ባለፈው ዓመት ከከፍተኛ ሊግ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አድጎ በ2015 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ እግር ኳስ ክለብ ባደገበት ዓመት መውረዱን ባለፈው ሳምንት ያረጋገጠ የመጀመሪያው ክለብ መሆኑ ይታወቃል።
ከትልቁ የውድድር እርከን ወደ ሁለተኛው የሚወርደው ሌላኛው ክለብም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ደማቅ ታሪክ ካላቸው ክለቦች አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሆኗል። ኤሌክትሪክ ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት ዓመት ተመልሶ መውረዱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ከአንድ ጊዜ በላይ ማንሳት ከቻሉት ሃዋሳ ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተርታ የሚሰለፍ ታሪካዊ ክለብ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ እግር ኳስ ክለብ በቀድሞ ስሙ ኤልፓ ወይም መብራት ኃይል ምሥረታውን በ1953 ዓ.ም አድርጎ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በርካታ ታሪኮችን መሥራት እንደቻለ ይታወሳል። ክለቡ በ2010 ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወርዶ በ2014 ዓ.ም ወደ ፕሪሚየር ሊግ መመለስ ቢችልም በሜዳና ከሜዳ ውጭ በነበሩና በተለይም የውስጥ አስተዳደራዊ ውዝግቦች ምክንያት ውጤት ርቆት ቆይቷል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚዘጋጁ በሁሉም የእግር ኳስ እርከኖች በመወዳደር በርካታ ክብሮችን መቀዳጀት ችሏል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ሦስት ጊዜ በማንሳት ታላቅነቱን አስመስክሯል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተለይም በቀደሙ በርካታ ዓመታት ታዳጊዎችን በማፍራት ጠንካራ ተፎካካሪ ከመሆኑም በላይ ለሀገሪቱ ክለቦችም አስደናቂ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በማፍራት አስተዋፅዖውን አበርክቷል።
ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከ 2010 ሲወዳደር ቢቆይም ከአራት ዓመታት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ በ2014 ዓ.ም ዳግም ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀል ችሏል። ምንም እንኳን በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የመጣ ቢመስልም በውድድር ዓመቱ በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ሊግ ላይ የነበረውን አቋም መድገም አልቻለም። ይህም ሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮች ተዳምረው በድጋሚ ወደ መጣበት ከፍተኛው ሊግ እንዲመለስ አስገድዶታል።
ለክለቡ ውጤት ማጣትና ከሊጉ መውረድ በርካታ ነገሮችን መጥቀስ ቢቻልም ዋናውን ድርሻ የሚወስደው ክለቡ የገጠመው አስተዳደራዊ አለመረጋጋት እንደሆነ ቀደም ሲልም ሲነገር ቆይቷል። ክለቡን በማነቃቃት ከከፍተኛው ሊግ ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካሳደገው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር መለያየቱ ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎበታል። ከአሰልጣኝ ክፍሌ ጋር ለመለያየቱ ምክንያት የክለቡ ደካማ አቋም ማሳየትና ውጤት ማጣት ቢሆንም፤ ከስንብቱ በኋላም የውጤት ማጣቱ ቀጥሎ ከመውረድ አላዳነውም።
አስተዳደራዊ ችግሮችን ቀርፎ ከአሠልጣኝ ለውጥ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ቢወሰዱም ክለቡን መታደግ አልተቻለም። የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ስንብት ተከትሎ የቡድኑን ምክትል አሠልጣኝ ገዛኸኝ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት መሾሙ ይታወሳል። በወቅቱም ክለቡ ከአዲሱ አሰልጣኝ ጋር በመሆን በጥር የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች በመያዝ በሊጉ ለመቆት እንደሚሠራ ተጠቁሞ ነበር። ይሁንና የክለቡ አለመረጋጋትና የውጤት ማጣቱ በመቀጠል አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማም ከክለቡ ጋር ሊለያይ ግድ ሆኗል። እሱን በመተካት የቀድሞ የክለቡ ዝነኛ ተጫዋች ስምዖን ዓባይን በዋና አሰልጣኝነት ቢሾምም የክለቡ ደካማ አቋም ቀጥሎ ከሊጉ ሊወርድ ችሏል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባከናወናቸው 25 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው። በ25ኛ ሳምንት መርሐግብር ከመቻል ጋር ባደረገው ጨዋታ በአቻ ውጤት በማጠናቀቁ በሊጉ ለመቆየት የነበረውን ጭላንጭል ተስፋ ያጨለመ ሆኗል። በነዚህ ጨዋታዎች 9 አቻ እና 15 ሽንፈቶችን አስተናግዶ 22 ጎሎችን አስቆጥሮ 40 ጎሎች ተቆጥሮበት በ18 የጎል እዳዎች አምስት ጨዋታዎች እየቀሩት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ሊወርድ ግድ ሆኖበታል። ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር እኩል 12 ነጥቦችን በመያዝ በጎል እዳ በልጦ 15ኛ ደረጃን በመያዝ ሁለተኛው ወራጅ ክለብ መሆኑን ያረጋገጠውም በዚህ መንገድ ነው።
አሰልጣኝ ሰምዖን አባይ ከሊጉ ላለመውረድ ስላደረጉት ጥረት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት፣ በአጠቃላይ የዓመቱ ጉዞ የተዘበራረቀ እንደሆነና ቡድኑን ለመደገፍ ከአስተዳደሩ ቦርድ ጀምሮ የተደረገው ጥረት ጥቂት ቢሆንም በደጋፊው ረገድ ጥረት ማድረጉን አብራርቷል። “ብዙ የተዘበራረቁ ነገሮች ነበሩ እነሱን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል ግን አልተሳካም” በማለትም አሠልጣኙ ተናግሯል። የክለቡ በሊጉ የመቆየት ጭላንጭል ተስፋ ተሟጦ በመውረዳቸውም ማዘኑን አክሏል።
ከፕሪሚየር ሊጉ የሚወርደው ሦስተኛ ክለብ ያልተለየ ሲሆን ማን ይሆናል የሚለው ጉዳይም አጓጊ ነው። በርከት ያሉ ክለቦች የመውረድ ስጋት ቢኖርባቸውም ከ5 ቀሪ ጨዋታዎች በኋላ ምላሽ የሚያገኙ ይሆናል። ከከፍተኛ ሊጉ ወድ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉ ሦስት ክለቦች ባለፈው ሳምንት መለየታቸው ይታወቃል። ሻሸመኔ ከተማ፣ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አላባ አምበሪቾ በ2016 የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦች ናቸው።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2015