በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ኩባንያዎች የተሳተፉበት ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ‹‹ኢትዮጵያን እንገንባ›› ኤግዚቢሽን በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ከግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ኤግዚቢሽን ከ24 አገራት የተውጣጡ ከ130 በላይ የኤግዚቢሽን አቅራቢ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እውቅና የተሰጠውና ድጋፍ የተደረገለት ይህ ኤግዚቢሽን፤ በዓለም አቀፉ ጂ ኤም ጂ ኢቨንትስና በአገር በቀሉ ኢቲኤል ኢቨንትስ ኤንድ ፕሮሞሽን የተዘጋጀ ነው። ኤግዚቢሽኑ ከ6 ሺህ በላይ በሕንፃ ንድፍ እና ግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን፣ የሕንፃ ጥገናና አስተዳደር ባለሙያዎችንና ተፅዕኖ ፈጣሪ የዘርፉ አካላትን እና ልሂቃንን በአንድ መድረክ ለማገናኘት ያስቻለ በዓይነቱ ለየት ያለ መድረክ ነበር።
ኤግዚቢሽኑ በሚኒስትሮች ፎረም ነው የተከፈተው። በዚህም ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለውን ምቹ ዕድል አስመልክተው ለኤግዚቢሽን አቅራቢዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ፕላን ኮሚሽን፣ ገንዘብ ሚኒስቴር የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ከነበሩት መካከል ናቸው፤ የተቋማቱ ኃላፊዎችም ሀሳባቸውንም አጋርተውበታል።
የኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ምን ደረጃ ላይ መድረስ አለበት? ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል? የመንግሥት ቀጣይ አቅጣጫስ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ካደጉት አገራት ምን ትምህርት ልትቀስም ትችላለች? የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችም ተነስተውበታል።
በሚኒስትሮች ፎረሙ ላይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰፊ ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል። በመድረኩ የተሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ብዙ አማራጮች እንዳሉም አመልክተዋል። የኮንስትራክሽን ዘርፉ ላለፉት በርካታ ዓመታት የ11 በመቶ እድገት እያስመዘገበ መምጣቱም ጠቅሰው፣ ይህ የእድገት ምጣኔ ከሚጠበቅበት አንጻር አነስተኛ ቢሆንም መልካም አፈጻጸም ነው ሲሉም ነው ያመለከቱት።
ዘርፉ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ከግንባር ቀደም ዘርፎች መካከል የሚመደብ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል። ለውጭ ድርጅቶች አማራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በሚኒስትሮች ጉባኤው የተገኙት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው በአገሪቱ ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድኖች በብዛት መኖራቸውን ጠቁመው፤ ኩባንያዎቹ በዚህ ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ በመዋል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልከተዋል።
የፕላን ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የአገሪቱ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፣ በእቅዱ ላይም በዘርፉ ለሚሰማሩም የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል። ኩባንያዎቹ በዘርፉ ቢሰማሩ ራሳቸውን እና ኢትዮጵያን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በኮንስትራክሽን ዘርፉ የአገር በቀል ኩባንያዎች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል። አገር በቀል ኩባንያዎች ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና ለአገሪቱ በአጠቃላይ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ተጠቃሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ኩባንያዎቹም ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። የአገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ መዋዕለ ንዋይ ቢያፈሱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ሚኒስትሯ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ በጦርነት ውስጥ እንደነበረች አስታውሰው፣ አሁን አገሪቱ ያን አስቸጋሪ ሁኔታ አልፋ ወደ ልማት እና ወደ አገር ግንባታ መመለሷን አስታውቀዋል። ኤግዚቢሽኑ ‹‹ኮንትራክት ኢትዮጵያ›› ‹‹ኢትዮጵያን እንገንባ›› በሚል መሪ ሀሳብ መካሄዱም ኢትዮጵያውያን የደህነት እና የእርስ በርስ ጦርነት ታሪክን ተሻግረው ወደ አገር ግንባታ መመለሳቸውን ለማሳየት በሚል የተሰጠ ስያሜ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ልማት ማፋጠንና ቀጣይነት ያለውን መሻሻል ማረጋገጥ ነው፤ ከዘርፉ የሚነሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ልማት እድገት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከኢንዱስትሪው ባህሪ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚውሉ ኤግዚቢሽኖች፣ የልምድ ልውውጦች የሚካሄዱባቸውን መድረኮች ማዘጋጀት አስፈላጊ ይሆናል። በቀጣይም እንደ ቢግ 5 ዓይነት መድረኮችንና የትውውቅ እና የኔትወርኪንግ መድረኮችን ለማመቻቸት ይሠራል።
ኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ምቹ የሆኑ እና በሰፊው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዳሏት ጠቅሰው፣ እነዚህ ሀብቶች ግን ጥቅም ላይ ሳይውሉ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት። የአገር ውስጥና የውጭ የዘርፉ ባለሙያዎች አገሪቱ ያላትን የኮንስትራክሽን ግብአቶች እምቅ አቅም አውቀው በዘርፉ መዋእለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ዘርፉን እየፈተነ ያለውን የኮንስትራክሽን ግብአት እጥረት እንዲቀርፉም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ ከውጭ አገራት የመጡ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ ዕድል መኖሩን መገንዘባቸውን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የውጭ ኩባንያዎቹ ተወካዮች በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም እያደገ ያለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ እና የሕዝብ ብዛት ኢትዮጵያ ላይ ዓይናቸውን እንዲያሳርፉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል።
የሳዑዲ አረቢያው ናጂራን ሴሜንት ኩባንያ በኤግዚቢሽኑ ላይ ከተሳተፉት አንዱ ነው። በሲሚንቶ ምርትና ኤክስፖርት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ ያለው ናጂራን፣ በዓመት ስድስት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማቅረብ አቅም አለው። ከሳዑዲ አረቢያ አልፎ ቀጣናው የሲሚንቶ ፍላጎ ግብይት ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ያለ ኩባንያም ነው።
የናጂራን ሲሚንቶ ፋብሪካ ተወካይ ናጂ መሃመድ የሲሚንቶ ፋብሪካው እ.አ.አ በ2005 ማምረት የጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀጣናውን የሲሚንቶ ፍላጎት ለማሟላት የተቋቋመ ፋብሪካ መሆኑን ይገልጻሉ። በኤግዚቢሽኑ ላይ የተገኙት ምርታቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስተዋወቅ መሆኑን አስታውቀዋል። ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሲሚንቶ ምርታቸውን አስተዋውቀው መመለሳቸውን ያስታወሱት ናጂ፤ አሁን ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ መጥተው በኤግዚቢሽኑ በመሳተፍ ምርታቸውን እያስተዋወቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለሲሚንቶ ምርት ምቹ ገበያ እንዳላት መገንዘባቸውን የጠቆሙት ናጂ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሲሚንቶ ገበያ ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ እጅግ ሰፊ ገበያ ያለ ከመሆኑም ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ሥራ ምክንያት የሲሚንቶ እጥረት መኖሩ ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ እንዲጥሉ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አሁን ካለው በላይ የሚመነደግበት ወቅት መድረሱን ሚኒስትሮች ለኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎች ካደረጉት ንግግር መረዳታቸውን ጠቁመዋል። በተለይም በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ሲሚንቶ የሚፈልጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሲሚንቶ እጥረት ችግር ለመፍታትና ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል።
ናጂ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አቀማመጥ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ እንዲያነጣጥሩ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ገበያ ለመግባት እንደበር ታገለግላለች። በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ምርታቸውን ማቅረብ አፍሪካ ገበያ ውስጥ በስፋት ለመሳተፍ እንደሚያስችላቸው ተስፋ አድርገዋል። በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባት እንደሚጀምሩ ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመው፣ ምርት ለመላክ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በኤግዚቢሽኑ የተሳተፈው ሌላኛው የውጭ ኩባንያ የጣሊያኑ ቫልፔይንት ነው። ኩባንያው በሕንፃ ማጠናቀቂያ ሥራ ላይ የተሰማረ ሲሆን፣ የሕንፃዎች ውጫዊና ውስጣዊ ክፍሎች ማሳመሪያ ግብአቶችን ያመርታል።
የቫልፔይንት የውጭ ሽያጭ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ጊኖ ሰፓዶኒ እንደሚሉት፤ ድርጅቱ እ.አ.አ በ1985 ነው የተቋቋመው፤ በ65 አገራት ውስጥ ቢዝነስ ይሠራል። በቱኒዝ እና ስፔን የማምረቻ ፋብሪካዎች አሉት። በተለይም በሰሜን አፍሪካ ውስጥ ድርጅቱ እጅግ ታዋቂ መሆኑን ጠቅሰው፣ አብዛኛው ምርትም ወደ ሰሜን አፍሪካ እንደሚላክ ነው የተናገሩት። ኩባንያው ጣሊያን ውስጥ ምርቶቹን ብዙም አይሸጥም። ከ90 በመቶ በላይ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ያለ ድርጅት ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ጊኖ፤ ጥራት ያላቸው ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት እያስተዋወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ምርታቸውን ለማስተዋወቅ በኤግዚቢሽኑ መገኘታቸውን በመጠቆም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዕድል ከግምት በማስገባት ጊዜ ምርቶቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ፋብሪካ ለመትከል ድርጅታቸው ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
መቀመጫውን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፤ ዱባይ ያደረገው ካኖ ማሽነሪስም በኤግዚቢሽኑ ምርቱን ሲያተዋውቅ አግኝተነዋል። ካኖ ማሽነሪ፤ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን፣ ሞተሮች እና የኃይል ማሽነሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ለሽያጭና ኪራይ የሚያቀርብ ድርጅት ነው።
የካኖ ማሽነሪስ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስተር ከነኣን ቻንድራሴካራን፤ ድርጅታቸው በሰባት አገራት እንደሚሠራ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመቃኘት በኤግዚቢሽኑ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ትልቅ አገር ከመሆኗ ባሻገር እያደገ ያለ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለባት አገር መሆኗን መገንዘብ መቻላቸውን የጠቆሙት ከነአን፣ ለኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ሽያጭ ያለውን ዕድል ለማየት ወደ አገሪቷ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት። ኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ ዕድል ያለበት አገር መሆኗን መገንዘባቸውን ጠቅሰው፣ አዳዲስ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ከማስገባት ባሻገር በአገር ውስጥ ያሉ ማሽነሪዎችን በመጠገን ሥራም ለመሰማራት ምቹ ዕድል መኖሩን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የጥገና፣ የኪራይ እና የተለዋዋጭ አካላት ፍላጎት ጥናትም ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። አገልግሎት የሰጡ በርካታ ማሽነሪዎች እንዳሉ የጠቆሙት ከነአን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ዕድል ማየታቸውን ጠቁመዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው እንደሆነ የሚናገሩት ከነአን ፤ ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ በምን ዓይነት መልኩ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ እያዩ መሆናቸውን አንስተዋል። በዘርፉ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ለመነጋገር ዕድል እንዳገኙም ገልጸዋል። ከመንግሥት ባለሥልጣናት የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚሰጡ መስማታቸውን ጠቁመው፤ ማበረታቻዎቹ መልካም የሚባሉ መሆናቸውም ነው የተናገሩት።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015