ዶክተር አረጋዊ በርሔ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም መሾማቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ትልቅ ደስታ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ፡፡ በዚህ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሥራት በመቻላቸውም ለእርሳቸው ትልቅ ክብር እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያታቸው ደግሞ ለሕዝባቸው እና ለሀገራቸው የሚያደርጉት አስተዋፅዖ በተግባር እንዳሳዩ እድል የሚሰጣቸው በመሆኑ ነው። ይህ በመሆኑም የሚሠሩት ከልባቸው ነው፡፡
ከሰሞኑን ግብፅ የዓባይ ጉዳይ በዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን ከመጎትጎት አልፋ ውሳኔዎች እንዲካሄዱም እየገፋች ነው፡፡ በተለይ በዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀምና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እየወሰደች ካለችው የተናጠል እርምጃ እንድትቆጠብ ውሳኔ እንዲተላለፍ ማድረጓ ተሰምቷል፡፡ ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የወንዙ መነሻ ሆና ሳለች የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው እንደሚባለው ሁሉ፤ በወንዙ ተጠቅማ ኃይል በማመንጨት ሕዝቧን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ማድረግ ሳትችል ቆይታለች። ከአጠቃላይ ሕዝቧ 55 በመቶ ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል ብርሃን በማግኘት ላይ ሲሆኑ፤ አሁን ግን የታችኛው ተፋሰስ አገራት ሳይጎዱ ሕዝቧን ከወንዙ በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ ሕዝቧን ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ሱዳን እና ግብፅንም ሳይቀር ሁሉን ተጠቃሚ በሚያደርግ መርሕ ላይ በመመርኮዝ ግድቡን መገንባት ጀምራለች፡፡
ይሁን እንጂ ግብፅ በተቃራኒው የሕዳሴው ግድብ ጉዳይን በማንሳት ተፅዕኖ ማሳደር ይችላሉ የምትላቸውን አገራትና ተቋማት በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲፈፀም ግፊት እና ጥሪ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ የአፍሪካ ኅብረት፣ የዓረብ ሊግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ኃያላኑን ምዕራባውያኑን በተደጋጋሚ ከግድቡ ጋር በተያያዘ እንዲደግፏት እየጠየቀች ትገኛለች፡፡
ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የህዳሴው ግድብ ሙሌት መጠኑንና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን በተመለከተ የሦስቱ አገራት ባለሙያዎች ስምምነትን ተከትላ በመፈፀም፤ ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳን የተፈራረሙትን የመርሆዎች ስምምነትን ሳትተላለፍ የመጠቀም መብቷን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው። ግብፅ ግን ከተፈራረመችው ስምምነት በመተላለፍ አሁንም የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት በበላይነት ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንን በተመለከተ የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄን በማነጋገር እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡
አዲስ ዘመን፡- የዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ እና በህዳሴው ግድብ ላይ እየወሰደች ካለው የተናጠል እርምጃ እራሷን እንድታቅብ ሲል ማመልከቱ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃኖች ተስተጋብቷል። በዚህ ጉዳይ እርስዎ በተመለከተ ምን ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ፡- በመሠረቱ በዋናነት ዓባይን የመጠቀም ጉዳይ ዓባይ በሚደርስባቸው የተፋሰሱ አገሮች ብቻ መታየት ያለበት ነው። በዋናነት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ እንጂ ከዛ ውጪ የዓረብ አገራትም ሆኑ፣ አውሮፓውያን እንዲሁም ኤዥያ ማናቸውም አገራት አይመለከታቸውም።
በተጨማሪ የዓረብ ሊግም ጉዳዩን ሲያይ በሐቅ እና በፍትሐዊነት ላይ ተመሥርቶ አልነበረም። እንዳየነው ከሆነ ከግብፅ ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በሚያንፀባርቅ መልኩ አድሏዊ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በማንኛውም ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ ተቀባይነት የሌለው ነው።
የዓረብ አገራቱ ይህንን ከማድረግ ይልቅ አርፈው ቢቀመጡ ይሻላል። ወይም ችግር እንፍታ ብለው ከተንቀሳቀሱም በዋናነት የሚመለከታቸው ሦስቱ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በራሳቸው ተመካክረው እና ተግባብተው እንዲሠሩ አስተዋፅዖ ቢያደርጉ የሚሻል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ ሂደቱ በግልፅ እንዲጎበኝ ከማድረግ አልፋ፤ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከሱዳን እና ከግብፅ የተወጣጣ የባለሙያ ቡድን ሚናውን እንዲወጣ መፍቀድ ብቻ አይደለም ስትገፋፋም ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ግብፅ በተለያየ መልኩ ተፅዕኖ ለማሳደር ሞክራለች። አሁን ደግሞ የዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤትን እየተጠቀመች ነው። ይህ ተግባር ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የዓለም ሕግ አንፃር እንዴት ይታያል?
ዶክተር አረጋዊ፡- በየትኛውም የሕግ መለኪያ የዓረብ አገሮችም ሆኑ ምክር ቤቱ በምንም መልኩ ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች በሚመለከታቸው የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጣልቃ መግባታቸው አግባብነት የሌለው ነው። ይህ የሚያሳየው ወገንተኝነትን ነው። የዓረብ ሊግ ስሙ እንደሚያመለክተው ብዙ የዓረብ አገራትን ያካተተ ማኅበር ነው።
እንደአቅማቸው ገንቢ የሆነ ሥራን መሥራት እንጂ በኢትዮጵያ እና በግብፅ ወይም በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ማድረግ አይገባም። አሁን አገራቱ ተስማምተው አካባቢያቸውን እንዳያለሙ እና የጋራ ዕድገት እንዳያስመዘግቡ እንቅፋት እየሆኑ ነው። ስለዚህ ከዚህ ተግባር መታቀብ አለባቸው። የዓለም አቀፉ የውሃ ሕግ እና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ቢመለከቱ ይመረጣል።
አዲስ ዘመን፡- ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ወደ ዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት መውሰዷ ትርጉሙ ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ፡- ይሄ ግልፅ ነው። ግብፅ ከድሮ ጀምሮ የዓባይን ውሃ ለመቆጣጠር እና የበላይነቷን ለማረጋገጥ በየትኛውም መልኩ ጥረት ታደርጋለች። የዓባይን ውሃ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እስከ መክፈት የደረሰችበት ጊዜም ነበር። ድሮም ቢሆን ከከፈተችው ጦርነት በተጨማሪ፤ በ18 ኛው እና በ19ኛው ክፍለ በተለያዩ ጊዜያት ጦርነቶችን ከፍታለች። ይህ ዋናው እቅዷ ዓባይን በኃይል ለመቆጣጠር ነው። ተስማምቶ እና ተግባብቶ መሥራት፤ ፍትሐዊ የሆነ የውሃ ክፍፍልን መሠረት አድርጋ እንደመሥራት፤ በጉልበት ለመቆጣጠር አቅዳ በቀይ ባሕር በኩልም ሆነ በሌላ በኩል ጦርነት ስትከፈት ኖራለች።
ከዛ በተጨማሪ የቅኝ ግዛት አባዜ ስለተጠናወታት ከእንግሊዞች ጋር በመሻረክ በ1929 እና በ1959 ዓ.ም ኢትዮጵያን ያላካተተ ውሎችን በማፅደቅ የራሷን ብቻ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትሠራ ቆይታለች። ይህ ጥረቷ በምንም መለኪያ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ስላልሆነ ተቀባይነት የለውም። አሁን ኢትዮጵያ መብቷን ለማስከበር በምትንቀሳቀስበት ጊዜ የድሮ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ አካሄድ የተሞላበት እና አንድ ወጥ የበላይነትን ለማምጣት የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈርስባት መሆኑን ስላወቀች የተለያዩ መንገዶችን እየፈለገች ወደ ድሮ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ነው።
ግብፅ እውነት ቢኖራት ኖሮ በፍትሐዊነት መንገድ ሦስቱ አገሮች ቁጭ ብለው ተወያይተው ችግሩን መፍታት ይችላሉ። ከዛ ባሻገር የአፍሪካ ኅብረትንም መጠቀም ይቻላል። የአፍሪካ ችግርን በአፍሪካውያን የሚለውን መርሕ ተከትላ አስፈላጊም ከሆነ ሁለተኛ ወገን ጨምራ በመወያየት የጋራ ጥቅምን ማስከበር ይቻላል። ይህንን ሁሉ ሳታደርግ ፈጥና ወደ ዓረብ ሊግ የሔደችው ዓረቦች ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት ለግብፅ እንደሚያደላ ስላወቀች ሆነ ብላ ነው። ይህንን ግምት ውስጥ አስገብታ ጉዳዩን ወደ ዓረብ ሊግ ወስዳዋለች። የዓረብ ሊግም እጄን ልሰንዝር ያለው ግብፅን ለመርዳት ነው። ስለዚህ ይህ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ኢ-ፍትሐዊ አካሔድ ስለሆነ ዞሮ ዞሮ ተቀባይነት የማይኖረው ውድቅ የሆነ ጉዳይ ነው።
ባለፈው እኤአ መጋቢት ወር 2015 አገራቱ በፈረሙት ‹‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንስፕልስ›› ስምምነት መሠረት ሦስቱ አገሮች በጋራ ተስማምተዋል። በወቅቱም ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ተግባራዊ ብናደርገው ሁላችንንም የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገናል ብለው ነበር። ግብጽ ያ አካሄዷ ጥሩ ነበር። አሁን በያዘችው አካሔድ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም። ተግባሯ አፍራሽ ነው። ኢትዮጵያ ምንም ሆነ ምን የዓባይን ውሃ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መጠቀም መጀመሯን ትቀጥላለች። አሁንም በዛው መልኩ ትቀጥላለች፤ የሚያደናቅፋት ነገር አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ዓባይን በመጠቀም ዙሪያ ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገ አካሔድን ለመምረጥ ዝግጁ ብትሆንም፤ እርስዎም እንደገለጹት ግብፅ ግን አሁንም ድረስ አካሄዷ ከኢትዮጵያ ተቃራኒ ነው። እርሷ ብቻ ተጠቃሚ እንድትሆን እና በተቆጣጣሪነትና በበላይነት እንድትቀመጥ ፍላጎቱ እንዳላት እያሳየች ነው። አንዳንዴ ግፊቷን በጣም የምትጨምርበት ሁኔታም ይስተዋላል። አሁን ላይ አዝማሚያዋን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አረጋዊ፡- አሁንም አካሄዷ ተመሳሳይ ሲሆን፣ በተፅዕኖ እና በኃይል ፍላጎቷን ለማሟላት የምታደርገው ጥረት የቀጠለ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይሄ ከግድቡ አንፃር እንየው ከተባለ የህዳሴው ግድብ ገና የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ እየተቃወመች ነበር። የውሃ ሙሌት እንዳይካሔድም ብዙ ጥረት ታደርግ ነበር። የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ላይ ብቻ ሳይሆን ሁለተኛው እና ሦስተኛው የውሃ መሙላት ተግባር ሲከናወን ትቃወም ነበር። አሁንም ወደ ፊት አራተኛው የውሃ ሙሌት እንዳይከናወን በማሰብ የምትፈፅመው ነው።
በቅድሚያ የአውሮፓ አገሮችን አሜሪካንን ጨምሮ በማስተባበር እና የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ተፅዕኖ ለመፍጠር ጥረት አድርጋለች። በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአስተዳደር ዘመንም በግድቡ ላይ ያልተገባ ዛቻ እስከመሰንዘርም ተደርሶ እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በመተባበር ማስፈራሪያ ሳይበግራቸው የግድቡ ግንባታ ቀጥሏል። ስለዚህ ግብፅ የግድቡ ግንባታ እውን እንዳይሆን የማስፈራሪያ ሙከራዎችን አድርጋለች፤ አሁንም በማስደረግ ላይ ናት። ይህንኑ ትቀጥል ይሆናል።
ኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት ወደ ኋላ የምትልበት ሁኔታ የለም። ኢትዮጵያ በማስፈራሪያዎቹ አልተበገረችም፤ ወደ ፊትም አትበገርም። ሕዝቡ ተባብሮ በቁርጠኝነት ለመጨረስ እየተባበረ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ግብፅ በተለያየ መልኩ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት ታደርጋለች። አሁን ደግሞ ለአፍሪካ ኅብረት አፍሪካዊ መፍትሔ በማለት የአፍሪካ ኅብረት እና የአፍሪካ አገራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ዓረብ ሊግ ምክር ቤት መውሰዷ አፍሪካዊ ማንነትን መካድ አይሆንም?
ዶክተር አረጋዊ፡- ችግሩ በአፍሪካ ኅብረት ላይ እምነት አለማሳደሯ ነው። በኅብረቱ እየታየ ውሳኔ ሲሰጥ የፍትሐዊነት ጥያቄ ይነሳል በሚል፤ ወይም የአፍሪካ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ያደላሉ ብላ በማሰቧ ነው። በሌላ በኩል የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ማለት የጥቁር አዓባይ እና የነጭ ዓባይ ተፋሰስ አገሮች በጋራ ሆነው ችግሩን እንዲፈቱ ወይም ቀጣናዊ ችግርን ተወያይቶ የሚፈታበትን ሁኔታ አይታለች። ግብፅ ደግሞ ይህንን አትፈልግም። በእኩልነት እና በፍትሐዊነት ላይ የተመሠረተ የውሃ ክፍፍልን አትፈልግም።
እርሷ የምትፈልገው ትልቁን ድርሻ ነው። ከዚህ በፊት ምንም ጠብታ ውሃ አስተዋፅዖ ሳታደርግ ነገር ግን 86 በመቶ የዓባይን ውሃ መጠቀም አለብኝ ብላ ስትጠቀም ነበር። ይህ ደግሞ የትኛውም አካል ሊረዳው የሚችል ፍፁም ፍትሐዊ ያልሆነ ጉዳይ ነው።
ይህ የዓባይ ውሃ ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ ግብፅ ልጠቀም ማለቷን አፍሪካውያንም ይገነዘባሉ። የአፍሪካ አገራትም ጥረት የሚያደርጉት አብሮ ለመልማት እና ፍትሐዊ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። ግብፅ ግን አሁንም ድረስ ፍትሐዊ ክፍፍልን አትቀበልም። ይህንን ፍትሐዊነት የጎደለው ድርጊት ዓረቦቹ ዝም ብለው በስሜት ግብፅ ከፊል ዓረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ስለሆነች እርሷም ለእነርሱ ያላትን ቀረቤታ በመጠቀም ለእርሷ ያደላ ውሳኔ ይተላለፋል የሚል ሕልም ያላት በመሆኑ ወደ እነርሱ አምርታለች። ይሄ ግን ከሕልም በታች ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ቅዠት ነው። ስለዚህ በዚህ ምክንያት ከአፍሪካ እየሸሸች ወደ ዓረቦች እየሮጠች ነው።
አዲስ ዘመን፡- የግብፅ ወደ ዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት መሮጥ ኢትዮጵያ እና የዓረብ አገራት ሕዝቦች የሚጋሯቸውን ታሪኮች እና ወዳጅነታቸው ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ በተመለከተ ምን ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ፡- ከመነሻው ግብፅ ፍትሐዊ የሆነ የውሃ ክፍፍልን አትፈልግም። ስለዚህ ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ ክፍፍል ሊደግፍ እና ተግባራዊ እንዲሆን ሃሳብ ሊሰነዝርላት የሚችለው የዓረብ ሊግ ወይም ዓረብ አገራት ናቸው ብላ ታምናለች። ስለዚህ የሆነ እና ያልሆነ ታሪክ በመደርደር ‹‹ግብፅን ድርቅ ሊመታት ነው፤ ግብፃውያን በውሃ ጥም ሊጠፉ ነው። ውሃውን ኢትዮጵያ እዛው ልታስቀረው ነው›› የሚሉ የተዛቡ እውነትነት የጎደላቸውን ሃሳቦች በማቅረብ ዓረቦችን እና ግብፆችንም ጭምር እያታለለች ነው። ይህ ሁሉ የተጠቀሱ ምክንያቶች እውነት አይደሉም። ውሃው አይቆምም፤ ኃይሉን ካመነጨ በኋላ ጉዞውን ይቀጥላል። ውሃውን ማግኘታቸው አይቀርም።
ግብፆችን ወዳልተገባ አካሔድ የሚገፋቸው በአንድ በኩል ፍራቻ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውሃውን ተጠቅማ ማደግ ከጀመረች ወደ ፊት የበላይነትን ትይዛለች ከሚል ስጋት እንጂ ሌላ ተጨባጭ ምክንያት የላቸውም። ሌላ ምክንያት ቢኖራቸው ኖሮ የሦስትዮሽ ውይይት በሚካሔድበት ጊዜ ግብፅ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርገዋል። አሳማኝ ምክንያት ቢኖራቸው ኖሮ በውይይቱ ላይ አቅርበው ተከራክረው ማሳመን ይችሉ ነበር። ስለዚህ የግብፅ አካሔድ ቅዠት የተሞላበት ነው። ቅዠቱም ከጩኸት የማያልፍ፤ የዓረብ ሊግም ቢሆን የትም መድረስ የማይችል ሲሆን፣ ግብፅ የሊግ አገራቱን ምክር ቤት በመጠቀሟ የዓረብ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነታቸው እንዲሻክር ከማድረግ ውጪ ምንም ውጤት አይኖረውም።
አዲስ ዘመን፡- ግብፅ በእርግጥም የዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤትን ያለአግባብ እየተጠቀመች ነው። ነገር ግን ከዚህ ተግባር አንፃር የአፍሪካ ኅብረት፣ አጠቃላይ የአፍሪካ አገራት ምን ማድረግ አለባቸው?
ዶክተር አረጋዊ፡- በዋናነት ለፍትሐዊነት በጋራ መቆም ነው። የዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕጎች ተግባር ላይ እንዲውሉ በጋራ መንቀሳቀስ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ አሸናፊው ፍትሐዊውን መንገድ የሚከተለው ወገን ነው። በዚህ ላይ ምንም ስጋት ሊያድርብን አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- ግብፅ ከመጠቀም አልፋ ተርፋ በበላይነት ወንዙን ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ነበር። አሁንም ያንኑ ጥረቷን ቀጥላለች። የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ መላው ኢትዮጵያውያን ከዓባይም ሆነ ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ ከግብፅ ባልተናነሰ መልኩ ለመሥራት እና በይበልጥ ተቀባይነት ለማግኘት ምን መሥራት ማድረግ አለባቸው?
ዶክተር አረጋዊ፡- ለሦስተኛ ጊዜ ውሃው የተሞላ ሲሆን፣ በሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ተጀምሯል። ወደ ሱዳን ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ከሚመነጨው ላይ ኃይል በመሸጥ ላይ ነው። ምክንያቱም የህዳሴው ግድብ የሚያመጣው ትሩፋት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሙሉ የሚቀይር አካሄድ ነው።
በራሳችን አቅም በራሳችን ችሎታ ያለምንም የውጪ እርዳታ እና ብድር የተሠራ ስለሆነ በዚህም ዘላቂ ዕድገት ሊኖር እንደሚችል አረጋግጠናል። ስለዚህ የሚፈለገው ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ቤትም ሆነ ውጪ ያለው ተባብሮ ከተንቀሳቀሰ በዲፕሎማሲው መንገድም ፍትሐዊ አካሔድ መሆኑ ለዓለም በማስረዳት የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንዲገኝ መሥራት ይገባል።
ተባብረን ከተንቀሳቀስን እንኳን ይህንን አንድ የህዳሴ ግድብ ቀርቶ አስር እና መቶ የህዳሴ ግድብን መገንባት ይቻላል። ዘላቂ ዕድገት ማስመዝገብ ማለት ይህ ነው። በብድር እና በእርዳታ ተሞክሮ አልተሳካም። ዕድገት የሚመጣው በዚሁ መልኩ በራሳችን መንቀሳቀስ ስንችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት ያስተላለፈውን መልዕክት አልቀበልም፤ ብሏል። ነገር ግን ጎን ለጎን ግብፆች ውሸት በመንዛት ከላይ እርስዎም እንደጠቀሱት ውሃው ሊቆም ነው፤ እያሉ ያስወራሉ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ የፍትሐዊነት ጉዳይ እውነትን ይዛ የቆመች ናት። የወንዙ አመንጪ ሆና ግማሽ ያህል ሕዝቧ ተጠቃሚ አይደለም። በአግባቡ ተጠቃሚ ለመሆን በስፋት ዲፕሎማሲውም ላይ መሠራት እንዳለበት እሙን ነው። መንግሥት እና ምሑራን በዚህ ላይ ምን መሥራት አለባቸው ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ፡- ምሑራኑም ሆኑ ዲያስፖራው ሁሉም ተባብሮ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። እንዲያውም አሁን የተለያዩ ጅማሬዎች አሉ። በህዳሴው ግድብ ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያየ መስክ አስተዋፅዖ ለማድረግ ዩኒቨርስቲዎች አሁን ተደራጅተው ሙከራዎችን እያደረጉ ናቸው። ውጪ ያለውም እየተሰባሰበ ኃይል እየፈጠረ የሕዳሴ ግድብ ትስስር በመፍጠር ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ወዳጅ የውጪ አገር ዜጎች ተባብረው ከተንቀሳቀሱ በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ውጤት ይገኛል።
እስከ አሁን ትብብር ቢታይም በተናጠል ነው። በተናጠል ከመርዳት ይልቅ በተለይ በዲፕሎማሲው ላይ ከተባበሩ በኢትዮጵያ በኩል ብዙ አሳማኝ ጭብጦች በመኖራቸው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብዙ ድጋፍ መሰብሰብ ይችላሉ። ይህንን እይታ ውስጥ አስገብቶ መንቀሳቀስ ይጠበቃል። መንግሥትም በዲፕሎማሲው መስክ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። በትኩረት ከተንቀሳቀሰ እና ከአስተባበረ በዓለም መድረኮች ላይ ተገኝቶ ተከራክሮ ማሳመን እና ማሳወቅ ከተቻለ የኢትዮጵያ ዕድል ሰፊ ነው። በዚህ ላይ ገብተን ብንሠራበት ጥሩና አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሠግናለሁ።
ዶክተር አረጋዊ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19 ቀን 2015