የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በንግድ ባንክ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ
ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስጠሩ አትሌቶችን ካፈሩ ብሄራዊ ውድድሮች መካከል ቀዳሚው ነው:: ከ1963ዓም አንስቶ በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር በ2012ዓም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከመሰረዙ በቀር ሳይቆራረጥ የተካሄደ ትልቁ የአትሌቲክስ ውድድር ነው:: በሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ ስፖርቶች የሚደረገው ይህ ቻምፒዮና ታዋቂና ጀማሪ አትሌቶችን በማፎካከር እንዲሁም አዳዲስ ከዋክብትን በማሳየት ዘልቋል:: ከሻምበል አበበ ቢቂላ አንስቶ እስካሁን ድረስም በኦሊምፒክ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ሀገራቸውን የወከሉ አትሌቶች ፈልቀውበታል።
የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዋዜማ ላይ በተከናወነው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይም አዳዲስ አትሌቶች ከ20 በላይ ከሆኑ ስመጥር አትሌቶች ጋር ፉክክር በማድረግ ከትናንት በስቲያ ተጠናቋል። ለ6ተከታታ ቀናት የተካሄደው ይህ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል:: በድምቀት በተደረገው ቻምፒዮና ክለቡ የበላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ የቻለውም 358 ነጥብ በማስመዝገብ ነው:: ክለቡ በሁለቱም ጾታ ድምር ውጤት ባገኘው ብልጫ የአጠቃላይ ቻምፒዮናው አሸናፊም ሊሆን ችሏል::
መቻል እና ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት በሴቶች አጠቃላይ ውጤት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሲሆኑ፤ መቻልና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በወንዶች ለደረጃ በቅተዋል:: ክለቦቹ በሰበሰቡት ጠቅላላ ውጤትም 295 አጠቃላይ ነጥብ ያገኘው መቻል ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ158 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽሟል:: በማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩም ላይ በሁለቱም ጾታ እንዲሁም በድምር ውጤት ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ አትሌቶች ሜዳሊያ ሲያጠልቁ፤ ክለቦች ደግሞ የገንዘብ እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል::
በማጠቃለያው ዕለትም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ አበራ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል:: በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶችና ክለቦችም ከዕለቱ የክብር እንግዶች እጅ ሽልማታቸውን ተረክበዋል::
በስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት እጥረት ምክንያት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተካሄደው ቻምፒዮናው በእድሳት ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም እንዲሁም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ቀሪዎቹ ውድድሮች ተከፋፍለው ነው የተከናወነው:: 11ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 30 ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማት የሚካፈሉበት ቻምፒዮናው፤ በወንድ 743 እንዲሁም በሴት 527 በጥቅሉ 1ሺ270 አትሌቶችን በማሳተፍ ብልጫ ታይቶበታል:: ለዓመታት ከቻምፒዮናው ርቆ የቆየው የትግራይ ክልልም በዚህ ቻምፒዮና ወደ ውድድር መመለሱ ታውቋል::
ከጥቂት ወራት በኋላ 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሃንጋሪዋ ቡዳፔስት እንደሚከናወን ይታወቃል:: ይህንን ተከትሎም ቻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ መልካም አጋጣሚ ሲሆን፤ ሃገራቸውን በ10ሺ ሜትር የሚወክሉ አትሌቶች የሰዓት ማጣሪያ ለማድረግ የሚመረጡበት ቅድመ ውድድርም ሆኗል:: በዚህም በሁለቱም ጾታ ከ1-8 የወጡ አትሌቶች በርቀቱ ባላቸው ምርጥ ሰዓት ከተመረጡ አትሌቶች ጋር ከሳምንታት በኋላ በሃዋሳ በሚከናወነው ማጣሪያ ላይ የሚፎካከሩ ይሆናል:: የውድድር ዕድል ከመፍጠርና ተተኪ አትሌቶች ከማፍራት ባለፈ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች መዘጋጃ እና ማጣሪያ የሆነው ቻምፒዮናው በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የሚካፈሉበት እንደመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚሳተፉባቸው የግል ውድድሮቻቸው አቋማቸውን የለኩበት መድረክ ሆኖ አልፏል::
ከመጪው ሰኔ 1-4/2015ዓም ድረስም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ለ3ኛ ጊዜ ይከናወናል:: የሻምበል አበበ ቢቂላ ኢንተርናሽናል ማራቶን ደግሞ ለ39ኛ ጊዜ በመጪው ሰኔ 18/2015ዓም ይደረጋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2015