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ እና ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አይረዲን ተዘራ ጠቁመዋል።በአካዳሚው በክፍተትነት ለተነሱ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባውም አክለዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በአካዳሚው በነበራቸው የአንድ ቀን የመስክ ምልከታ የአካዳሚውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የስልጠና ቁሳቁሶች፣ የሰልጣኞች መመገቢያ፣ መኖሪያ፣ የውስጥ ጂምናዚየም፣ የሕክምና ማዕከል፣ የስፖርት ቤተ-ሙከራ፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የመሰብሰቢ አዳራሾች፣ የመረጃ ማዕከል እና ሌሎችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።በሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችም አካዳሚው ስለሚሰጠው አገልግሎት ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ከመስክ ጉብኝቱ በኋላም የአካዳሚው የዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ መኮንን፤ አዲሱን የመንግሥት ምስረታ ተከትሎ የፌዴራል ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት የወጣውን አዋጅ 1263/2014 መሠረት በማድረግ አካዳሚው ከአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ጋር ያደረገውን ውህደት እና የመዋቅር አደረጃጀትን የተመለከተ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለጻ አድርገዋል።
ጉብኝቱን እና ገለጻውን ተከትሎ በተደረገው ውይይትም በርካታ ሃሳቦች ተነስተዋል።ከምልመላ፣ ከስልጠና፣ ከጥናትና ምርምር ሥራዎች፣ ከስፖርት ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ ከሰልጣኞችና አሰልጣኞች ጥምረትና ውህደት፣ ከመዋቅር፣ ከውስጥ ገቢ አሰባሰብ፣ ከስፖርት ትጥቅ ግዢ፣ ከውክልና አሰጣጥ፣ ከሰልጣኞች ዕለታዊ የምግብ ፍጆታ፣ ከጥገና እና መሰል የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ በጥንካሬ እና በክፍተት በታዩ ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል።በአካዳሚው በኩል ለተነሱ ጥያቄዎችም የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው እና የሚመለከታቸው አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ፤ የቋሚ ኮሚቴው ጉብኝት በአካዳሚው ላይ ይነሱ የነበሩ ብዥታዎችን ግልጽ ያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።አካዳሚው የኢትዮጵያን ስፖርት ሕዝቡ በሚፈልገው ልክ የበኩሉን ድርሻ ከመወጣትም ባሻገር የአገሪቱን የስፖርት ችግሮች ፈትሾ ለይቶ ጥናት በማድረግ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት እንዲሆኑ ማድረግ እንዳለበት አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ከክለቦችና ከብሔራዊ የስፖርት ማህበራት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፣ የውጭ አገር ተሞክሮን በልምድ ልውውጥ ማዳበር እንደሚገባው፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ከአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ጋር ወጥና ተከታታይነት ያለው የግንኙነት መድረክ በመፍጠር ተቋማዊ ጥንካሬ መፍጠር እንደሚገባው አብራርተዋል።በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ አካዳሚው ከመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ከዚህ በላይ ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ታዳጊዎች ሳይንሳዊ ስልጠና በመስጠት ለአገርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁና ውጤታማ ለማድረግ የሚተጋው ይህ አካዳሚ፤ የስፖርት ባለሙያዎችን አቅም መገንባት እንዲሁም የስፖርት ጥናትና ምርምር የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቶታል።በሚያሰለጥንባቸው የስፖርት ዓይነቶች ለብሔራዊ ቡድን ግብዓት የሆኑ ምርጥ ስፖርተኞችን ከማበርከት ባለፈ፤ በዓለም አቀፍ የታዳጊና ወጣት ውድድሮች ላይ በሰልጣኞቹ በርካታ ሜዳሊያዎችንና ዋንጫዎችን ማስገኘት ችሏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015