በበዙ ትናንቶች ድልድይ እየተሸጋገረ ዘመናትን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል። ትናንትናን በዛሬ እየቃኘ ዛሬ ደግሞ አዲስ ዘመን ድሮ እያለ ኋላውን በትዝታ ይቃኛል:: አዲስ ዘመን ድሮ ምን ይመስል ነበር…ቆየት ካሉ የአዲስ ዘመን ትዝታዎች ቀንጨብጨብ እያደረግን እንቃኛቸዋለን:: በህገ ወጥ መንገድ የተዘጋጀ ሥጋ ተያዘ፣ ሰርዞና ደልዞ የተያዘ አጭበርባሪ፣ የገበሬዎች በዓል በፍቼ ተከበረ፣ በጭላሎ ወረዳ የተያዘ ወንበዴና ሌሎችም ቆየት ያሉ የጋዜጣውን ዘገባዎች በማካተት ለትውስታ አቅርበናል::
በሕገ ወጥ መንገድ የተዘጋጀ ሥጋ ተያዘ
(ኢ.ዜ.አ) በሕገ ወጥ መንገድ የታረዱ የ14 በሬዎች ስጋ ከቃሊቲ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለማስገባት ሲሞከር ትናንት ሰኔ 11 ቀን 1955 ዓ.ም አቃቂ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ተያዘ:: ንብረትነቱ አቃቂ ማዘጋጀቤት በሆነ አፈር ገልባጭ መኪና ላይ ተጭኖ ከነበረው ከዚህ ስጋ ጋር 12 ሰዎች በአንድነት ተጭነው ስጋውን እየረገጡ ይጓዙ እንደነበር ጓድ ደበበ ጌታሁን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የእርድ አገልግሎት ማስተባበርያና መቆጣጠርያ ዋና ክፍል ኃላፊ ገልጠዋል::
(አዲስ ዘመን ሰኔ 11 1955 ዓ.ም)
ሰርዞና ደልዞ የተያዘ አጭበርባሪ
በአዳማ ወረዳ ግዛት በወንጂ ምክር ቤት ወረዳ ግምቱ በወይዘሮ ገነት ስም የተመዘገበ አንድ ጋሻ መሬት የ54 ዐመት ግብርና አስራት የትምህርት ታክስ ባለመክፈሉ ወኪላቸው የሆነው አቶ ተረፈ ወልደ ገብርኤል የተባለው ግብሩን ከአጠፌታው ጋር እንዲከፍል ቢጠየቅ ከፍ ያለ ማስረጃ አለኝ ስላለ ወንጀል መዝገብ ቁጥር 1ሺ 1መቶ 85/54 ዓ.ም ተከሶ ከቀረበ በኋላ፤ አለኝ ያለውን ማስረጃ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ስላዘዘ ያዋጣኛል ብሎ የፈጠረው የማችበርበር ዘዴ ካርኔውን በተመሳሳይ ስርዝድልዝ ለውጦ ማቅረብ ስለነበረ መሬቱ ከወይዘሮ ገነት ለወይዘሮ ጽጌ ተዘዋውሮ ኑሮ መጀመርያ ገነት የሚለውን በስርዝ ድልዝ ጽጌ፤ የ53 የሚለውን የ54 በማለት አስተካክሎ አቀረበ:: እዚህ ላይ በካርኔ ውስጥ 2/53 ተጽፎ ኑሮ አንደኛው ሲስተካከል፤ 2ኛው ተዘሎ ከመቅረቱም በላይ፤ ስርዝድልዙም ዳኛውን ማጠራጠሩ አልቀረም ነበርና ፤ የክፍሉ ግምጃ ቤት ሂሳብ ሹም ቀርቦ ይህ ካርኔ ሴሪ ቁ/9ነኛ ቁጥሩም 11ሺ 210 ሲሆን በ53 ዓ.ም እንጂ በ54 ዓ.ም ፈጽሞ የግብር መቀበያ ካርኔ አልነበርም በማለት፤ ወድያው ቀሪው ተፈልጎ በመገኘቱና ተከሳሹ ያቀረበው ካርኒ ስርዝ ድልዝ መሆኑ ከታወቀ በኋላ፤ ጥፋተኝነቱን በማረጋገጥ ፍርድ ቤቱን አስተያየት እንዲያደርግለት ስለጠየቀ በወንጀል መዝገብ ቁጥር 1ሺ 403/54፤50 በር እንዲቀጣ ተፈርዶበታል ሲል የአዳማ ወረዳ ግምጃ ቤት በላከልን ጽሑፍ ገልጧል::
(አዲስ ዘመን ህዳር 15 1955 ዓ.ም)
የገበሬዎች በዓል በፍቼ ተከበረ
ፍቼ ጥቅምት 24 ቀን 1955 ዓ.ም በግራር ጃርሶ ወረዳ ግዛት አራት ማርያም ከተማ የአውራጃው ገዥ ክቡር ፊት አውራሪ ዓምዴ አበራ በተገኙበት በእርሻ ወኪሉ በአቶ ኃይሉ ስያሜ አማካኝነት የአባትና የወጣቶች ገበሬዎች በዓል ተከብሮ ውሏል:: ይህንንም በዓል ለማክበር ከእርሻ ሚኒስቴር አቶ አውግቸው ካሳ የእርሻ ክፍል ምክትል ዲያሬክተርና ሚስቴርዴን ሐንሮልዳ፤ የእርሻ ኤክሳቴንሽን ሹም ሌሎችም ሰራተኞችና ከአምስት መቶ በላይ ሚሆኑ አባት ገበሬዎች ተገኝቶ ነበር::
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 1955 ዓ.ም)
በጭላሎ ወረዳ አንድ ወንበዴ ተያዘ
በአሩሲና በባሌ ጠቅላይ ግዛት በሚገኙ ተራራዎችና ሸንተረሮች እየተዘዋወረ ከግብረ አበሮቹ ጋር ሆኖ የብዙዎቹን ሰላማዊ ሰው ህይወት በማጥፋትና በማሰቃየት፣ ንብረት በማቃጠልና በመዝረፍ ልዩ ልዩ ወንጀል ሲፈጽም ነበረው ኮሮርሳ ሴዎ የተባለ ወንበዴ ታህሳስ 8 ቀን 1955 ዓ.ም በበቆጂ ወረዳ ገዥ በአቶ ፍሥሐ ወልደ ሚካኤልና በአራት ፖሊሶች ተከቦ የተያዘ መሆኑን ከወረዳ ግዛቱ የተላለፈልን ጽሑፍ ያረጋግጣል:: ወንበዴው ኮሮሳ ሴዎ የተያዘው በበቆጂ ወረዳ በአቶ ጌታቸው በለጠ ባላባትነት ሌሙጋለማ ቀበሌ ሐጂ ካዎ ከሚባለው ሰው መኖርያ ቤት ሲሆን፤ አሁን በወረዳው ግዛቱ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ታስሮ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል::
(አዲስ ዘመን ታኅሳስ 15 1955 ዓ.ም)
የአንበሳ አውቶቢስ ማኅበር አዳዲስ አውቶቢሶችን ሊያስመጣ ነው
ከሺፈራው መንገሻ
በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር ግምታቸው ፰፻፹ ሺህ ብር የሆነ ፲፩ አውቶቡሶች ከኢጣልያና ከጀርመን አገር እንደሚያስመጣ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ወርቅነህ ገለጡ::
የተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር በጠቅላላው ፩፻፷፩ አውቶቡሶች አሉት ::ከእነዚህም ፩፻፴ የሚሆኑት ለከተማ ሕዝብ አገልግሎት ሲቀርቡ ፴፩ዱ ለጠቅላይ ግዛት የተመደቡ ናቸው::
በ ፲፱፻፷፩ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየቀኑ ፩፻፮ አውቶቡሶች ፯፻፴ ሺህ መንገደኞችን አመላልሰዋል::
የተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር የተቋቋመው በ፩፻፺ ማኅበርተኞች ነው::ከነዚህም ውስጥ አንድ አራተኛው አክሲዮን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጎት ሥር የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሲሆን፤ ፩፴፭ አክሲዮን በኢትዮጵያውያን ፤ ፲፪ በውጪ አገር ዜጎች የተያዘ ነው::
ማኅበሩ ወደፊት ስላለው ዕቅድ ሥራ አስኪያጁ ሲገልጡ፤ ፩ኛ / በየመንገዱ ዳር በሚገኙት መሣፈሪያዎች መጠለያዎችን ለመሥራት፤ ፪ኛ/ማዘጋጃ ቤት የሚሠራውን መንገድ ድርጅቱ እየተከተለ አዳዲስ መኪናዎችን ለማቅረብ ፤ ፫ኛ/ መንገደኛ በሚበዛባቸው መስመሮችና ከሥራ በመውጪያና በመግቢያ ሰዓቶች ላይ የአውቶቡሶችን ኃይል ለመጨመር፤፬ኛ/ የተሳፋሪውን ምቾት ለመጠበቅ የጽዳትና የጥበብ ሁኔታ የሚያስከትሉትን ጭነቶችም በማስቀረት ለማገልገል ከመታቀዱም በላይ እስከ የካቲት ወር መጨረሸ ድረስ ፲ የፊያት አውቶቡሶችና ፩ ልዩ ማርቸዲስ በጠቅላላው ፲፩ አውቶቡሶችን አስመጥተን የነበረውን ችግር ለማስወገድ ነው ብለዋል::
(አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 13 ቀን 19 62 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2015