የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወንዶች እግር ኳስ ክለብ ከስድስት ዓመታት በኋላ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል። ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተው በ2009 ዓ.ም ነበር። በሶስት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር፤ ክለቦች ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግ የሚያደርጉትን ፍክክር አጓጊ በማድረግ ከመጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል:: ቀደም ሲል በምድብ ሁለት ሲወዳደር የነበረው ሻሻመኔ ከተማ ከሊጉ ከወረደ ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ ተመልሶ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉ ይታወሳል:: ከሱ በመቀጠል በምድብ አንድ የሚወዳደረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወንዶች እግር ኳስ ክለብ ከ6 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ዋናው የሊግ እርከን ያደገ ሁለተኛው ክለብ መሆኑን አረጋግጧል::
በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ባከናወናቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ ነጥቦችን በመሰብሰብ ተከታዮቹን በሰፊ ርቀት በማስከተል ወደ ሊጉ መመለሱን ማረጋገጥ ችሏል:: የከፍተኛ ሊግ ስፔሻሊስቱ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ መድንን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደግ የሚታወቅ ሲሆን፤ በዘንድሮ ዓመት ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በድጋሚ በማሳደግ ታሪክ መስራቱን ቀጥሎበታል:: በአሰላ ከተማ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተዘዋወሩት ቀሪ የምድብ አንድ ጨዋታዎች የዝናቡ ሁኔታ የሰዓት ለውጥ እንዲደረግባቸው ተጽዕኖ አሳድሯል:: የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በሊጉ በአራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ጋሞ-ጨንቻ ጋር ጨዋታውን ከማድረጉ አስቀድሞ ነው ወደ 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ መቀላቀሉን ያረጋገጠው::
ቡድኑ ተከታዩ ቤንች ማጂ ቡና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 2ለ1 መሸነፉን ተከትሎ ከስድስት የውድድር ዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መመለሱን አረጋግጧል። ቡድኑ ሊጉን በአምስት ነጥብ ልዩነት በመምራት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግ የሚያደርገውን ጥረት ማሳካት ችሏል:: ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድቡ ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎች 54 ነጥብና 24 የጎል ክፍያዎችን በመያዝ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች እየቀሩት ነው ማደጉን ያረጋገጠው:: ክለቡ የሚቀሩትን መረሃ ግብሮች ማሸነፍ የሚችል ከሆነ በከፍተኛ ሊግ 60 ነጥቦችን በማስመዝገብ ታሪክ መስራት ይችላል::
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የቀደመ ትልቅ ስም ያለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 ከፕሪሚየር ሊጉ በመውረዱ የመፍረስ አደጋ አጋጥሞት እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እያስመዘገበ በነበረው ደካማ ውጤት ከ33 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለመፍረስ ተገዷል:: ክለቡ በ1975 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ በ1992 ዓ.ም የግል ባንኮችን አባል አድርጎ የኢትዮጵያ ባንኮች ስፖርት ማህበር በሚል በአዲስ አደረጃጀት መቅረቡ ይታወሳል:: በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በርካታ ክለቦች
ከሊጉ በወረዱ ማግስት የመፍረስ አደጋ ያጋጠማቸዋል:: ዳሽን ቢራ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሙገር፣ ጉና እንዲሁም አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ በወረዱ ዓመት ክለባቸውን ማፍረሳቸው ይታወሳል:: የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ በ1996 ዓ.ም በታሪኩ ብቸኛውን የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን፤ በ1997 እና 2002 ዓ.ም የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ላይ መሳተፍ ችሏል:: ከሁለት ዓመታት በፊት ግን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንን(ኢኮስኮን) ክለብ በመግዛት በከፍተኛ ሊጉ ተሳትፎ በማድረግ ቆይቷል። በከፍተኛ ሊጉ በነበረው ቆይታም በከፍተኛ ትግል ዳግም ፕሪሜየር ሊጉን የመቀላቀል ተስፋው እውን አድርጓል::
‹‹የቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መመለስ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞችና ለሌሎች የቡድኑ ደጋፊዎች ታላቅ የምስራች እንደሚሆን አልጠራጠርም›› በማለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልሰን አሰፋ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:: የስፖርት ቡድኑ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞችና አመራሮች ቀሪዎቹን ጨዋታዎች በድል በማጠናቀቅ የሚያደርገውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ጠንክረው መስራት ይገባቸዋልም ብለዋል:: እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ባንኩ የእግር ኳስ ቡድኑን ወደ ቀድሞ መልካም ስሙ ለመመለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው:: በመጪው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቡድኑ በተሻለ ብቃት ተሳታፊ እንዲሆንም አስፈላጊው ዝግጅትና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል:: ክለቡ ቡድኑን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በድጋሚ እንዲመለስ ጉልህ ሚናን ለተጫወተው የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በጸሎት በ2016 ዓ.ም ከክለቡ ጋር እንደሚቆይም ማረጋገጫ ሰጥቷል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም