በመስኮቱ በኩል እሳታማ ጀምበር ትታየዋለች…በአፍላ የጎህ ጸዳል የተከበበች:: ከእንቅልፉ ሲነሳ ደስ እያለው ነበር..ኮቱን ሲለብስ፣ ከረቫቱን ሲያደርግ፣ ቁርሱን ሲበላ ደስ እያለው ነበር:: ከቀኖች ሁሉ ጠዋት ደስ ይለዋል::
ቢሮው ሲገባ ሮማን የለችም..ዛሬ ገና ቀድሟት መግባቱ ነው:: ጠዋቱን ከሚያሳምሩለት ነገሮች ውስጥ አንዱ ሮማን ናት:: ሳቋ፣ መዐዛዋ:: ቢሮው ውስጥ እሷ መኖሯን ሲያስብ፣ ዓለም ላይ እሷ እንዳለች ሲያውቅ ይባረካል:: በምትቀባው ሽቶ፣ በምትለብሳቸው ጽዱ ልቦሰቿ ሀሴት ያደርጋል::
አይኖቹን በመስተዋቱ ውስጥ ሲወረውር የአንገት ስከርቧን አየው:: ቀድሟት ሳይሆን ቀድማው እንደገባች አሁን ገባው:: እምነቷ ይገርመዋል..ጽናቷ፣ ለስራ ያላት ፍቅር ያስደንቀዋል:: አገራችን ላይ የእሷን አይነት መቶ ጠንካራ ሰዎች ቢኖሩ ሲል ሁሌ ያስባል:: ጥንካሬዋ ሁሌም እምነቱን ይሽርበታል:: ተነሳሽነቷ ሁሌም እውቀቱን ይንድበታል:: ከሁሉም በኋላ ወንዶች በኃይል ይቺን ዓለም የራሳቸው አደረጉ እንጂ ዓለም የሴቶች ትሆን ነበር ሲል ይደመድማል:: ለምንም ነገር ምስክሩ ናት:: ታስደንቀዋለች..::
በህይወቱ ውስጥ ሶስት ሴቶችን ያውቃል:: ከነዚህ ሶስት ሴቶች ጋር እምነትን፣ እውነትን፣ ጽናትን ተቋድሷል:: ሊዲያ የህይወቱ አልፋ ናት:: በመጀመሪያነት ውስጥ ያለውን ገናና እውነት፣ ያለውን ነፍሳዊ ስቃይና ደስታ የሰጠችው.. በመኝታው ግርግም እንደሚያያት የጧት ጣይ ፈክታና ደምቃ የሚያያት የነፍሱ ጠል:: በአሁናዊ የህይወቱ አብራክ ውስጥ እንደሚያየው የሮማን ፈገግታና ሳቅ የሚያስታውሰው:: አስራ ስምንት ዓመቱን ባከበረ በማግስት ነው መንገድ ላይ አግኝታ ካልተዋወኩህ ሞቼ እገኛለው ስትል የተዋወቀችው:: ትውውቃቸውን ወደ ፍቅር ለመቀየር ሳምንት ነበር የፈጀባት:: ያኔ እሷ አስራ ስድስት እሱ አስራ ስምንት ዓመታቸው ነበር:: ከስድስት ወር በኋላ ተለያዩ:: ሊዲያ አባቷ እንግሊዛዊ በመሆኑ ትታው ለንደን ገባች:: ከሊዲያ ጋር ያሳለፋቸው እነዛ ስድስት ወራት በአስራ ስምንት ዓመታት ውስጥ ከእናቱ እቅፍ ቀጥሎ ያገኛቸው የበረከት ወራቶቹ ነበሩ:: እነዛ ስድስት ወራት የህይወቱ ባለቀለም ንጋት ነበሩ:: የሚያፈቅሩትን ሰው እያሰቡ ከእንቅልፍ እንደመንቃትና ወደ መኝታ እንደመሄድ ደስታ እንደሌለ ያወቀው ያኔ ነው..በሊዲያ ፍቅር:: ዛሬም ድረስ በነፍሱ ፍኖት ስር አለች:: ዛሬም ድረስ በልቡ ምድጃ ላይ ፍቅሯና ትዝታዋ ይንቦገቦጋል:: ዛሬም ድረስ ያልጠፋ፣ ዛሬም ድረስ ያልረሳውን እውነት ሰጥታው፣ በምንም የማያገኘውን የትዝታ ረመጥ በህይወቱ ላይ ትታ፣ ነፍሱን በፍቅር እሳት ለኩሳ ላትመለስ ለንደን ገባች::
ሁለተኛዋ ሴት ራሄል ናት:: ራሄልን የትዝታው አንድ አካል አድርጎ መጥራቱ ያስቆጨዋል:: ጭራሽ በትላንቱ ውስጥ እሷን ማወቁ ያበሳጨዋል:: ብዙ ነገሯ ሴጣናዊ ነው:: የሊዲያን እውነት፣ የሊዲያን ፍቅር ልታረክስ ወደ ህይወቱ የመጣች እንጂ ልትባርከው የመጣች አትመስለውም:: ፍቅርን ሳይሆን ራስ ወዳድነትን ይዛ የመጣች ሴት ነበረች:: ከራሄል ጋር መከራ እንጂ ትዝታ የለውም:: በህይወቱ እሷን በማወቁ ይቆጫል:: በህይወቱ እሷን በመቅረቡ ይከፋል:: አብረው የቆዩት ለዘጠኝ ወራት ነው:: በነዚህ ወራት ውስጥ ሊዲያዊ ፍቅሩን ገላ አውሬ አድርጋው ነበር:: ፍቅሯን ከመጥላቱ የተነሳ እንደ እሷና እሱ ምድር ላይ ረጅም ዓመታትን በፍቅር ያሳለፈ ያለ አልመስልህ ብሎት ነበር:: በአንድ የተባረከ ቀን ተለያዩ..ከእሷ ጋር የተለያዩበትን ቀን ሊዲያን እንዳወቀበት ቀን ዓመት እየጠበቀ ለድሀ በመመጽወት ያከብረዋል::
ከራሄል ጋር በተለያዩ በዓመቱ ብስራት ከምትባል ሴት ጋር ተዋወቀ:: ትውውቃቸው ይገርመዋል..ቤተክርስቲያን ደጃፍ ላይ ከራሄል ጋር የተለያዩበትን ቀን አስታውሶ ለአንድ ነዳያን ፍራንክ ሰጥቶ ሲመለስ በእጇ ቡራኬ ይዛ ለመምዕኑ የምታድል አንዲት ሴት ይመለከታል:: ከቡራኬው ሊወስድ ወደእሷ ሲሄድ ቡራኬው አልቆ ነበር… ከደቂቃዎች በኋላ ይቺው ሴት ቡራኬ ልትሰጠው ወደ እሱ ስትመጣ አየ..:: ከምስጋና ጋር ተቀበላት… በዛው ተዋወቁ:: የፈጣሪ ሀሳብ ይገርመዋል:: ፈጣሪ የት ጋ፣ ከማን ጋር፣ እንዴትና መቼ እንደጣፈን አናውቅም..ብስራት የመጨረሻው እንድትሆን ፈልጎ ነበር ግን አልሆነችም በተዋወቁ በዓመቱ ተጋቡ፣ በተጋቡ በሁለት ዓመታቸው ተለያዩ..መጥፎ መለያየት:: የሚሰራበት መስሪያ ቤት ልደት የምትባል ሴት ወደደችው:: አሁን ላይ ሲያስብ ልደት ከሳጥናኤልና ከራሄል ቀጥሎ መጥፎዋ ሴት ትመስለዋለች:: እሱ ሳያውቅ ስለሁለታቸው መጥፎ ነገር ለብስራት ይደርሳት ጀመር:: መጨረሻ ላይ ብስራት ሳትነግረው ጥላው ጠፋች:: ከብስራት ጋር የነበረው ታሪክ ይሄ ነው:: ሊዲያ በተነሳች ቁጥር ልጅነቱ፣ ብስራት በተነሳች ቁጥር ልደት ትዝ ይሉታል..መጥፎ ትዝታ:: በህይወቱ ውስጥ ሊያስታውሳት የማይፈልጋት አንድ ሴት ልደት ናት..ሊረሳቸው የማይችላቸው ሁለት ነፍሶች ደግሞ ሊዲያና ብስራት::
ብስራት እንደ ስሟ ለህይወቱ ብስራት ነበረች:: ከደጀ ሰላም የመለኮት ኃይል ጋር የሚያመሳስላቸው የሆነ ነገር ያላት ይመስለዋል:: በዘላለማት ውስጥ የማይረሱ ዳግማዊ ሊዲያ ይላታል:: አንዳንዴ ሊዲያ በሌላ ሴት ነፍስ ውስጥ ተደብቃ ፍቅረኛው የሆነች ይመስለዋል:: ብዙ ነገሯ መላዕካዊ ነው::
ብስራትን ሳይጨርሳት ሮማንን በመስተዋቱ ውስጥ አያት…የህይወቱን አራተኛ ሴት:: በመኝታው ግርግም እንደሚያያት የንጋት ጀምበር ተውባ:: በመስተዋቱ ውስጥ ሲያያት ለእይታ ሙዚየም የተቀመጠች ቀይ እንቁ መሰለችው:: ወደዳት..ከወደዳት በላይ:: አሰባት..ካሰባት በላይ:: በህይወቱ ውስጥ አብሮት እንዲቆይ የሚሻው አንድ እውነት የእሷ እውነት ነው:: ፍቅሯና ሴትነቷ:: መልካምነቷና ትህትናዋ:: ሮማንን አፍቅሯታል.. እንደ ሊዲያና እንደ ብስራት::
የሚገፋውን አያውቅም ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ በሩ ተራመደ:: እግሮቹ ወደ እሷ እየወሰዱት ከመንገድ አገኛቸው::
ባቀረቀረበት የሆነ ደስ የሚል ነገር ሸተተው:: ቀና ሲል ከፊት ለፊቱ አያት..ወደ እሱ እየመጣች:: ነፍሱ በደስታ በልቡ ውስጥ ሰከረች:: ወደ ህይወቱ እንድትገባ በሚፈልጋት አራተኛዋ ሴት..ሮማን::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2015