ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አራት(ዞን4) ጎልፍ ስፖርት ቻምፒዮናን ታዘጋጃለች።ቻምፒዮናው ከግንቦት 28-ሰኔ 04/ 2015 ዓ.ም በመከላከያ ፋውንዴሽን አዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ እንደሚካሄድም የኢትዮጵያ ጎልፍ አሶሴሽን አስታውቋል።
ቻምፒዮናው በኢትዮጵያ ጎልፍ ስፖርት አሶሴሽን፣ በመከላከያ ፋውንዴሽን እንዲሁም በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት እንደሚካሄድ ታውቋል።የአፍሪካ ጎልፍ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን እና አር ኤንድ ኤ ተባባሪ አዘጋጆች መሆናቸውም ተጠቁማል።
“ጎልፍ በኢትዮጵያ ይስፋፋል፤ ኢኮኖሚያችንንም ይደግፋል” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ ቻምፒዮና በየአመቱ የሚደረግ መደበኛ መረሃ ግብር ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ታዋቂ ጎልፍ ተጫዋቾችን በቀጣናው አገራት ማፍራት ነው።የጎልፍ ስፖርትን በመላው ሀገሪቱ በማስፋፋት ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንዲያግዝም ለማድረግ መዘጋጀቱም ተጠቁማል።ኢትዮጵያ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የጎልፍ እንቅስቃሴን በማድረግ ላይ ትገኛለች።በ2008 ዓ.ም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የምስራቅ አፍሪካ የጎልፍ ቻሌንጅ የተሰኘ ውድድር ማዘጋጀቷን ከአሶሴሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
በዘንድሮው ቻምፒዮና በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አራት ያሉ አገራት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ርዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኮሞሮስ፣ ሲሸልስና አዘጋጇ ኢትዮጵያ የቻምፒዮናው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።እስከ አሁን በቻምፒናው ለመሳተፍ ስድስት ሀገራት ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን፤ የቀሩት ሀገራትም በቀጣይ ይሁንታቸውን እንደሚገልጹ ይጠበቃል።
ጎልፍ በኢትዮጵያ አንጋፋ ከሚባሉ ስፖርቶች አንዱ ሲሆን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥሯል።ስፖርቱ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ (በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ፕሬዚዳንት ደጃዝማች ካሳ ወልደማርያም የበላይ ጠባቂነት ይመራ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።በተፈጠረው የሥርዓት ለውጥ ሳቢያ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳው ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ የራሺያ ሚሊተሪ ካምፕ በመሆኑ የጎልፍ እንቅስቃሴ ተገቶ ቆይቷል። ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ስፖርቱ በድጋሚ አንሰራርቶ ወደ እንቅስቃሴ ገብ ቷል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀጣና 4፣ የአፍሪካ ጎልፍ ኮንፌዴሬሽን እና የዓለም አቀፉ ጎልፍ ፌዴሬሽን ቋሚ አባል እንደሆነች ይታወቃል። በመሆኑም ውድድሩን ማዘጋጀቷ ለጎልፍ ስፖርት የሚሰጠውን ትኩረት በእጅጉ እንደሚያሳድግ አሶሴሽኑ ጠቁሟል። በተጨማሪም የጎልፍ ስፖርት ትልቅ ስምና ዝና ስላለው ዝግጅቱ ለገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ ከማድረጉም ባለፈ ብዙ ጥቅም እንደሚኖረው ተጠቁማል።ስፖርት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ምቹ መድረክ እንደመሆኑ፤ ውድድሩ በዋናነት አፍሪካን ለአፍሪካውያን የሚለውን መርህ በመከተል የሚከናወንም ይሆናል።
ኢትዮጵያ ያላት ባለ 18 ጉድጓድ የመጫወቻ ሜዳ በዓለም አቀፍ በሚወጣለት ደረጃ መሰረት ተመዝኖ ብቁ በመሆኑ የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ማግኘት በመቻሉ ለውድድሩ ዝግጁ ሆኗል።በቴክኖሎጂ በመታገዝም በተጫዋቾች እጅ ላይ በሚገጠም መሳርያ አማካኝነት በመላው ዓለም የሚዳረስ ይሆናል።ይህም ሜዳው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና እውቅና ማግኘቱን ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ሀገር ሆና በውድድሩ እንደመሳተፏ ከቀጣናው ሀገራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የብሄራዊ ቡድን መረጣ እና ዝግጅቷን አጠናቃለች።የኢትዮጵያ ጎልፍ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ሞሲሳ፤ ውድድሩን ማዘጋጀቱ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፈውን ብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ በርከት ካሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ ብሄራዊ ግብረኃይል ተዋቅሮ ስራውን እየመራ መሆኑን ተናግረዋል።
ግብረኃይሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።ግብረሃይሉ አምስት ዋና ዋና ስራዎችን የሚሰሩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ በመስራት ላይም ይገኛል።ከአምስቱ ንዑሳን ኮሚቴዎች ውስጥ ብሄራዊ ቡድንን ማብቃት ላይ የሚሰራው ንዑስ ኮሚቴ በርካታ የማጣርያ ውድድሮችን በማድረግ አራት ምርጥ ብሄራዊ ቡድንን የሚወክሉና አንድ ተጠባባቂ በአጠቃለይ አምስት ተጫዋቾችን መርጧል፡፡
ኢትዮጵያም ደረጃዋን የሚመጥን በቂ ዝግጅት በማድረግ እንግዶቿን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ትገኛለች።ለዝግጅቱ መሳካትም የአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና መከላከያ ፋውንዴሽን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2015