ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2015 ዓ.ም የውድድር ዓመት ወደ ማገባደጃው ተቃርቧል:: የሊጉ ቻምፒዮን ለመሆን ከሚደረገው ፍልሚያ ይልቅ ወደ እታችኛው እርከን ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበም ይገኛል:: ከሊጉ በሚወርዱት ክለቦች ተተክተው ከከፍተኛ ሊግ ያደጉ ሦስት ክለቦች ቀደም ሲል ተለይተዋል:: ሻሻመኔ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ በ2016 የውድድር ዓመት ከፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች መካከል መሆናቸውን አረጋግጠዋል::
ሊጉ በውድድር ዓመቱ ከመጫወቻ ሜዳ ችግር አንስቶ በርካታ ፈታኝ ክስተቶችን እያስተናገደ ሊጠናቀቅ የጥቂት ጨዋታዎች ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል:: በቀሪዎቹ ጨዋታዎችም በሊጉ ለመቆየት የሚደረገው ፍልሚያ አጓጊ ሆኗል:: ፕሪምየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 16ቱን በማሸነፍ፣ 7ቱን አቻ በመውጣት እና በሁለቱ ብቻ በመሸነፍ በ55 ነጥቦችና 30 የግብ ክፍያዎችን ይዞ ከላይ ሆኖ በመምራት ላይ ይገኛል:: ባህርዳር ከተማ ተመሳሳይ ጨዋታዎችን በማድረግ 50 ነጥቦችን ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ የዘንድሮ የሊጉ ክስተት የሚባለው ኢትዮጵያ መድን 44 ነጥቦችን ሰብስቦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል::
ሊጉ የቴሌቪዥን ሽፋን ካገኘበት ወቅት አንስቶ የተሻለ ገቢና ሽፋን ማግኘት ችሎ ነበር:: ዲኤስ ቲቪ ዘንድሮም በገባው ውል መሰረት እስከ 25ኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎችን ወደ ተመልካች ሲያደርስ ቆይቷል:: ነገር ግን ከ25ኛ ሳምንት ጀምሮ ያሉ ጨዋታዎች ስርጭት እንደማይኖራቸው ተጠቁሟል::
የስርጭት ሽፋን አለመኖሩ ሊጉ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ቢሆንም ከፕሪምየር ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማን ይወርዳል የሚለው ይጠበቃል:: በውድድር ዓመቱ ካሳዩት አቋም፣ ከሚቀሩት ጨዋታዎችና ከሰበሰቧቸው ነጥቦች አኳያ መውረዳቸውን ያረጋገጡ ሲኖሩ፤ ባሳዩት ደካማ አቋምና በሰበሰቧቸው ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው እንዲቀመጡና ከሌሎች ክለቦች በይበልጥ የመውረድ ስጋት ውስጥ የገቡም አሉ::
ቀጣይ የሚደረጉት 5 ቀሪ ጨዋታዎች ወራጅ ክለቦችን ሙሉ ለሙሉ ለመለየት ወሳኝ በመሆናቸው የሚደረገው ትንቅንቅ ቀላል የሚባል አይሆንም:: በወራጅ ቀጠናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ11 ነጥብ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ በ12 ነጥብ እና አርባ ምንጭ ከተማ በ26 ነጥቦች ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ይገኛሉ::
በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በውድድር ዓመቱ ካደረጓቸው 25 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት ሁለቱን ብቻ ሲሆን፤ በ6 ጨዋታዎች አቻ ወጥተው በ17 ጨዋታዎች በመሸነፋቸው በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው አብቅቶለታል:: በአጠቃላይ በሊጉ 57 ግቦች በማስተናገድ 40 የግብ እዳዎችን በመያዝ ከየትኛውም ክለብ በላይ ከፍተኛ ግብ በማስተናገድ ቀዳሚም ናቸው:: በ25ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ መረሃ ግብር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት በመለያየታቸው 5 ቀሪ ጨዋታዎች እየቀራቸው ከሊጉ መውረዳቸውን ቀድመው ማረጋገጥ ችለዋል:: በዚህም መሰረት ክለቡ ወደ ሊጉ ባደገበት ዓመት ተመልሶ ይወርዳል::
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እግር ኳስ ክለብ እንዲሁ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደገበት ዓመት ተመልሶ ሊወርድ ተቃርባል:: ክለቡ ከሊጉ ከወረደ ከዓመታት በኋላ ቢመለስም፤ በውድድር ዓመቱ ያሳየው አቋም ደካማ የሚባል ነው:: በአጠቃላይ ካደረጋቸው ጨዋታዎች በአብዛኛዎቹም ተሸንፏል:: ክለቡ ከቀሩት ጨዋታዎች አንጻር ታዓምር ካልተፈጠረ በቀር መውረዱ የማይቀር ይመስላል::
ከአሰልጣኙ መሳይ ተፈሪ ጋር በውጤት ማጣት ምክንያት የተለያየውና በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ሌላኛው ክለብ አርባ ምንጭ ከተማም የመውረድ ስጋት ተጋርጦበታል:: 25 ጨዋታዎችን አከናውኖ 4 አሸንፎ በ14 አቻ፣ በ7 ተሸንፎ 26 ነጥብና 5 የጎል እዳ ይዞ 14 ደረጃ ላይ ይገኛል:: በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ተስፋ ቢኖረውም ቀሪ ጨዋታዎቹን በሙሉ አሸንፎ የሌሎቹን ነጥብ መጣል ይጠብቃል::
ሌሎች በሊጉ መቆየታቸውን ያላረጋገጡና የመውረድ ስጋት ያለባቸው ክለቦች ወልቂጤ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ፣ ሲዳማ ቡና፣ ድሬዳዋ ከነማ፣ ሃዋሳ ከተማ እና መቻል ናቸው:: ከ13ኛ እስከ 9ኛ ደረጃ ያሉ ክለቦች በሂሳባዊ ስሌት የመውረድ ስጋት አለባቸው:: እነዚህ ክለቦች ካላቸው ነጥብና የጎል እዳ አኳያ ከቀሯቸው 5 ጨዋታዎች ቢያንስ አራቱን ማሸነፍ የሊጉ ቆይታቸውን ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥላቸው ይሆናል:: 14ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ክለብ ጀምሮ በሊጉ የመቆየት እድል አላቸው:: በመሆኑም በቀሩት ጨዋታዎች ማን ቻምፒዮን ይሆናል፣ ከሊጉ ይወርዳል እና በኮንፌዴሬሽን ካፕ ይሳተፋል የሚሉት መልስ የሚያገኙም ይሆናል::
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2015 ዓ.ም ከ23ኛ እስከ 27ኛው ሳምንት ባለው መርሃ ግብር መሰረት በሃዋሳ ከተማ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እየተደረገ ይገኛል:: ቀጣይ ከ28ኛ ሳምንት እስከ 30ኛው ሳምንት የመጨረሻ ሳምንታት ውድድሮች ደግሞ በአዳማ ከተማ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚደረጉም የሊጉ አክስዮን ማህበር አሳውቋል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2015