ሙዚየሞች የሰው ልጆች ቀደምት ታሪክ፣ ማንነት፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ስልጣኔና ጥበብ እንዲሁም በርከት ያሉ በምድራችን ላይ የተከሰቱና ለወደፊትም የሚከሰቱ ሁነቶችን በጉያቸው ይይዛሉ። ከዚህ አኳያ ሲታይ የሚሰጡት አበርክቶና ጠቀሜታ በእጅጉ ከፍተኛ ነው። የአንድን አገር የተፈጥሮ፣ የታሪክና ልዩ ልዩ የቅርስ ሃብቶች በአንድነትና በአንድ ስፍራ ማግኘት ከፈለግን ወደ ሙዚሞች ማቅናት፣ ጊዜ ወስደን መመልከት፣ የምንፈልገውን መረጃ ጠንቅቀን እንድንረዳና በቀላሉ እንድናገኝ ይረዳናል። ለዚህም ነው ለመዝናኛ፣ ለጠቅላላ እውቀትም ሆነ ለምርምር ዘርፍ ሙዚየሞች ተመራጭ ስፍራዎች እንደሆኑ የሚጠቀሰው። በተለይ የዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ቀልብ ለመሳብና የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ሙዚየሞች ጉልህ ደርሻ እንዳላቸውም ይገለጻል።
ዓለም አቀፉ የሙዚየሞች ካውንስል ሙዚየም ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመነሳት በየዓመቱ ግንቦት 10 ቀን “የሙዚየም ቀን” እንዲከበር ደንግጓል። ከዚህ መነሻም አገራት ያላቸውን ታሪካዊ ሃብቶች በማልማት፣ በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅና ተደራሽነታቸውን በማስፋት አንፃር ለንቅናቄ ማስጀመሪያና ግንዛቤ ማስጨበጫ መንገድ ይህንን ቀን ይጠቀሙበታል።
ይህ ካውንስል ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ46ተኛ ጊዜ የሚከበረው የሙዚየም ቀን “ሙዚየሞች፣ ለዘላቂነት እና ደህንነት” የሚል መሪ ሃሳብ እንዲኖረው አርጎ ካሳለፍነው ሃሙስ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በልዩ ልዩ መሰናዶዎች እንዲከበር እድርጓል። ኢትዮጵያም ይህንን ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ እያከበረች ትገኛለች።
ሙዚየሞች ለደህንነት እና ለማህበረሰባችን ዘላቂ ልማት ቁልፍ አስተዋፆኦ አላቸው። አስፈላጊ በሆኑት የጋራ ማህበረሰባዊ ስሪቶች ውስጥ፣ አወንታዊ ለውጥን ለማዳበርና ትልቅ ለውጥ ለመፍጠር በልዩ ሁኔታ ያግዛሉ። ሙዚየሞች የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት አስተዋፅኦ የሚያደርጉባቸው ብዙ መንገዶች እንዳሉ ዓለም አቀፉ የሙዚየሞች ካውንስል ይገልፃል። በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና እርምጃውን ከመደገፍ አንፃር ብሎም ማህበራዊ መገለልን ከማስቀረት እና የአእምሮ ጤናን ከማሻሻል አኳያ ሚናቸው ጉልህ መሆኑን ነው ካውንስሉ የሚገልጸው።
የዘንድሮው መሪ ሃሳብም ይህንን መሰረት አድርጎ እንደተቀረፀ ካውንስሉ ይፋ ባደረገው መረጃ አስታውቋል። “ሙዚየሞች ጠቃሚ ናቸው፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ታሪክን፣ ባህል እና እሴቶችን ስለሚጠብቁ እና ስለሚያሳዩ” በማለት ስላለፈው፣ ስለ አሁኑ እና የወደፊቱ ማስረጃ ውበትና ግንዛቤ የምንረዳው ከእነዚህ ተቋማት መሆኑን ይጠቁመናል። እንዲሁም በሁሉም እድሜ ያሉ ሰዎችን በተጨባጭ ተሞክሮ እንደሚያስተምሩ ይገልፅልናል። ሙዚየሞች ሰዎች ራሳቸውን፣ ታሪካቸውን እንዲገነዘቡ እና ህይወታቸውን እንዲያበለጽጉ እንደሚረዳቸው ያመለክታል።
ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን ሰዎች ሙዚየሞችን እንዲጎበኙና እንዲዝናኑ ለማበረታታትና ሙዚየሞች በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚያስችል ግልፅ ዓላማ ላይ ተመርኩዞ መከበር እንዳለበትም ካውንስሉ አሳውቋል።
አቶ ደምረው ዳኜ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የብሄራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክን፣ ቅርስን፣ ባህልን፣ ማንነትን፣ ጥበብን፣ ቀደምት ስልጣኔንና እውቀትን የያዙ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሙዚየሞች እንዳሉ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ይናገራሉ። ከነዚህ ውስጥም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም እንደሚገኝበት ይገልጻሉ።
“ዘንድሮ እያከበርነው ያለውን የዓለም የሙዚየም ቀን አስመልክተን በብሄራዊ ሙዚየም ነፃ የጉብኝት አገልግሎት ሰጥተናል” የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ባሻገር ለግማሽ ቀን በተደረገ የፓናል ውይይት አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የሙዚየም አስተዳዳሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ይገልፃሉ። ‹‹ሙዚየሞች ለደህንነት እና ለማህበረሰባችን ዘላቂ ልማት›› የሚለውን የቀኑ መሪ ሃሳብ
ዋና ዓላማ ማህበረሰቡና ተቋማቱ ያላቸው ግንኙነትና ግንዛቤ እንዲጠናከር ለማድረግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
“ሙዚየሞች አደራ ተረካቢና ጠባቂዎች ናቸው” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የህብረተሰቡንና የአገርን ቅርስ ይዘው እንደሚገኙ ይጠቁማሉ። እነዚህን ሃብቶች ጠብቀው በመያዝም መልሰው ህብረተሰቡ፣ አዲሱ ትውልድና መላው ዜጎች ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ ቀደምት ስልጣኔና ጥበባቸውን እንዲያውቁ የማድረግ ኃላፊነት ወስደው እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ይህንን ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ የዓለም የሙዚየም ቀን እየተከበረ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት መረጃ አሳውቀውናል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሙዚየሞች ከሰው ኃይል፣ ከበጀት፣ ከህብረተሰቡ ግንዛቤ አንፃርና ከሚሰጣቸው ትኩረት አንፃር በርካታ ችግሮች አሉባቸው” የሚሉት አቶ ደምረው፤ ይህንን ቀን በማስመልከት ችግሮቹ ትኩረት አግኝተው መፍትሄ እንዲያገኙ ድምፅ የሚያሰሙበት አጋጣሚ እንደሆነ ይናገራሉ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ከ200 ሺህ በላይ የቅርስ ስብስብ አለው። በተለይ ከሰው ዘር መገኛ ጋር የሚያያዙ እጅግ በርካታ መረጃዎችና ቅርሶች ይገኙበታል። በቅርቡ የተጀመረና በእቅድ ላይ ያለ “የሰው ዘር መገኛ ሙዚየም” ለመገንባት ሃሳቡ አለ። ትልቅና ራሱን የቻለ ብሄራዊ ሙዚየም ይገነባል የሚል በእቅድም ላይ የተያዘ መረጃ እንዳለ እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአፋር ክልል አካባቢ ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም ይሰራል ለተባለ ሙዚየም ለፕላን ኮሚሽን የተላከ እቅድም እንዲሁ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሙዚየሞችን ቁጥርም ሆነ ጥራትን ለማሻሻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን የሚያመላክቱ ናቸው።
የዝግጅት ክፍላችን በተለያየ አጋጣሚ ለመረዳት እንደቻለው ከግንዛቤ እጥረትም ይሁን መረጃዎችን በአግባቡ ካለማወቅ የተነሳ ዜጎች ወደ ሙዚየሞች ጓዳ ጎራ ብለው ሃብቶቹን የመጎብኘት እንዲሁም መረጃዎችን የማወቅ ልምዳቸው ደካማ ነው። የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ቀደምት ስልጣኔን የሚያሳዩ አርኪዮሎጂካል ሃብቶችን በማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን የመሳብ እንቅስቃሴውም እንዲሁ ክፍተት እንደሚታይበት የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ሙዚየሞችን የማደራጀትና መረጃ የመያዝ ባህሉም እንዲሁ ክፍተት ይታይበታል። ይሁን እንጂ ቁንፅል ቢሆኑም ውስን መረጃዎች እንዲሁ ማግኘት ይቻላል።
የአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና ብቃት ማረጋገጥና የቱሪዝም ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት በ2013 ዓ.ም የሰራው ዳሰሳ፣ በአዲስ አበባ 18 የሚደርሱ ሙዚየሞች እንዳሉ ያመለክታል፡፡ እነዚህ ሙዚየሞች የከተማዋንና የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክ የሚዘክሩ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡ ሙዚየሞችም የሚተደደሩት በመንግስት፣ በሀይማኖት ተቋማት እና በግለሰብ ነው፡፡ ከሙዚየሞቹ መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል።
እንጦጦ ሙዚየም
በእንጦጦ ተራራ አናት በማርያም ቤተክርስቲያን የሚገኝ ሙዝየም ሲሆን፣ በውስጡም የአደዋ ዘመቻ የተነገረበት ነጋሪት፣ የሚኒሊክ አልጋ፣ የንግስና ዘውድ እና ሌሎች በርካታ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡
ኤትኖግራፊ ሙዚየም
የሚገኘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ አሁን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት በመባል በሚታወቀው በቀድሞ ገነተ ልዑል ቤተ-መንግስት ሲሆን፣ እንደሙዚየም የተቋቋመው በ1955 ዓ.ም ነው፡፡
በውስጡም የአገሪቷን ባህል፤ ኪነ-ጥበብ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ እና የመሳሰሉትን ቅርሶች አከማችቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡
ብሔራዊ ሙዚየም
በ1936 ዓ.ም በጥቂት የአርኪዎሎጂ ግኝቶችና የብሔር ብሔረሰቦች አልባሳትና መገልገያ ቁሶች የተጀመረው የማስጎብኘት ተግባር በአሁኑ ወቅት በአራት ቆሚ ኤግዚብሽን ክፍል ተደራጅቷል፡፡ እነሱም፤ ፓለንቶሎጂ ቅድመ ታሪክ ክፍል፣ አርኪዎሎጂና የታሪክ ክፍል (1 ሚሊኒየም -16ክ/ዘ)፣ ኤትኖግርራፊ ክፍል እና ዘመናዊ አርት/ኪነ-ጥበብ / ክፍል ተብሎ ተከፍሏል፡፡
ዙኦሎጂካል የተፈጥሮ ሙዚየም
ይህ ሙዚየም የሚገኘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ /በአራት ኪሎ ግቢ/ ውስጥ ነው፡፡ ከ1100 በላይ ዝርያ ከ200 በላይ በውሀ ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት የሚገኙበት በአገራችን ብቸኛው ሙዚየም ነው፡፡
በአታ ማርያም ሙዚየም
ሙዚየሙ የሚገኘው በታዕካ ነገስት በአታ ለማርያም ቤተክርስያን ውስጥ ነው፡፡ ይህ ባለ አንድ ፎቅ ቤተክርስቲያንና ሙዝየም ሆኖ የሚያገለግለው የተገነባው በ1903 ዓ.ም በንግስት ዘውዲቱ ነው፡፡ የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ፣ የንግስት ጣይቱ፣ የንግስት ዘውዲቱ እና የግብጽ ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ አፅም በቤተክርስቲያኑ የታችኛው ክፍል እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ሙዚየም
ለአዲስ አበባ ከተማ 100 ዓመት ምስረታ የተለያዩ የከተማዋን ታሪኮች፣ ባህሎች እና የመሳሰሉትን እንዲያሳይ በ1979 ዓ.ም በራስ ብሩ መኖሪያ ቤት በመስቀል አደባባይ አካባቢ የተቋቋመ ሙዚየም ነው፡፡
ፖስታ ሙዚየም
ከ1888 ዓ.ም አገራችን ትጠቀምባቸው የነበሩ ቴምብሮችንና በዓለም ያሉትን ቴምብሮች በመሰብሰብ ለትውልድ ለማስተማሪያነት እያገለገለ የሚገኝ ሙዚየም ነው፡፡
ገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የሃይማኖት አባቶች አልባሳትን፣ መስቀል፣ ሃይማታዊ መፀሐፍት እና የመሳሰሉት ይዞ በገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደውል ቤት በ1982 ዓ.ም የተቋቋመ ሙዚየም ነው፡፡
ቅድስት ስላሴ ሙዚየም
በቅድስ ሥላሴ ካቴድራል የሚገኝ ሲሆን፣ በውስጡም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የመስታውትና የግድግዳ የስነ ጥበብ ስራዎች እንዲሁም የራሱ የሆነ የተለያዩ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ ቅርሶች የሚታይበት ሙዚየም ነው፡፡ ካቴድራሉ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አጽም ያረፈበት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ቀብር የተፈጸመበት ነው፡፡
ዞማ ሙዚየም
በአዲስ አበባ መካኒሳ አቦ የሚገኘው ዞማ ሙዚየም በግለሰብ ደረጃ በተፈጥሮ ዕፅዋት ላይ ትኩረት አድርጎ የተመሠረተ ሙዚየም ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በውስጡ ከ10 በላይ በጭቃ በተለያየ ዲዛይን ያሸበረቁ የቢራቢሮ የህይወት ኡደትና የሰው ልጅ የጣት አሻራ ቅርፃቅርፅ የተገነቡ ቢሮዎች አሉት፡፡
ሰማዕታት ሙዚየም
በ1969-1970 ዓ.ም በቀይ ሽብር ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ እንዲሆን በ2002 ዓ.ም በሰማዕታቱ ቤተሰቦችና ጓደኞች “በፍፁም መቼም መደገም የለበትም” (Never Ever Again) በሚል መሪ ቃል የተቋቋመ ሙዚየም ነው፡፡
ቢላሉል ሀበሺ ሙዚየም
በ1992 ዓ.ም ለሙስሊሙና ለተቸገሩ ኢትዮጵያን ማህበረሰባዊ አገልግሎት ለመስጠት በተቋቋመ ዕድር / ማህበር/ የተመሰረተ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ኢስላሚክ ቅርሶች በመሰብሰብ በ2010 ዓ.ም ሳር ቤት አካባቢ እድሩ ባሰራው ባለ 4 ፎቅ ህንፃ ለማህበረሰቡ እንዲታይ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተቋሙ ውስጥ የታዋቂ የእስልምና አባቶች አልባሳት የእስልምና ሃይማኖትን የሚወክሉ ቆብ/ ኮፍያ/ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ጥንታዊ መፅሐፍት፣ መገልገያ ቁሶች እና የመሳሰሉትን ይዞ በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎት እየሠጠ የሚገኝ ብቸኛው ኢስላማዊ ሙዚየም ነው፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2015